Saturday, November 8, 2025

አለቃው መነኩሴ ብቻ 

መቼስ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለች ክፋት መንፈሳዊነት ወይም ጥቅስ ማልበስ የተለመደ ስልት ነው። ምእመኑን አይጠይቅም እልልል
እውን ቤተ ክርስቲያንን መነኩሴ ነው የሚያስተዳድረው?

ማለት ይቀናዋል። ለምን እንዴት ብሎ መጠየቅ ነው ማሰብ የሚባለው። የሚጠይቅ ሰው ለውጥ ፈላጊ ነው። 

ከዚኽ በፊት “ደብር ወገዳም” የሚል ስም አስገርሞኝ ነበር። አኹን ደግሞ “አስተዳዳሪው መነኩሴ ብቻ” የምትለዋ ሌላ ቅጥፈትን እንመልከት። 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ካህን ነው። ካህን መነኩሴም ቄስም ሊኾን ይችላል። መነኩሴ ብቻ፣ ቄስ ብቻ የሚል ካለ ሌላ ድብቅ ተንኮል ይዟል ማለት ነው። እንደ ዛሬው ምንኩስና የከተማ ከመኾኑ በፊት ቤተ ክርስቲያንን የመሩት ካህናት (ቄሶች) ናቸው። 

የደጃዝማቾችና የራሶች ንሰሐ አባት በተለይ በንጉሡ ጊዜ ንሰሐ አባቶቻቸው መነኮሳት እየኾኑ ወደ አስተዳዳሪነት መምጣት ጀመሩ። 

ገዳማት ሥሪታቸው ለመነኮሳት ነው። አበምኔቱ ወይም አስተዳዳሪው መነኩሴ ነው። ቄስ የገዳም አስተዳዳሪ አይኾንም። ገዳም ለመነኮሳት ብቻ ነው። 

ምእመናን የሚገለገሉበት ደብር አጥቢያ አስተዳዳሪው መደቡ ቄስ ነው። መነኩሴም አስተዳዳሪ ይኾናል። ነገር ግን “መነኩሴ ብቻ” የምትለዋ የሉተር ሎጂክ አታስኬድም። ሉተር ነው እምነት ብቻ sola fide መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ sola scriptura ብሎ ፕሬቴስታንትን መውጫ የሌለበት ገደል የከተታቸው። 

ጳጳሳት ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር የበላይ ጠባቂ እያሉ አድባራቱን መምሪያዎቹን ይዘው ምንም ላይሠሩ ቤተ ክርስቲያን ሽባ አድርገዋታል። አራት ኪሎ መዋያ ኾነ። ሊቃውንቱን ገፍተው ራሳቸው ያዙት። 

አሜሪካ ካህን እንደ ልብ በማይገኝበት አካባቢና ደብር፣ ምእመናን ብዙ ሐብታቸው አውጥተው፣ ከልጆቻቸው ትምህርት ቀንሰው ፣ እንቅልፍ አጥተው ሠርተው የገዙት ሕንጻ “አስተዳዳሪው መነኩስ ብቻ” ብሎ ጨዋታ የለም። 

ለሕዝቡ ቅርብ የኾኑት ካህናት ናቸው። የሕዝብ ችግር የውስጥ ፈተና ተጋሪዎች ካህናት ናቸው። “መነኩሴ ብቻ” የምትለዋ ሸፍጥ ቄሶችን እንደፈለገ እያባረሩ ለመኖር ነው። ካህናቱ የማስተዳደር አቅምም መብትም አላቸው። ካህናቱን ለመግፋት የተደረገች የአቡነ ኢብራሂም ሤራ ናት። 

“አስተዳዳሪው መነኩስ ብቻ” ብለኽ ሕግ ከሠራኽ በኋላ የቆብ ዘረኝነትን በራስኽ ላይ አነገሥክ ማለት ነው። አንዱ አንዱን ዘመዱን እየሳበ እድሜ ልክህን መከራ ማየት ነው። አብርሃም ወለዶ ለይስሃቅ ይስሃቅኒ ወለዶ ለያዕቆብ...  የሚለውን እያነበብክ ትኖራለኽ። 

ሕወሃት በእልህ “አሰብን ግመል አጠጡበት” ብላ አሰብን በሕግ ፈርማ ሰጠች። ዛሬ መንግሥት በውጊየ ካላስመለስኩ እያለ ነው። ነገ ብታለቅሱ አትመልሱትም።

የአቡነ ኢብራሂምን ተንኮል ንቁባቸው። አሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ርስት የላቸውም። ባሕር ዳርን እንጂ ባሕር ማዶ አስተዳዳሪ አይደሉም። ለደብራችሁ ችግር ከሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋር ምከሩ። ማንም ጳጳስ ያለ ሀገረ ስብከቱ ማዘዝ አይችልም። 

“ደብር ወገዳም” በቀደመው ሕግ ከሌለ ዛሬ ለምን መጣ? መርዝ አንድ፣ “አለቃው መነኩሴ” ብቻ የሚለው ኹለተኛው መርዝ ነውና ጠንቅቀኽ መርምር። ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊነት እስክንችል ድረስ ወርደን ዝቅ ብለን የምናገለግልበት እንጂ የጉልበትና የሤራ አይደለም። “ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።  በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥  ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ማቴ.20:25

ንዋይ ካሳሁን

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment