Monday, March 19, 2012

በዝቋላ ገዳም በቁጥጥር ሥር ውሏል የተባለው ቃጠሎ ዳግመኛ አገርሽቷል

  • ቃጠሎው የገዳሙን ዙሪያ ገባ እያካለለው ነው
  • የቃጠሎው መንሥኤ “ከሰል አክሳዮች ናቸው” መባሉ አጠራጥሯል
  • “ትንት ምሽቱን ነው ዳግመኛ የተቀሰቀሰው፤ የተጠበቀው የአየር እገዛ አልተደረገልንም፤ እሳቱ ዙሪያውን ይዞታል፤ በእሳቱ እየተከበብን፣ በጭሱ እየታፈንን ቢሆንም ባፈር በቅጠሉ እየታገልን ነው፤ ወደ ጠበሉ ከገባ ግን አለን ለማለት አይቻልም፤ . . . ገብረ መንፈስ ቅዱስ መቶ ዓመት ለጸለዩባት፣ ለደከሙባት ቅድስት ቦታ ምላሹ ይህ ነውን? እንዲያው ወሬ ብቻ ነን!!” /የገዳሙ መነኰስ/
  • ዳሩ እሳት - መሀሉ እሳት!! በምሥራቅ እሳት - በመሀል እሳት - በሰሜን እሳት!! 


(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 9/2004 ዓ.ም፤ ማርች 18/2012 READ THIS ARTICLE IN PDF)፦  በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊበን ዝቋላ ወረዳ አዱላላ ቀበሌ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ በሚገኘውና የመንግሥት ይዞታ በሆነው ደን ምሥራቃዊ ገጽ ትንት ቀትር ላይ ተነሥቶ ማምሻውን በቁጥጥር ሥር መዋሉ የተገለጸው ቃጠሎ ሌሊቱን አገርሽቶ ዙሪያ ገባውን ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ሌሊቱን ዳግመኛ ማገርሸቱ የተነገረው ቃጠሎ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሚገኝበትና ትንት እሳቱ ከተነሣበት አዱላላ ከሚባለው ምሥራቃዊ ቦታ በምዕራብ አቅጣጫ የሴቶች ገዳም ወደሚገኝበት የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንና ወደ መሀል የገዳሙ ክልል እየተዛመተ ነው፡፡
ከስፍራው በደረሰን መረጃ መሠረት÷ በአሁኑ ወቅት የቃጠሎው ጭስ እሳቱን ለማጥፋት የሚካሄደውን ጥረት በእጅጉ አዳጋች አድርጎታል፡፡ በቦታው በርከት ብሎ የሚታየው አስታ የተባለው አጭር ዛፍ፣ የደረቀው ሣርና በበጋው ሙቀት የከቸረው መሬት/ አፈር እሳቱን በከፍተኛ ደረጃ በማቀጣጠል÷ በምሥራቅ አቅጣጫ በከባዱ ከሚነፍሰው ነፋስ ጋራ ተደማምሮ ለእሳቱ በአጭር ጊዜ መዛመት አስተዋፅኦ ማድረጉን የገዳሙ መነኰሳት ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ቃጠሎው ከገዳሙና ከአካባቢው ማኅበረሰብ አቅም በላይ ለመሆኑ ርግጥ ቢሆንም በትንትናው ዕለት በአየር ኀይሉ ሄሊኮፕተር ወይም የእሳት አደጋ መከላከል መኪኖች ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀው እገዛ እንዳልደረሰላቸው አንድ የገዳሙ መነኮስ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ እኚህ አባት እንዳስረዱት ቃጠሎው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ጠበል እየተባለ ወደሚጠራው ጫካ ከደረሰ የገዳሙን ጠቅላላ ህልውና አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡
መነኮሱ አያይዘው የሰጡት ገለጻ ቃጠሎው “በከሰል አክሳዮች ነው የተነሣው” የሚባለውን የሚያስተባብል ነው - “የትንቱ ጠፍቷል ስንል ይኸው ሳይጠፋ አደረና በመድኃኔዓለም፣ በኪዳነ ምሕረት፣ በሴቶች ገዳም በኩል እያስጨነቀን ነው፤ መሬቱ፣ ሣሩ፣ ቅጠሉ በጣም ደረቅ ነው፤ ይነዳል፤ ነፋስ አለ፤ ጭሱም ያፍናል፤ በዕድሜ የገፉ አባቶች ሳይቀሩ በእሳት ተከበውም ቢሆን ባፈር በቅጠሉ ቢታገሉም ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡”
ምንም ዐይነት እገዛ ባለመደረጉ በእጅጉ ያዘኑት ሌላዋ እናትም “ጣድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መቶ ዓመት ለጸለዩባት፣ ለደከሙባት ቅድስት ቦታ ምላሹ ይህ ነውን? እንዲያው ወሬ ብቻ ነን!!” ሲሉ የተሰማቸውን ብሶት ገልጸዋል፡፡
የዜና ዘገባው እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በሀገረ ስብከቱ ደረጃ ይኹን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤትና የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ምን ጥረት እየተደረገ እንዳለ በጎላ በተረዳ የተሰማ ነገር የለም፡፡

የዝቋላ ገዳም ዐፄ ገብረ መስቀል እና ቅዱስ ያሬድ ከነበሩበት አምስተኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ የሚነገር ታሪክ ቢኖረውም በታወቀ መነሻ የቀናው ገድላቸውን በግብጽ ጀምረው በኢትዮጵያ በፈጸሙት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አማካይነት በ1168 ዓ.ም እንደሆነ ይታመናል፡፡ ጻድቁ ሁለት ኪ.ሜ ርዝመት እና 60 ሜትር ጥልቀት ባለው የዝቋላ ሐይቅ ውስጥ የቁልቁሊት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያና ለዓለም ሁሉ ለ100 ዓመታት እንደ ጸለዩ፣ በርእሰ ደብር ዝቋላም ለ262 ዓመታት እንደኖሩ፣ በዚህም ወቅት ልዩ ልዩ የአጋንንትን ፈተና ድል መንሣታቸውንና ከጌታችን ዘንድ ቃል ኪዳን መቀበላቸውን በገድላቸው ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በ15ው መ/ክ/ዘ የነበረው ንጉሥ እንድርያስ (ሕዝበ ናኝ) በርእሰ ደብር ዝቋላና በዙሪያው በመድኃኔዓለም፣ በእመቤታችን፣ በቅዱስ ገብርኤል፣ በቅዱስ ሚካኤል እና በጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም አብያተ ክርስቲያን አሳንጧል፡፡

እኒህ አብያተ ክርስቲያን በግራኝ ወረራ ወቅት ጠፍተው ገዳሙ ጠፍ ሆኖ እስከ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ እና ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ከቆየ በኋላ መተዳደሪያ መሬት (ጉልት)፣ አገልጋዮች ተሰጥተውታል፤ አብያተ ክርስቲያኑም ዳግመኛ ታንፀዋል፡፡

በእሳተ ጎሞራ የተፈጠረ ሐይቅ (Crater Lake) ተግኖ የሚገኝ ጥንታዊው የዝቋላ ገዳም በአምስቱ ዓመት የጠላት ወረራ ዘመን ከየካቲት 12፣ 1928 ዓ.ም ጭፍጨፋ በኋላ (ፋሽስት ኢጣልያ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ እንደፈጸመው ሁሉ) የአርበኞች መደራጃ ማእከል ነው በሚል ከባድ ጥፋት ቢያደርስበትም ፋሽስቱ በአየር ይሰንዝር የነበረውን የቦምብ ድብደባ አንጥሮ የሚመልስ ታላላቅ ገቢረ ተኣምራት እንደተፈጸሙበት ይነገራል፡፡

ከ1989 ዓ.ም አንሥቶ ከርዳታ ጋራ በተያያዘ ወደ አካባቢው በገቡት ሉተራውያን ምክንያት ገዳሙ ከሚደርስበት ሰው ሠራሽ ችግር በተጨማሪ በበጋ የውኃ እጥረት፣ በክረምት ደግሞ ከባድ ቁርና የመንገዱ አስቸጋሪነት ተግዳሮቶቹ ናቸው፡፡

 

እረ ጎበዝ ይሄ ነገር የት እንደሚደርስ እናስበው ትላንት ከትላንት በፊት

  • የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ተቃጠለች ተባለ

  • የጅማ ክርስቲያኖች በግፍ ታረዱ ተባለ

  • የደብረ ሊባኖስ ገዳም የአብነት ት/ቤቶች በፖትሪያሪኩ ትዕዛዝ ተዘጉ ተባለ

  • የአሰቦት ወደብረ ወጋግ ገዳም በ፩ ዓመት ውስጥ ፭ ጊዜ ተቃጠለ ተባለ

  • መንግስት የዋልድባን ገዳም በግፍ ለመውሰድ እየታገለ ነው ተባለ

  • የጎንደር ታሪካዊ የአቋቋም እና የብሉይ እና ሃዲሳት አብነት ት/ቤቶች ተቃጠሉ ሙሉ ለሙሉ ወደሙ ተባለ

  • ክርስቲያኖች በግፍ ታረዱ፣ ተሰደዱ፣ መሬታቸው ተቀማ

  • የእምነታችን መገለጫ የቃልኪዳኑ ታቦት ማደሪው በመንግስት ተወስዶ ለባለሃብቶች ቦታው ተሸጠ . . . ሌላም ሌላም ብዙ አለ

ቀጥሎ ምን እንደሚሆን ገምተን እናውቃለን? ነገ እያንዳንዳችን ያሰርናትን ማኅተብ በጥሱ እንደምንባል አያጠራጥርም፣ በእውነት ለሁሉም መልሱ ወደ እግዚአብሔር ማመልከት በጸሎት መጠየቅ አይነተኛ መንስኤ መሆኑን ማንም ክርስቲያን የሚያውቀው እውነታ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ያብቻ ደግሞ በቂ ይሆናል ብለን አናምንም እያንዳንዳችን መስዋዕትነት መክፈል ካለብን መስዋዕት መሆን ይጠበቅብናል፥ ቅዱሳን የምንላቸው ሐዋርያት እና ሰማዕታት መራራ ሞትን የቀመሱት ልእኛ ይህችን እውነት የሆነችውን ቤተክርስቲያን ለማስረብ እና ለማስተላለፍ መሆኑ ግልጽ ነው በመሆኑም ይህ ትውልድ አደራም ሀላፊነትም አለበት፣ ለተተኪው ትውልድ ሳትበረዝ፣ ሳትከለስ፣ እንደተረከብናት የማስረከብ ሃላፊነት ታዲያ ዛሬ ላይ ቆመን ገዳማቱ ሲቃጠሉ፣ ሲመዘበሩ፣ መነኩሳት ለዓለም በጸለዩ ዱር ለዱር ተሰደው ድምጸ አራዊቱን ታግሰው፣ ግርማ ሌሊቱን ችለው ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ለክርስቶስ ፍቅር ብለው ለእኛ ለደካሞቹ በጸዩ ለምን ገዳማቱ ይደፈራሉ በማንም እንዴት ክብራቸው ይነፈጋሉ።

ይህ ጥሪ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ይልቁንም በስም ኦርቶዶክሳዊ ለሆነው በሙሉ ነው፣ ዛሬ ቤተክርስቲያን ሰው አጥታለች፣ እንባዋን የሚያብስ ትውልድ የምትፈልግበት ወቅት ነው ትርምሳችንን እኔ የአባ እገሌ ነኝ፣ እኔ የመምህር እገሌ ነኝ መባባሉት ትተን ቤተክርስቲያኒቱን ልንታደግ ይገባናል፣ አባቶችቻችን እና እናቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው በደማቸው ያቆዩልንን ርስት ዝም ብሎ እንደቀላል ነገር ብንለቀው ነገ በትውልድም በታሪክም ከተጠያቂነት አናመልጥም።

ዝምታችን ይቁም፥ ቤተክርስቲያንን እንታደጋት!


ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment