Saturday, November 29, 2025

አውሮጳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ «ይፈፀማል» ያሉትን ግድያ በሠልፍ አወገዙ

ኢትዮጵያውያን በአውሮጳ
ጀርመን እና በአጎራባች የአውሮጳ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ  ውስጥ በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ክርስቲያኖች ላይ ይፈፀማል ያሉትን ግድያ፣ ግፍና ማፈናቀል ዛሬ በርሊን-ጀርመን ውስጥ ባደረጉት የአደባባይ ሠልፍ አወገዙ። ሰልፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት አስተባባሪነት የተጠራ ሲሆን በተለያዩ የጀርመን ከተሞች፤ እንዲሁም በጀርመን አጎራባች የአውሮጳ ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያ ተሳትፈዋል።

ሰልፈኞቹ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አካባባቢዎች «በተደጋጋሚና ሆን ተብሎ» የሚፈፀመውን ግድያና ግፍ እስካሁን ማስቆም አልቻለም። «ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚፈጸመው በቃላት ተገልጾ የሚያልቅ አይደለም» ያሉት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ከተሰላፊዎቹ አንዱ የሆኑት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሥራችና የኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ ሊቀካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ፤ «ሰዎች በቋንቋቸው፤ እንደዚሁም በሃይማኖታቸው ተለይተው እየታረዱ፣ እየተጨረሰ ይህን ያህል ግፍ ሲፈጸምባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬ ይህን ሰቆቃ ሊያስቆም አልቻለም» በማለት ዛሬ ድምጻቸውን በዓለም ሸንጎ ለማሰማት መውጣታቸውን ገልጸዋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያውያን ካህናትና ምዕመናን ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች ሃገራት ዜጎችም አብረዋቸው ድምጻቸውን እያሰሙ እንደሆነም አመልክተዋል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ፤ ጅማ፤ ወለጋ፣ ሻሸመኔ፣ እንዲሁም በሐረር ክርስቲያኖች መገደላቸውን የገለጹት ሊቀካህናት ዶክተር መርዓዊ፤ ባጠቃላይ «በሀገሪቱ ግፍ እየተፈጸመ ነው» በማለት በጀርመንዋ ዋና ከተማ በርሊን ለሰልፍ ያስወጣቸውን ምክንያት ዘርዝረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለው «ዓለም ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው» ያሉት የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊ ልሳነ ወርቅ ውቤ በበኩላቸው ከሚገደሉት ሌላ «የታፈኑ፤የታገቱ፤ የተፈናቀሉ እና ሀብት ንብረታቸው የተወሰደባቸው፤ እንደው ጨረቃ ላይ የቀሩ፤ በረሃብ እያለቁ ያሉ፤ አካለ ስንኩላን የሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው » በማለት እነዚህ ወገኖች የሚደርስላቸው አጥተዋል ነው ያሉት። በዋና ከተማ በርሊን ሰልፉ የተካሄደው የኢትዮ ጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር ጉባኤ እየተከናወነ ባለበት ዕለት ነው።


የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment