Wednesday, November 26, 2025

የዘጸአት ነገረ መለኮት ትርጓሜ

ጉዞ ወደ ከነዓን 

ከነዓን በትርጉሙ ዝቅ ያለ ትኁት የሚል ትርጉም ሲኖረው የሸንበቆ ምድር ማለት ነው የሚልም አለ። ነገር ግን የኖኅ የልጅ ልጆች የካም
ስንቶች ምንደኞች አሉን ይሆን? 

ዘሮች ሲሆን መጀመሪያ የተስፋይቱን ምድር የኖሩ የጥንቷ ከነዓናውያን ሕዝቦች መጠሪያ ነው። በጥቅሉ የተስፋይቱ ምድርን ያመለክታል። በዮርዳኖስና በሜዲትራንያን መካከል ያለ ነው። ዘፍ.9 እና 10

 የነዌ ልጅ ኢያሱ እንጂ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች ዮርዳኖስን እንዳላሻገራቸው እንዲሁ ክርስቶስ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡባትን ጥምቀት ለአዳም ልጆች አልሰጣቸውም ይኽንን መንፈስ ቅዱስ ሰጣቸው እንጂ። ይኽውም ከእርሱ ጋር ያለ የክርስቶስ መንፈስ ነው። (ዘቦቱ ለከ ምስሌሁ ወምስለ ቅዱስ መንፈስ) እንዲል) ሊጦን።

እርሱም ከሁሉም ሐዋርያት ጋር ይኖራል እነዚኽም በእውነት መንግሥቱን እስኪወርሱም ድረስ በዲያብሎስ ሠራዊት ላይ ድል መንሳትን አሸናፊነትን ይሰጣቸዋል። 

እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን መንግሥተ ሰማያትን ይወርሱ ዘንድ በገነት እንዳኖራቸው አብርሃም በድንኳን አኖረ። ድንኳን ጊዜያዊ ነው። ገነትም ዓለም ሲጠቀለል የምትጠፋ ዓለም ናት። 

የአዳም ልጆች ወደዚህ ዓለም እንደ ወደቁ የአብርሃም ልጆች ከድንኳኖች እስከ ግብጽ ምድር ወረዱ። እንዲኹ ሰው ምቹ ከኾነው ከእናቱ ማኅፀን ወደዚኽ ምድር ይመጣል ይወርዳል። 

ዲያብሎስ በአባቱ አዳም ላይ እንደ ነገሠ ፈርዖንም በአብርሃም ልጆች ላይ ነገሠ። ከዲያብሎስ የሚላከው ሠራዊት ርኩስ መንፈስ ሥራውን ያሠራው ዘንድ ያስገድደው ነበር። በአዳም እንዳደረገው ፈርዖን በእስራኤል ልጆች ላይ አደረገ። 

እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ነጻ ባወጣቸው ጊዜ በኤርትራ ባሕር እንዳሻገራቸው እንዲኹ እግዚአብሔር ሰዎችን በክርስትና ጥምቀት አሻገራቸው። ከዲያብሎስ ነጻ አወጣቸው። በተጠማቂው ላይ የነበረውን ርኩስ መንፈስ በጥምቀት አሰጠመው። ፈርዖን በባሕሩ እንደ ሰጠመ። 

ተጠማቂው ከክርስትና እንደ ወጣ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚገባ የእስራኤል ልጆች ከባሕር መውጣት በኋላ ወደ በረሃ እንዳስገባቸው በድንኳንም እንዳኖራቸው ቤተ ክርስቲያን የድንኳን ምሳሌ ናት። 

ሰው ከጥምቀት በኋላ ወደ ድንኳኑ ሲገባ በውስጧ መና ይበላል። ይኽውም ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ የክርስቶስ ሥጋው ነው። የእስራኤል ልጆች በድንኳን መና ይበሉ እንደነበር። “ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።” ዮሐ.6:35

የተጠመቀ ሰው በመስቀል ላይ ሳለ በወጉት ጊዜ ከክርስቶስ ጎን የፈሰሰውን ውኃን ደም ይጠጣል። የእስራኤል ልጆች በሙሴ በትር ከዓለት የፈሰስላቸውን ውኃ በበረሃ እንደ ጠጡት። የማሰናከያው ዐለት ክርስቶስ ነው። የሚያምንበት አያፍርም። (ይኽንን ለብቻው ወደ ፊት ተርጉመን እናየዋለን)


አዳም በገነት ያለ ድካም ያለ ኃጢአት ያለ ኩስ መውጣት (ወገብ መፈተሽ) ጥቂት ይመገባል። እርሱ ብቻውን ከዓለም የራቀ ነው። እርሱ በእናቱ ማኅጸን በሰማይም በምድርም መካከል እንደ ገነት ነው። 

