Saturday, November 29, 2025

የሰሜን አሜሪካ ማኅበራት የጋራ መግለጫ

የሰሜን አሜሪካ ማኅበራት የጋራ ማግለጫ
ቀን ኅዳር ፲፩/፳፻፲፰ ዓ/ም (November 20, 2025)

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 

ምሥራቅ አርሲ በምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ እና መከራ እየተቀበሉ ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን አስመልክቶ የተሰጠ የጋራ መግለጫ

 

ü    የሰሜን አሜሪካ ካሪቢያንና ላቲን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት፣

ü    በኢ/ኦ/ተ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል፣

ü    በኢ/ኦ/ተ/ቤ የማኅበረ በዓለ ወልድ በሰሜን አሜሪካ

ü    ዋልድባን እንታደግ ሰሜን አሜሪካ

 

ይድረስ የንጹኃን ደም ሲፈስ ግድ ለሚላቸው የእምነት ተቋማት፣ የማኅበራዊ ሚድያ ኃላፊዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እና የሌሎችም ተመሳሳይ ድርጅቶች መሪዎች በሙሉ፦ 

 

ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ። ምሳሌ ፳፱፥፲

 

ክብር የሆነውን በሥላሴ አምሳል የተፈጠረን ሰው ነፍስ መግደል ቀላል ሆኖ በሚታይባት የኢትዮጵያ ምድር ሕፃናት እና አረጋውያን እንዲሁም ልጆች እና ወጣቶች በግፍ ሲገደሉ ማየት እና መስማት የዕለት ከዕለት ዜና ሆኖ ለጆሯችን አዲስ ባይሆንም ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከያዝነው ኅዳር ወር ድረስ ግን ከሞታቸው በላይ አሟሟታቸው የከፋ ሆኖ በምሥራቅ አርሲ እንዲሁም በምዕራብ ሐረርጌ የሚኖሩ ወገኖቻችን ውድ ሕይወታቸውን በግፈኞች ሲነጠቁ መመልከታችን «ከእንግዲህ ደም ማፍሰስ ይብቃ፣ ሕፃናት ያለ ወላጅ አይደጉ፣ አረጋውያን እና ወጣቶች በግፍ አይገደሉ፣ ሰዎች ተወልደው ባደጉበት ገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ታይተው በፍርሐት አይኑሩ፣ የግፈኞች በትር ሰዎችን እያፈናቀ ከቀዬአቸው እንዲሰደዱ ማድረጉ ይቁም» ብለን እንድንነሳ አድርጎናል። ይ ፍጹም ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ደም ማፍሰስ ከፍጹም ጥላቻ የመጣ መሆኑን ስንረዳ አደጋው የደረሰባቸው የቅርብ ሰዎች ለብቻቸው የሚወጡት እንዳልሆነ እንገነዘባለን።

 

ለብዙ ዓመታት የሰው ልጆች ሕይወት ፍጹም ከአቅም በላይ ባልሆነና የመንግሥት አካላት ሊከላከለው በሚቻል በሰው ሠራሽ አደጋ የእሳት፣ የጥይት እና የሰይፍ ሰለባ ሆነው በተደጋጋሚ የንጹኃን ደም እየፈሰሰ መሆኑን ብናስተውልም አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት እንደነበረው ዓይነት የደም መፍሰስና ግድያ የምትናጠው አርሲ እንዲሁም በቅርቡ በሐረርጌ የብዙ ኦርቶዶክሳውያን ሕይወት እየተቀጠፋበት ይገኛል። የአምናውን አደጋ ዘንድሮ፣ የትናንቱን አደጋ ዛሬ፣ እንዲሁም የዛሬውን አደጋ ነገ እንዳይደገም አድርጎ ማስቆም እየተቻለ፥ ዛሬም ተመሳሳይ በሆነ ዕልቂት ሕዝባችን በተለይም ኦርቶዶክሱ ማለቁን ስንመለከት ለምን? እንዴት? ብሎ መጠየቁ የሁሉም ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።

 

እንዲህ ያለው ዓይን ያወጣ እኩይ ምግባርና ልሸሽግህ ቢሉት የማይሸሸግ አስፈሪም አሳፋሪም የሆነው ድርጊት በንጹኃን ዜጎች ላይ በተለይም በኦርቶዶክሳውያኑ ዘንድ እየተፈጸመ መሆኑን የሰማ እና የተመለከተ ሁሉ በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች ላይ ዜናውን ዘግቦታል፤ የድረሱልን ጥሪም አሰምቷል። የግድያውን ክብደት የተመለከቱና የተረዱ ሞታቸውን እንጂ አሟሟታቸውን ለመግለጽ እጅግ እንደተቸገሩ ከሁኔታቸው መረዳት ችለናል። ወሬውን ማውራት እንዲህ ከባድ ሆኖ አሟሟታቸውን ለመግለጥ ካስፈራ እነዚያ የዚህ ግድያ ሰለባ የሆኑት ከዕልፈታቸው በፊት ያሳለፉትን መሪር ሥቃይ ለመገንዘብ የተለየ ጥበብና ዕውቀት አያስፈልገውም።

 

            የሟቾችን ሕይወት በለቅሶ እና በጩኽት ባንመለሰውም ሰዎች ነንና ድርጊቱን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መኮነን፣ መቃወም፣ ማጋለጥ እና ማውገዝ ብሎም በመላው ዓለም ለሚከኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት፣ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ በሙሉ ልናሳውቅ ይገባናል። የሰው ልጅ በዘሩ፣ በቀለሙ፣ በቋንቋው እና በሃይማኖቱ ምክንያት ሊወቀስ፣ ሊጉላላ፣ ሊደበደብ፣ ሊታሰር እና ሊገደል አይገባውም። በተለያዩ ጊዜያት በምድራችን ላይ እየሆነ ያለው ዕልቂት መነሻውም መድረሻውም የዘር፣ የቋንቋ፣ የቀለም እና የሃይማኖት መሆኑን ተረድተናል። ሰው ወዶ እና ፈቅዶ፣ ፈልጎ እና መርጦ፣ ጠይቆ እና አስፈቅዶ ያላገኘውን ማንነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት «አንተ ከእኛ ወገን አይደለህምና ሞት ይገባኻል» በሚል ትርጉም የለሽ ምክንያት ከቀዬው እንዲፈናቀል፣ ለስደት እንዲዳረግ፣ በፍርሐት እንዲኖር እና በግድያ ምድሪቱን እንዲሰናበት ማድረግ ከሁሉ የከፋ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።

 

 

ኦርቶዶክሳውያን እናቶችና አባቶች፣ ወንድሞች እና እኅቶች እንዲሁም ሕፃናት ጭምር በሃይማኖታቸው ምክንያት ክቡር ሰውነታቸውንና ነፍሳቸውን ሲነጠቁ በማየታችን ዛሬ በዚህ መልኩ ለወገኖቻችን ድምፅ ልንሆናቸው ይኽንን መልእክት ለመጻፍ ተገድደናል። ይኽንን ድርጊት ማንኛውም በጎ ሕሊና ያለው ሁሉ በሰብዓዊነት ብቻ ሊቃወመው፣ ሊኮንነው እና ሊያወግዘው የሚገባ ጉዳይ ነውና ዓለም ይኽንን አይቶና ሰምቶ ዝም ይል ዘንድ ባለመውደዱ «ደም መፍሰስ ይብቃ» በማለት መልእክቱን ከዳር እስከ ዳር አስተጋብቷል።

 

ኦርቶዶክሳውያን ለምን ይሳደዳሉ?

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ያለ ስሟ መጥፎ ስም ያለ ግብሯም መጥፎ ግብር ተሰጥቷት በእኩልነት የማታምንና ለሌሎች ሃይማኖቶች ፀር እንደሆነች በሐሰት ትርክት ከመፈረጅዋ ባሻገር «ፖለቲካ አራማጆች ፓለቲካቸውን የሚያራምዱት በውስጥዋ ተደብቀው ነው» በሚል የፈጠራ ወሬ ያላትን ሉዓላዊነት ለመናድ ለዘመናት ውድቀቷን እንጂ ዕድገቷን የማይፈልጉ የውስጥ እና የውጪ ኃይሎች ተደራጅተው መንግሥት በተቀያየረ ወቅት አጋጣሚውን በመጠቀም ግባቸውን ለመምታት በመሯሯጣቸው ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፊት መሪ መሆኗ ተዘንግቶ ኋላ ቀር እንደሆነችና የዕድገት ጎታች ሆና ለአገር ብልጽግና ዕንቅፋት እንደሆነች ተደርጎ በየሚያው ይወራ የነበረው ከንቱ ወሬ ዛሬ ነፍስ ዘርቶ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክብሯን አሳጥቶ፣ ቁጥሯን አመንምኖ፣ ልጆቿን አስፈራርቶ፣ ተቋሟን አዳክሞ እና ማንነቷ ጎልቶ የሚታይበትን እምነቷን በመሸርሸር ቢሆን እንድትጠፋ ባይሆን እንዳታንሰራራ የማድረግ ዘመቻው አመቺ ጊዜ ላይ በመውደቁ ምክንያት ነው።

 

በመሆኑም እምነቷን በሚገባው መልኩ እንዳታራምድና ሃይማኖቷን ጠብቃ ልጆቿን እንዳታስተምር ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት ይስተዋላል። ስለዚህም ይኽንን መልዕክት በጋራ ጥምረት የምናስተላልፈው ማኅበራት «ይኽ ግድያና መከራ ሊቆም ይገባዋል፤ ለወገን መጮህ እና ለሃይማኖታችን መጸለይ ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባ ነውና ካለንበት ሆነን ይበቃል፤ አትግደሉን፤ አትፈታተኑን፤ መከራ አታብዙብን፤ ደማችንን በከንቱ አታፍስሱብን እንዲሁም በዚህ ግድያ እና ሰቆቃ ላይ እየተባበሩ ያሉ እና ተባባሪ የመንግሥት አካላት ሃገር ሰላም ስትሆን ከፍርድ እንደማያመልጡ ከወዲሁ ለማሳሰብ እንወዳለን።» የሚል ጥብቅ አቋም አለን።  

 

በመጨረሻም የንጹኃን ደም ሲፈስ ግድ ለሚላቸው እና የኦርቶዶክሳውያንን ግድያና ስቃይ ለማስቆም እንዲሁም ጥፋተኞች ለሕግ ለማቅረብ፦

 

፩ኛ)     ቅዱስ ሲኖዶስ እና የቤተ ክርስቲያን አባቶች

፪ኛ)     የፌደራል እና የክልሉ መንግሥታት

፫ኛ)     መላው ምእመናን ኅብረት

፬ኛ)     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወዳጆች

፭ኛ)     የሌሎች እምነት ተቋማት መሪዎችና አማኞች

፮ኛ)     የሰብአዊ መብት ተቋማትና ተሟጋቾቾ

፯ኛ)     ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት

፰ኛ)    የሚዲያ ተቋማትና የማኅበረሰብ አንቂዎች 

የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥያቄአችንን እናቀርባለን።

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን

 

 

 

ü    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ ካሪቢያን እና ላቲን

አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት፣

ü    በኢ/ኦ/ተ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል፣

ü    በኢ/ኦ/ተ/ቤ የማኅበረ በዓለ ወልድ በሰሜን አሜሪካ

ü    ዋልድባን እንታደግ ሰሜን አሜሪካ

 ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ 

 


የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment