Sunday, December 15, 2013

በጋሻው ደሳለኝ በይቅርታ ሚዛን ተመዘነ÷ ቀልሎም ተገኘ – ምእመኑን አስቆጣ አባቶችን አሳዘነ! የ‹ፀጉራሙ በግ› ታሪክ በሐዋሳ ተደገመ

welcoming banner

በጋሻው ደሳለኝ በይቅርታ ሚዛን ተመዘነ÷ ቀልሎም ተገኘ – ምእመኑን አስቆጣ አባቶችን አሳዘነ! የ‹ፀጉራሙ በግ› ታሪክ በሐዋሳ ተደገመ

 • ‹‹በነበረው ሒደት በተለያየ ምክንያት ለበደላችኹን ኹሉ ይቅርታ አድርገንላችኋል፤ እናንተም ይቅርታ አድርጉ፤›› (በጋሻው ደሳለኝ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.፤ ለሐዋሳ ደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን የተናገረው)
 • ‹‹ይኼ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ በፍጹም እንዳያደርገው፡፡ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ጥፋተኛ ነኝ፤ ተሸማቅቄ እኖራለኹኝ ማለት ነው፤››   (በጋሻው ደሳለኝ፣ ግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የክብረ መንግሥት ግብረ አበሮቹን ሲመክር)
 • የሐዋሳው የዕርቀ ሰላም መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ በጋሻው ደሳለኝ የበደላትን ቤተ ክርስቲያንና ያሳዘነውን ምእመን ይቅርታ እንደሚጠይቅ በቤተ መቅደስ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል አረጋግጦላቸው ነበር፤ ብፁዕነታቸውም ሦስት ጊዜ ‹‹አጥፍቻለኹ÷ይቅርታ›› አሰኝተውት ነበር፡፡
 • ይቅርታ ጠያቂ ሳይኾን ይቅርታ አድራጊ እና ይቅር ባይ መስሎ በቀረበው የበጋሻው ደሳለኝ የእብሪት አነጋገር ያዘኑት አቡነ ገብርኤል እና አቡነ ሉቃስ ምእመኑን ይቅርታ ጠይቀዋል፤ በጋሻው ከእንግዲህ በአህጉረ ስብከታቸው ስፍራ እንደማይኖረው በቁርጥ የተናገሩት አቡነ ገብርኤል፣ ‹‹እርሱ መቼም የሚስተካከልና የሚመለስ ሰው አይደለም›› ሲሉምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹አለመማር የሚያመጣው በሽታ ነው፤ ያሳዝናል›› ብለዋል፡፡
 • የሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት በተፈጸመበት ዕለት በደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በተካሄደው የምሽት ጉባኤ ላይ ከአሜሪካ ተጉዛ የደረሰችውና በበጋሻው አነጋገር ማዘኗ የተነገረው ዘማሪት ወ/ሮ ፋንቱ ወልዴ ግለሰቡን ክፉኛ መገሠጽዋ ተሰምቷል – ‹‹ከአሜሪካ ድረስ ገንዘቤን አውጥቼ የመጣኹትና ያን ኹሉ የደከምነው ይቅርታ እንድትጠይቅ እንጂ እንድታበላሸው አልነበረም፡፡››
Hawassa St. Gabriel Church
የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም
 • በ(ተ)ነሳሒነት የማያምነው በጋሻው ደሳለኝ፣ በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ስምምነት አጋጣሚ ቀልሎ የተገኘበት ሚዛንያለቀኖናዊ ምርመራ በዕርቅ ሰበብ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ የተሯሯጡለት እነወ/ሮ ፋንቱ ወልዴም አካሄዳቸውን እንዲያጤኑት አስገዳጅ ኹኔታ የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
 • የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ምእመናን የዕርቀ ሰላም ሥነ ሥርዐት የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሠየማቸው ልኡካን ተከናውኗል፤ ለዕርቀ ሰላሙ ዕውቅና እንዲሰጥና ለስምምነቱ መከበር ጥንቃቄ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡

ሰበር ዜና – በጋሻው ደሳለኝ በሐዋሳ የአቋራጭ ይቅርታ ሊጠይቅ ነው፤ ‹‹ውጫዊ ጫናውን በጉልሕ የሚያሳይ ነው›› /ምእመናን/

 • በዕርቀ ሰላም ሒደቱና መግለጫው ስለ በጋሻው ደሳለኝ የተጠቀሰ ነገር የለም
 • የምእመናን ተወካዮች በጋሻው ይቅርታ እንዲጠይቅ የተሰጠውን ፈቃድ ተቃውመዋል
 • በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቁን ፈቃድ እንዲያገኝ በፓትርያርኩና በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ ላይ የክልል እና ፌዴራል ግለሰብ ባለሥልጣናት ጫና መደረጉ ተጠቁሟል
Begashaw Dessalegn
በሊቃውንት ጉባኤው ለጥያቄ ተፈልጎ ያልተገኘውና በአቋራጭ ይቅርታ እንዲጠይቅ ‹የተፈቀደለት› በጋሻው ደሳለኝ
የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ዛሬ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. የዕርቀ ሰላም ስምምነት መግለጫ በሚያወጣበት በሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳም በጋሻው ደሳለኝ ‹‹ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ›› ፈቃድ ማግኘቱ ተሰማ፡፡
በጋሻው ደሳለኝ ይቅርታ የመጠየቅ ፈቃድ ማግኘቱ የታወቀው÷ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የዕርቀ ሰላም ልኡኩ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ትላንት፣ ከቀትር በኋላ ወደ ሐዋሳ ደ/ምሕ/ቅ/ገብርኤል ገዳም ምእመናን ተወካዮች ስልክ በመደወል፣ በመግለጫው ላይ በጋሻው ምእመኑን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትና እንደተፈቀደለት፣ የምእመናን ተወካዮቹ በዚህ እንዲስማሙና የማይስማሙ ከኾነ እርሳቸውም እንደማይገኙ ባስታወቁ ጊዜ ነው፡፡
ዋነኛው የዕርቀ ሰላም ንግግር በተደረገበት ኅዳር ፭ እና ፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም በተያዘው ቃለ ጉባኤና በተዘጋጀው መግለጫ ላይ የበጋሻው ስም እንኳ እንዳልተነሣ የሚጠቅሱት የምእመናን ተወካዮች፣ የዕርቀ ሰላም ስምምነቱ የሐዋሳ ችግር ብቻ የተዘረዘረበትና የከተማውን ምእመናን ብቻ የሚመለከት እንደኾነ ለብፁዕ ዋና ጸሐፊው ለማስረዳት ቢሞክሩም ብፁዕነታቸው በአቋማቸው በመጽናታቸው ተቀባይነት እንዳላገኙ ተገልጦአል፡፡
የምእመናን ተወካዮቹ ተቃውሞ፣ ግለሰቡ በዕርቀ ሰላም ስምምነት ውስጥ አለመጠቀሱ ብቻ ሳይኾን የሐዋሳ ከተማ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ነዋሪ ምእመን አለመኾኑና ኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖትንና ክርስቲያናዊ ትውፊትን በመፃረር በተናገራቸውና በጻፋቸው ሕጸጾች የበደለው የሐዋሳን ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያንንና በርካታ ኦርቶዶክሳውያን መኾኑን፣ ስለዚህም ከፍተኛ በደሉ በታኅሣሥ ወር ፳፻፬ ዓ.ም. በተቋቋመው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ጉባኤ ጉዳዩ የተያዘ መኾኑን የሚጠቅስ ጭምር ነው፡፡

የቅ/ሲኖዶስ የሲዳማና ጉጂ ቦረና አህጉረ ስብከት ልኡክ ነገ በሐዋሳ የዕርቀ ሰላም መግለጫ ያወጣል፤ ዕርቀ ሰላሙና መግለጫው የሐዋሳውን ውዝግብ ብቻ እንጂ በሊቃውንት ጉባኤው ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ የታዘዘውን በጋሻው ደሳለኝንና ሌሎች ሕገ ወጦችን አይመለከትም

 • ዕርቀ ሰላሙን በሚያወርደው የሁለቱም ወገኖች ስምምነት መሠረት ከኅዳር ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ከሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ‹‹ወንዲታ›› በተባለው የግለሰብ ስቱዲዮ ውስጥ ሲሰበሰቡ የነበሩ ምእመናን÷ በሰንበት ት/ቤት፣ በስብከተ ወንጌል እና በልማት ኮሚቴዎች ውስጥ የመሳተፍና የማገልገል መብታቸውይጠበቅላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሰንበት ት/ቤቱ አመራርና በስብከተ ወንጌል ኮሚቴ ሁለት፣ ሁለት፤ በልማት ኮሚቴ ውስጥ ደግሞ በሰበካ ሳይወሰኑ እስከ አምስት አባላትን በማሳተፍ የማገልገል መብት ይኖራቸዋል፡፡
 • የ‹‹ወንዲታ›› ተሰብሳቢዎች ጥያቄ ያነሡበት የደብረ ምሕረት ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ደንብ መሠረት የተመረጠ በመኾኑ የሥራ ጊዜውን ሲጨርስ በሚያካሂደው አዲስ ምርጫ ብቻ ይተካል፡፡ በሌሎች የከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ያለ ሰበካቸው በሰበካ ጉባኤያት የተመረጡ ምእመናን ካሉ በአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እርምት እንዲደረግበት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
 • ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ባወጣቸው መመሪያዎች መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጡ ሰባክያንና መምህራን ሕጋዊነት የሚኖራቸው፡- 1) የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ ሲኾኑ፣ 2) የጠቅላይ ቤተ ክህነት ማስረጃ ሲኖራቸው፣ 3) በአህጉረ ስብከት የመምህራን ይላክልን ጥያቄ ሲቀርብ ነው፡፡
 • ስለኾነም ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ለአገልግሎቱ መሳካት ይረዳ ዘንድ ሰባክያንና መምህራነ ወንጌል÷ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ወይም ከአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት ወይም ከአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዕውቅናና ፈቃድ ሊያገኙ ይገባል፡፡
 • በዚህ መሠረት ያለ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ያለሀ/ስብከቱና ያለብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ማዘጋጀት ይኹን ሰባክያንና መምህራንን መጋበዝ እንደማይቻል፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱም ከቡድናዊ ተጽዕኖዎች ነጻ ኾኖ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት ማዕከል አድርጎ መፈጸም እንደሚገባው በሐዋሳው የዕርቀ ሰላም ስምምነት ላይ ተገልጦአል፡፡