የነዌ ልጅ ኢያሱ  በእስራኤል ልጆች ላይ እንዳደረገው መንፈስ ቅዱስ ከዲያብሎስ ያድናቸዋል። በበረሃ ሳሉ ኹል ጊዜ  መና ይበሉ ነበር። ይኽውም የክርስቶስ ሥጋው ነው። ከዐለቱም ውኃ ይጠጡ ነበር። ይኽውም የክርስቶስ ደሙ ነው። (ይኽ ነው የምስጢራት ሕይወት sacramental life) የሚባለው። 

ሙሴ የላካቸው ሰላዮች የከነዓንን ፍሬ እንዳመጡ የመንግሥተ ሰማያትን እውቀት የተረዱ ካህናት የመንግሥተ ሰማያት ፍሬ ይሆነውን የክርስቶስን ሥጋውን ደሙን ለምእመናን (ለመሀይምናን) ይሰጣሉ። የእስራኤል ጉበኞች (ጠባቂዎች) ፍሬውን ቀምሰው ሕዝቡ እንዲቀምስ እንዳመጡ ካህናት ከሥጋው ከደሙ ተቀብለው ሕዝቡ መንግሥተ ሰማያትን በውስጧ ይኖሩ ዘንድ እንዲመኙ ያቀብሏቸዋል (ያቆርቧቸዋል)።

ቁርባን በዚያ ሕይወት የምንኖርበት የመንግሥተ ሰማያት መያዧ ነው። ጉበኞቹም ካህናት ናቸው። የነዌ ልጅ ኢያሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። በጥምቀትና በክህነት በውስጣችን የሚያድር መንፈስ ቅዱስ ነው። ጉበኞቹ ከኢያሱ ጋር ወደ ከነዓን እንደ ወጡ እስከ መንግሥተ ሰማያት ድረስ ልባችን ከእርሱ ጋር ይወጣል። ከእርሱ ጋር በወጣን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተረድተን ወደ ምእመናን መጥተን መጣፈጧን እንናገራለን። ከፍሬዋም እናበላቸዋለን። 

ምእመናንን ሰይጣንን በመዋጋት ለማሸነፍ እምነታቸው እንዲጸና የሚያስተምር ካህን ከኢያሱ ጋር የእስራኤልን ልጆች ከነዓን እንዲወርሱ እንዳጸና እንደ ካሌብ  ናቸው። መልካም ምግባር የሚያስተምር ካህን ካሌብ ነው። 

የመንግሥተ ሰማያትን ጣእም አውቀው ሰዎችን የማያስተምሩ እነርሱም የማይማሩ ከመንግሥተ ሰማያት ይልቅ የምድር ገንዘብ ብቻ የሚታያቸው ምእመናንን የማያጸኗቸው እምነታቸውን የማያበረቷቸው ካህናት ሁሉ ከእግዚአብሔር ጸጋ ይጠፋሉ። የከነዓንን የምድሯን ጣእም ያዩ ዐሥሩ ጉበኞች እንደ ጠፉ። ሕዝቡን "እኛ በነሱ ፊት እንደ አንበጣ ነን በውስጧ ያሉ ሕዝቦች ኀያላን ናቸው" ብለው ሕዝቡን አስንፈዋል። 

መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ከባድ ነው ብሎ የሚያስተምር ካህን እንዲሁ ነው። እምነት ያጎደሉትን ከግብጽ የወጡትን ኹሉንም ሕዝብ አጠፋ። በባርነት መንፈስ ከነዓን አይወረስምና። 

ዛሬም ምእመናን የሰይጣን ውጊያ ላይ እንዲያጸኗቸው ለካህናት ይገባል። ሰይጣናት ያለ ጥርጥር ኃያላን ናቸው። ምእመናን ግን እንደ አንበጣ ናቸው። ምእመናን የሚፈልጉት ቦታ ከፍ ያለ ነው። እኛ ካህናትና ምእመናን ክርስቶስ በመስቀል ላይ አለቃቸውን ድል እንደ ነሳው በሲኦል ያሉትን ሁሉ ከሠራዊቱ ከእጃቸው ነጥቶ እንዳዳናቸው ካመንን ስለ እኛ ተዋግቶ ድል ይነሳቸው ዘንድ ያመነውን ከእጃቸው ያድነን ዘንድ ሁሉን ቻይ ነው። ከፍ ወዳለችው ወደ ሰማይ ርስቱ ያደርሰን ዘንድ ወደ እርሱ እንማልድ። 

ሰይጣናት ኀያላን ናቸው እኛ እንደ አንበጣ ነን ብለን ድል ልንነሳቸው አንችልም ብለን ከተጠራጠርን ግን የእስራኤል ልጆች እንደ ጠፉ እንጠፋለን። ወደ ሲኦል እንሄዳለን። ከመናው የበሉ ከዐለት የፈሰሰውን ውኃውን የጠጡ ሁሉ እንዳልተፈወሱ አንድንም። በክርስቶስ ያመንን እኛ ሁል ጊዜ እንቀድሰው እናመስግነው በእነርሱ ላይ ድል መንሳትን ይሰጠን ዘንድ። 
የእስራኤልን ልጆች መውጣት (ፀአት) ምስጢር ተረዳህን?

 አበቃሁ።

ንዋይ ካሳሁን

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment