Saturday, November 1, 2025

ከጥምረት ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

ከጥምረት ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ
“ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል።” ሮሜ ፰ ÷ ፴፮

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታቀደና በተጠና መልኩ ከሃገር ለማጥፋት ካልሆነም አናሳ ሆና እንድትቀጥል

ሥርዓታዊ ጥቃት እየደረሰባት ትገኛለች። በተለይም ከ ፳፻፲ ዓ.ም. ጀምሮ ከሰሜን አስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በአራቱም መዓዘን ካህናቱ ምእመናኑ ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ አብያተ ክርስቲያናት ይቃጠላሉ። “ኦርቶዶክስን ከኦሮሚያ ማጽዳት” የሚለው የቆየ የመንግሥት እቅድ የመተግበር አካል ነው።
ሰሞኑን ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሥር ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች “ማንነታቸው ያልታወቁ” በሚባሉ ነገር ግን አገዛዙ እና ሌሎች አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ኃይላት በሚያሰማሯቸው ታጣቂዎች ሃያ አምስት ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች መገደላቸውን እና ከሞት የተረፉትም ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወቃል።
በእነዚህ ጥቃቶች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ወንድማማቾች እና እህታማቾች እንዲሁም ከሁለት ዓመት ሕፃን እስከ ሰባ ስድስት ዓመት አረጋዊ ሽማግሌ የግፍ ግድያው ሰለባ መሆናቸው ታውቋል። በያዝነው ዓመት መስከረም ፯፣ ጥቅምት ፲፬፣ እና ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በጉናና መርቲ ወረዳዎች፤ በሸርካ ወረዳ፤ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች ከሃያ አምስት በላይ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ተገድለዋል። በዚሁ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ፻፲፭ (አንድ መቶ አራ አምስት) ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከአሥራ ስድስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል።

እንደሚታወቀው አሁን ያለው አገዛዝ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ እና አብያተ ክርስቲያናትን ማውደም በአገዛዙ የሚመራና ሌሎች አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚሳተፉበት የእለት ከእለት ተግባር ሆኗል። በመሆኑም ብዙ ካህናት እና ምእመናን በተለያዩ ቦታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል፤ የብዙ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሀብትና ንብረታቸው ወድሟል፤ ብዙዎቹ ከቤትና ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ከግድያ የተረፉት ብዙዎቹ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችም ለከባድ የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት ተዳርገው ሕይወታቸውን በመከራ እየገፉ ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች የክርስቲያኖችን ሞትና መከራ መስማት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በዚህም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችን መጨፍጨፉና ማጽዳቱ ያለ ምንም ከልካይና ተጠያቂነት ላለፉት ስምንት የመከራ ዓመታት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን በየትኛውም አካባቢ የሚገደሉበት እና ሞታቸውም ከምንም የማይቆጠርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይኼ ሁሉ እየሆነ ያለው ከሀገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በሆኑበት በሀገረ ኢትዮጵያ መሆኑ አሳዛኝ ነው። በቀደመው ጊዜ የክርስቲያን ሃገራት የነበሩ የሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በሂደት በተደረገ የማጽዳት ጥቃት ክርስቲያኖች የጠፋበት አካባቢ ነው።
ይሁን እንጅ የቤተ ክርስቲያናችን ላዕላይ መዋቅር ከሲኖዶስ እስከ ሀገረ ስብከት ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር መንጋውን ለመጠበቅ የተዘጋጀ ባለመሆኑና ለዚህ መራራ ተጋድሎ የተሾሙ ባለመሆናቸው ዛሬ ላለንበት መከራ መውጫ መንገዱን ሩቅ አድርጎታል። ሲኖዶስ ለዓመታት በመዋቅር የሚደረገውን የኦርቶዶክሳውያን ግድያ ለማስቆም ከመጣር ይልቅ በዝምታ ከገዳይ ጋር በመተባበር በሚመስል መልኩ “ከመንግሥት ጋር ተግባብቶ መሥራት” ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ሳዊሮስ በአዲስ ዓመት በመግለጫ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ እንኳ አንድም ሀገረ ስብከት እንደ ችግር ቆጥሮ በሪፖርት ያቀረበ የለም። ሲኖዶሱም በዚህ ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ውይይት አላደረገም። አሁንም በብዙዎች ግፊት ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ ቢያወጣም ችግሩን በአግባብ ያልገለጸ መፍትሔ የማይሰጥ ለተጎጂዎችም ዳግም ጥቃትን የማይከላከል፤ ካሉበትም መከራ የሚያግዝ አይደለም።
በሀገር ደረጃ ብዙኃን የሆነ ማኅበረሰብ በዚህ ልክ መጠቃት አልነበረበትም። ሀገሪቱ በጸረ ኦርቶዶክሳውያን እጅ ወድቃለች። ሲኖዶሱም ይኽ ሁሉ ግፍና መከራ በኦርቶዶክሳውያኑ ላይ እየተፈፀመ በዝምታ በማለፍ ተባባሪ ሆኖ ቀጥሏል። ኖላዊ ተብለው የተሾሙት የቤተ ክርስቲያኗ መሪዎች የራሳቸው ጥቅምና ምቾት እንዳይጓደል ከመጨነቅ ውጭ የካህናት እና ምእመናን ግድያው፣ መፈናቀሉ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መውደም እና አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ ለመለወጥ የሚያደርጉት አውዳሚ አካሄድ የሚገዳቸው አልሆኑም። አገዛዝ በተቀያየረ ቁጥር ከአገዛዝ ጋር እየተለጠፉ የግል ጥቅማቸውን የሚያጋብሱ እንዲሁም ቀኖና እና ሥርዓት እየሻሩ አገዛዙ የሚላቸውን የሚፈጽሙ አካላት ቤተ ክርስቲያኗን ወረዋታል። በፍቅረ ንዋይ እና ምንደኝነት የተሾሙበትን ኃላፊነት ዘንግተው ለግል ጥቅምና ድሎት መጨነቅ የብዙዎቹ መገለጫ ሆኗል።
አሁን ያሉት ብዙዎቹ አባቶች በአገዛዙ ዘንድ ተንቀው ቤተ ክርስቲያኗንም ያስናቋት ሆነዋል። ስለዚህ ይኽን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቀየር እና የተንሰራፋውን ችግር ለመቅረፍ ጉዳዩ የሚያሳስበን ካህናት እና ምእመናን በአጥቢአይችን በየማኅበራቱ በሰንበት ትምህርት ቤት ውይይት በማድረግ መፍትሔ መንገድ መወያየት ይገባል።
ጥምረት ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊ ንቅናቄ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን። በሕይወት የመኖር መብት የሰው ልጅ አንዱ መሠረታዊ መብት ነው። ኦሮቶዶክሳውያን በህብረት መቆምና መጋደል እስካልቻልን ድረስ በልመና የሚቆም ግድያም ሆነ ድረስልን ብለነው የሚደርስ አካል የለም። ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በያለንበት እየተደራጀን እልቂቱን ማስቆም ይኖርብናል። እግዚአብሔር አምላክ ለሞቱት ወገኖቻችን እረፍተ ነፍስን እንዲያድላቸው እና ያዘኑትን ሁሉም እንድያጽናናቸው እንለምናለን።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥፋት
ሕዝባችንን ከስደት፣ ከእንግልት ያድንልን !!!
ጥምረት ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኦርቶዶክሳዊ ንቅናቄ
ጥቅምት ፳፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.


ጥምረት ኦሮዶክሳዊ ንቅናቄ ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
ዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment