ረቡእ፣ ሕዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ሰላማዊ በሆኑ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ እና ለሞት፣ ለአካል
ጉዳትና ለእገታ የዳረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ማረጋገጡን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የክልሉም ሆነ የፌደራል የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቋል።
| አርሲ የደም ምድር! |
ጉዳትና ለእገታ የዳረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ማረጋገጡን ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የክልሉም ሆነ የፌደራል የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቋል።
በምስራቅ አርሲ የተፈጸሙ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን መመርመሩን ያስታወሰው ኢሰመጉ፤ “በእነዚህ አካባቢዎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በቂ ትኩረት እንዲሰጣቸው እና ድርጊት ፈጻሚዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መግለጫ ማውጣታችንና ጥሪ ማቅረባችን የሚታወስ ነው” ብሏል።
በዚህም ኢሰመጉ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በጉና መርቲ ሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ጥቅምት 14 ለ 15 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲሁም በ 18 ለ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ብዛት ያላቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፣ የእስልምና እምነት እንዲሁም የተለያዩ የሌሎች እምነት ተከታዮች በታጠቁ አካላት የተገደሉ መሆኑን እና የተወሰኑትም ታግተው የተወሰዱ መሆኑን ገልጿል።
በተመሳሳይ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ጎዶ በሚባል አካባቢ የጤፍ አጨዳ ላይ ቆይተው ምሳ ለመብላት በተቀመጡበት አምስት አርሶ አደሮች በታጠቁ አካላት የተገደሉ መሆኑን ኢሰመጉ ባደረኩት ምርመራ ተረድቻለሁ ብሏል።
ይሁን እንጂ የክልሉም ሆነ የፌደራል የመንግሥት አካላት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ኃላፊነታቸውን በበቂ ሁኔታ ባለመወጣታቸው የመብት ጥሰቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን ኢሰመጉ በመግለጫው አመላክቷል።
በመሆኑም የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በቂ ትኩረት በመስጠት የሕዝቡ ሰላም ተጠብቆለት የመኖር መብቱን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ጥሪውን አቅርቧል።
የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት የማስከበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ በተለይም ጥቃቶች በተደጋጋሚ በሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች በቂ የጸጥታ ጥበቃ እንዲያደርጉ፣ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የፌደራልና የኦሮምያ ክልል መንግስታት የጸጥታ አካላት ጥቃቶች ሳይደርሱ ቅድመ የመከላከል ስራን በመስራት፣ ተፈጽመው ሲገኙም አፋጣኝ ምላሽና ትኩረት በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ አሳስቧል።
በምስራቅ አርሲ ዞን በተፈጸሙት ግድያዎች እና አፈናዎች ላይ በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኩል የተጀመረው የምርመራ ሂደት መኖሩን ኢሰመጉ የሚገነዘበው ቢሆንም፣ ሂደቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ደረጃዎችን ያሟላ፣ ሙሉ በሙሉ
ገለልተኛ፣ ግልጽ እና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን መንግስት እንዲያረጋግጥና፤ የምርመራው ግኝትም ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ የጥፋት ፈጻሚዎችና ትዕዛዝ ሰጪዎች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግም አሳስቧል።
የምስራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ የጸጥታ አካላት በተለያዩ ቀበሌዎች እየተፈጸሙ ያሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲቆሙ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት እና በመከታተል ጥፋት አድራጊዎችን ለሕግ በማቅረብ ተጠያቂ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንዲወጡም ኢሰመጉ ጠይቋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን የዘይሴ ማሕበረሰብ ያቀረበውን የልዩ የወረዳነት አስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄ ጋር ተያይዞ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በተቀሰቀሰ ግጭት ንጹኃን ዜጎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እና በርካቶች ለእስር መዳረጋቸውንም ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰበው መረጃ ለመረዳት መቻሉን ገልጿል።
ስለሆነም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በክልሉ የሚነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች የሀገሪቱን ሕግ በተከተለ እና ማሕበረሰቡን አሳታፊ በሆነ በሰላማዊ መንገድ በወቅቱ የሚፈታበትን ሁኔታ እንዲያመቻችና በሂደቱ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እንዲከላከል ኢሰመጉ በጥብቅ ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
መረጃው፤ ከአዲስ ማለዳ የተገኘ ነው
No comments:
Post a Comment