Wednesday, November 5, 2025

"እናቴን አምጡ" የሕፃኑ ታምራት አውግቸው ተማፅኖ።

እናትና  አባት  ከተጋቡ  ወደ  አስር  ዓመት   ገደማ  እንዳስቆጠሩ   የቅርቦቻቸው  ይናገራሉ።  
እነሆ በረከት ከሕፃን ታምራት!


ኑሯቸው  በምሥራቅ አርሲ  ዞን  በጉና  ወረዳ ኖኖ  ጃዌ  ቀበሌ  ነውና  እንደ  ሀገር  እና አካበቢ ማኅበረሰብ  ሁሉ  የዕለት  ጉርስ  የዓመት  ቀለብ  የሚያገኙት  ደረቁን  መሬት  አለስልሰው  ፣  ከብቶች  አርብተው  ባገኙት  ጥሪት  ነው። የሕጻን ታምራት  አውጋቸው  ወላጆች።

የዚህ  ብላቴና  ቤተሰቦች  በክርስትና  ሕይወታቸውም  ቢሆን ቤተክርስቲያንን  ሳይሱሙና  የፈጠራቸውን  ሳይማልዱ  ውለው  አያድሩም።  እንደ  ቅድስት  ቤተክርስቲያን  አስተምህሮ  መጾም  ፣ መጸለይና ማስቀደስ ግዴታ  መሆኑን በተግባር  መፈፀማቸውንም  መረጃውን  ከነገሩን  ከቅርቦቻቸው  ሰምተናል።

የታምራት  ቤተሰቦች  በቀያቸው  በነበሩበት  ወቅት  በትዳር  አንድ  ወንድና  አንድ  ሴት  ልጅ  አፍርተዋል ።

አበው  እንደሚሉት  የቀንም  ጎዶሎ  አለና  በምሥራቅ አርሲ  ዞን  በጉና  ወረዳ  ኖኖ  ጃዌ  ቀበሌ   በሚገኘው  የመኖሪያ   ቀያቸው  ሐሙስ  ጥቅምት   13 ቀን  2018  ዓ.ም  ለ14  አጥቢያ  ሀገር  ሰላም  ቀየው  አማን  ብለው  በተኙበት  ሰዓትን  ቆጥሮ  ለመግደል  የሚፋጠን  እግርና  እጅ  ከለሊቱ   6:00  ላይ  ወደ  ኦርቶዶክሳዉያኑ  ቤት አመራ።

ሞት  በራቸውን  ያንኳኳው  የታምራት  አውግቸው  ቤተሰቦችና  ጎረቤቶቻቸው  በድቅድቅ   ሌሊት  እየተገፈተሩ  ከቤታቸው  በማስወጣት  ከደጃፋቸው  በሚገኘው  ሜዳ  ላይ  ደርድረው  አንበረከኳቸው። 

በወቅቱ  ብላቴናው  ከእናቱ  ጀርባ   ላይ  እንደነበር  ያዩ  ምስክሮች  ነግረውናል።

ታዲያ የታምራት  እናት  እና  አስራ  ሦስት  ኦርቶዶክሳውያን  በታጣቂዎች  በዘነበባቸው  ተኩስ  ሕይወታቸውን  ማትረፍ  ሳይችሉ  እስከ  ወዲያኛው  ላይመለሱ  አሸለቡ። 

በሰዓቱ  ሕፃን  ታምራት  ከመሬት  ወድቃ  የእናትነት  ትንፋሿ  ሲርቀው  እናቱ  ከወደቀችበት  እንድትነሳ  ይማፀናት  ጀመር።

ይህንን  የሰሙ  እነዛ  የታጠቁ  ኃይሎች  ልጅነቱ  ሳያሳሳቸው  ወገኖቹ  የቀመሱትን  ጥይት  እነሆ  ሲሉ  ተኮሱበት።

ሕፃን  ታምራት  አውግቸውም በደረሰበት  ጉዳት  መቋቋም  አቅቶት  ከእናትና ከብዙ  ኦርቶዶክሳውያን አስክሬን አጠገብ  ወደቀ።

በሰዓቱ  የሚደርስላቸው  ባለመኖሩ  የብላቴናው እግር ላይ  ያሉት  የደም  ስሮች  ተፈጥሯዊ  የደም  መዘዋወራቸውን  ለማከናወን   ተሳናቸው።

አይነጋ  የለምና  በአስክሬን  መሀል  ራሳቸውን  ከአገኙት  መካከል  አንዲት  የ8  ዓመት  ታዳጊ  የሰው  ያለህ እያለች  ትጣራ  ጀመር።

አካባቢ ከማታ  ይልቅ በጥቂቱም ቀን  የተሻለ  ነውና ሕፃናቱን  ወደ  ሕክምና፣ ቤተሰቦቻቸውን  ደግሞ  አፈር  ለማቅመስ  በአካባቢው  ወደ  ሚገኘው  አጥቢያ  አመሩ።

በሕፃናቱ  ላይ  በደረሰው  ከባድ  ጉዳት   አዳማ ለሕክምና  ቢመጡም  የታዳጊ  ታምራት  ጉዳት  እጅጉን  በማየሉ   ወላይታ  ሶዶ  ክርስቲያን  ሆስፒታል  ሊመጣ  ችሏል።

ሕፃን  ታምራት  ከእግሩ  ባሻገር  ሌሎች  የሰውነቱ  አካላት  ላይ  ጉዳት  ስለደረሰበት  የሕክምና  እርዳታ ሊደረግለት  ችሏል።

ይሁን  እንጂ የደረሰበት ጉዳት  ከባድ  በመሆኑ በሆስፒታሉ  የሕክምና  ባለ ሙያዎች ትእዛዝ  መሰረት  ጥቅምት  26  ቀን  2018 ዓ.ም  ከቀኑ  4:00  አንድ  እግሩ  ሊቆረጥ  ችሏል።

ይህ  ብላቴና  ከእግሩ   መቆረጥ  በተጨማሪ   በቤተሰቡ  ናፍቆት  እየተሰቃየ  ይገኛል  ሲሉ  አስታማሚዎቹ  ይናገራሉ።

የሕመም  ስቃዩን  የአልቻለው  ይህ  ታዳጊ  በአሁኑ  ወቅትም  "እናቴን  አምጡ  እያለ"  ክፉኛ  እንደሚያለቅስና ከፍተኛ  ስነ  ልቡናዊ   ጫና  ውስጥ  እንደሚገኝ     አስረድተዋል።

የሕፃን  ታምራት ቤተሰቦች  እና  ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን   ቤተክርስቲያንን  ብለው  በአካባቢው   ባለመራቃቸው  ይህ  አይነት  አሰቃቂ  ጥቃት  ደርሶባቸዋል  የሚሉት  አስታማሚዎቹ   ከጥቃቱ  የተረፉትን  ሕፃናት ልጆችን  የመንከባከብ  እና  የማሳደግ  ኃላፊነት የሁሉም  ኦርቶዶክሳውያን  ነው  ይላሉ።

በተለይም  ለብላቴናው  ሰው  ሰራሽ  እግር  ፣  ወደ  ጤናው  ሲመለስ  ትምህርትና  መሰል  እገዛዎችን  ከቤተክርስቲያንና  ከምእመናን  እንጠብቃለን  ሲሉ  ጥሪያቸውን  አቅርበዋል።

በተመሳሳይ  የጥቃቱ  ሰለባ  የሆነችው  የ8  ዓመቷ  ታዳጊ  የእነ  ታምራት  የቅርብ  ጎረቤት  ስትሆን  በአሁኑ  ወቅት  በአዳማ  ሕክምና   እየተከታተለች  ትገኛለች።

በአርሲ  ሀገረ  ስብከት  በርካታ  ኦርቶዶክሳዉያን  በጭንቅ  ውስጥ  የሚገኙ  በመሆናቸው  ላሉት  ልንደርስላቸው  ለተጎዱት  ድጋፍ  ልናደርግላቸው  ይገባል  መልእክታቸው  ነው።

የታምራት አባት ከዚያች ምሽት በኋላ  የት እንደሚገኙ ማወቅ እንደማይቻል እና እህቱ ደግሞ ቤተሰብ ጋር መሆኗን ሰምተናል።


የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment