Friday, March 2, 2012

የአሰቦት ገዳም ለሁለተኛ ጊዜ ተቃጠለ . . .


·                     ማኅበረ መነኮሳቱ አስቸኳይ ርዳታ ጠይቀዋል
·                     ከብት ዘራፊዎችና ከሰል አክሳዮች የቃጠሎ መንሥኤዎች ናቸው ተብሏል
·                     ‹‹ውኃ የለንም፤ የሚረዳን ሰውም የለንም፤ እሳቱ ወደ ትልቁ ደንና ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እየተቃረበ በመሆኑ ከፍተኛ ርዳታ ያስፈልገናል›› /የገዳሙ መነኮስ/
·                     ገዳሙ በግራኝ ወረራ የመጥፋት፣ በኢጣልያ ወረራ የመዘረፍ አደጋ ገጥሞት ነበር፤ ከ20 ዓመት በፊት ‹‹የኦሮሚያ ነጻነት እስላማዊ ግንባር/ጃራ/›› ገዳሙን ወርሮ በአካባቢው የሚኖሩ 16 ክርስቲያን አባ ወራዎችን አርዶ ነበር
(ደጀ ሰላም፣ የካቲት 21/2004 ዓ.ም፤ ፌብሩዋሪ 29/2012/READ THIS NEWS IN PDF)፦ እንደጥድ፣ ዝግባ፣ ወይራ፣ ግራር፣ ብሳና፣ ቀረሮ በመሳሰሉት አገር በቀል እና ዕድሜ ጠገብ ዛፎች የተሞላውን በአጠቃላይ 13ሺሕ ሄ/ር መሬት ያህል ይሸፍን እንደነበር የሚነገረው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴ እና አቡነ ሳሙኤል ገዳም በአራት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰ ሰደድ እሳት እየጋየ መኾኑ ተሰማ፡፡


ሰደድ እሳቱ ትንት፣ የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከረፋዱ አራት ሰዓት ግድም የተቀሰቀሰው ለከብት ዘረፋ ወደ ገዳሙ ክልል የገቡ የኢሳ ጎሳ አባላትን ለመከላከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ መሆኑን አንድ የገዳሙ መነኮስ ተናግረዋል፡፡
መነኮሱ በስልክ ለዜና ሰዎች እንደተናገሩት በአቅራቢያው ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ጥቂት የገዳሙ መነኮሳት እና የአካባቢው ምእመን ባላቸው አቅም ርብርብ እያደረጉ ቢሆንም በቂ የሰው ኀይል ይኹን ውኃ/እርጥበት የለም፡፡
ከታች ከበርሓው አካባቢ ተቀስቅሶ ከ24 ሰዓት በላይ የቆየው ሰደድ እሳት በአካባቢው ከፍተኛ ሙቀት እና የነፋስ ኀይል እየተባባሰ በአሁኑ ወቅት ወደ ትልቁ ደንና ገዳሙን ባቀኑት ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ስም ወደተሠራው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ዞሮ እየተቃረበ በመሆኑ መንግሥትና በጎ አድራጊ አካላት አስቸኳይ እገዛ እንዲያደርጉላቸው ተማፅነዋል፡፡ ‹‹የአካባቢው ምእመን እንኳ ስለ አደጋው በሚገባ አልሰማም፤ ሁኔታው ከእኛ አቅም በላይ ነው፤ አፋጣኝ እና በአየር የተደገፈ ከፍተኛ ርዳታ ያስፈልገናል፤››ብለዋል መነኮሱ በተማኅፅኗቸው፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሜኤሶን ወረዳ በሚገኘው አሰቦት ገዳም ሰደድ እሳት ሲቀሰቀስ ከ2001 ዓ.ም መጋቢት ወር ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ ከ15 ቀናት በላይ ቆይቶ የነበረው ሰደድ እሳት 11 ሺሕ ሄ/ር መሬት የሚሸፍነውን ደን በከፊል መጉዳቱ ተዘግቧል፤ በቁጥጥር ሥር የዋለውም ከዋናው የገዳሙ ግቢ ለመድረስ 500 ሜትር ያህል ሲቀረው እንደ ነበር ተመልክቷል፡፡ በወቅቱ ከ38 ያላነሱ ከሰል አክሳዮች ለሰደድ እሳቱ መነሣት መንሥኤ ናቸው በሚል ተይዘው በዋስ መለቀቃቸውን የዜናው ምንጮች አስታውሰዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በገዳሙ ላይ በሚደርሱት የእሳት ቃጠሎዎች ከአጠቃላዩ 13 ሺሕ ሄ/ር ደን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የቀረው ከአንድ ሦስተኛ እንደማይበልጥ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡
የአሰቦት ደብረ ወገግ ገዳም በግራኝ ወረራ አስቀድመው ከጠፉት ገዳማት አንዱ ነበር፡፡ ደብረ ወገግ ዳግመኛ የቀናው በ1911 ዓ.ም ነው፤ ያቀኑትም የታወቁት ሊቅ አለቃ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ አለቃ ገብረ መድኅን የጻድቁ አቡነ ሳሙኤልን ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ሠሩ፡፡ በ1918 ዓ.ም ደግሞ የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ጀምረው ፍጻሜውን ሳያዩ ቢያርፉም ሥራው በ1919 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
በ1929 ዓ.ም በሶማልያ በኩል በገባው ፋሽስት የኢጣልያ ጦር ገዳሙ ተዘርፏል፤ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም ፈርሷል፡፡ በወቅቱ በገዳሙ ከነበሩት 500 መነኰሳት መካከል ከፊሎቹ ታቦቱን ይዘው ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲሸሹ የቀሩት ደግሞ ሞቃዲሾ ተወስደው ታስረዋል፡፡ የአቡነ ሳሙኤል ቤተ ክርስቲያን ግን ምንም ጉዳት አልደረሰበትም ነበር፡፡ ከነጻነት በኋላ መነኰሳቱ በ1936 ዓ.ም ተሰብስበው ወደ ገዳሙ መጡ፡፡ ከ22 ዓመት በኋላ ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በዐፄ ኀይለ ሥላሴ አማካይነት በ1952 ዓ.ም ተሠራ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 1984 ዓ.ም ራሱን የኦሮሚያ እስላማዊ ነጻነት ግንባር/ጃራ/ የተባለ አክራሪ ድርጅት ገዳሙን ወርሮ በዙሪያው የሚኖሩ 16 ክርስቲያን አባ ወራዎችን አርዷል፡፡ 
ከአመለል እስከ ንብ ገደል፣ ከአሩሲ እስከ ምድረ አዳል/ምድረ አቢዳራ/ በሚያካልለው ሀገረ ስብከታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት በፈጸሙት በ13ው ምእት ጻድቅና የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር አቡነ ሳሙኤል የቀናው ገዳሙ የቀድሞ ስሙ ያግሙ ይባል ነበር፤ ደብረ ወገግ ያሉት ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ናቸው፤ ትርጓሜውም ደብረ አእምሮ፤ የዕውቀት ደብር ማለት እንደሆነ ገድላቸው ይናገራል፡፡
በምድረ ሐረርጌ፣ በደብረ ሐዘሎ እና በባሌ አካባቢ ሰፊ የስብከተ ወንጌል ሥራ የሠሩት ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ያረፉት በጥንተ ክርስቲያኑ ኦጋዴን ነበር፡፡ ዐፅማቸው በአፋር ምድር ባቀኑት ደብረ ኪሩብ ገዳም ለሰባት ዓመታት የቆየ ሲሆን ወደ አሰቦት ደብረ ወገግ የመጣው ቆይቶ ነው፡፡

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment