Tuesday, March 6, 2012

በቅርብ ጊዜ ሊደረግ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ

‹‹እናንተ ደፋሮች ይህን ጉዳይ ብላችሁ የአንድን ሀገር መሪ ልታናግሩ መጣችሁ ››

ለዋልድባ ገዳም መነኮሳት ከ4ኪሎ ቤተመንግስት የተሰጠ ምላሽ

ከዋልድባ ገዳም ተወክለው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የአቤቱታ ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

በዋሽንግተን ዲሲ የተጠራው ታላቅ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ

በቅርብ ጊዜ ሊደረግ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ዓላማው:
  • የኢትዮጵያ መንግስት በልማት ሰበብ በዋልድባ ገዳም የሚያደርሰውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ባስቸኳይ እንዲያቆም ለመጠየቅ፥
  • በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የቤተክርስቲያንን ታሪክ እና የሀገርን ቅርስ ለማጥፋት እና ለማውደም የሚሯሯጡትን የውጪ ቅጥረኞች መንግስት፣ እንደ መንግስትነቱ ሊከታተል እና ለፍርድ እንዲያበቃ ለመጠየቅ፥
  • በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት፣ አድባራት፣ ቤተ-እምነቶቻችን ላይ በተለይ በአክራሪ ሙስሊሞች እየደረሰ ያለውን እንግልት፣ ጠባጫሪነት፣ ስደት፣ እና የሰው ነፍስ የማጥፋት ዘመቻ እንዲያስቆም እና ፍትህ እንዲሰፍን ለመጠቆም፥
  • በቤተክህነት ውስጥ ተንሰራፍቶ ስላለው የሙስና፣ የዘመድተኝነት፣ እና የተንኮል ሥራዎችን እንዲያስቆም እና አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ፣ ወንጀለኛን ለፍርድ እንዲቀርቡ፥
 
የሰላማዊ ሰልፉ ጥሪ በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አለማት የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አማኞች በሙሉ በያሉበት ሃገር በኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በቆንሲላው ጽ/ቤት ቀርበው ተቃውሞአቸውን እንደሚያደርሱ ይህንን መልዕክት የላኩልን ጨምረው ገልጸውልናል።
ከላይ አላማው እንደተገለጸው ሁሉ በሚከተሉት ከተሞች ሰልፉን ሊደረጉ እንደታሰቡ ከምንጮቻችን ሊደርሰን ችሏል
- በለንደን                                          - በበርሊን                          - በናይሮቢ
- በብራስልስ                                       - በኑረምበርግ                      - በካምፓላ
- በስቶኮልም                                       - በሲድኒ
- በፓሪስ                                           - በጆሃንስበርግ

እንዲሁም በተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች ተመሳሳይ ሕዝባዊ ሰልፎችን ለማድረግ የዝግጅት ክፍሉ እየተዘጋጀ እና እያዘጋጀ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያስረዳል። ጥቂቶቹ የአሜሪካን ከተሞች መካከል
- ሎስ አንጀለስ                                    - ቺካጎ
- አትላንታ                                         - ሲያትል
- ናሽቪል                                          - ዳላስ

 
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በመንግስት ቸልተኝነት በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ እንደሚከተለው ቀርበዋል:
v  በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሜኤሶን ወረዳ በሚገኘው አሰቦት ገዳም ሰደድ እሳት ሲቀሰቀስ ከ2001 ዓ.ም መጋቢት ወር ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
·  የአሰቦት ደብረ ወገግ ገዳም በግራኝ ወረራ አስቀድመው ከጠፉት ገዳማት አንዱ ነበር፡፡ ደብረ ወገግ ዳግመኛ የቀናው በ1911 ዓ.ም ነው፤ ያቀኑትም የታወቁት ሊቅ አለቃ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ አለቃ ገብረ መድኅን የጻድቁ አቡነ ሳሙኤልን ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ሠሩ፡፡ በ1918 ዓ.ም ደግሞ የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ጀምረው ፍጻሜውን ሳያዩ ቢያርፉም ሥራው በ1919 ዓ.ም ተጠናቋል፡፡
v  በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ጎንደር ከተማ በሳምንት ልዩነት በሁለት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በተነሡ የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች አንድ ጥንታዊ የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤት ሌላ የቅኔ ቤተ ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ወደሙ።
·  የትርጓሜ ት/ቤቱ በኢትዮጵያ ከአራቱ ጉባኤያት አንዱ የሆነውን መጻሕፍተ መነኮሳትን ብቻ የሚያሄድ ብቸኛ ቤተ ጉባኤ እንደነበር ተገልጧል፡፡
·  የጎንደር ከተማ አድባራት በአራቱ ጉባኤያት ማእከልነት የሚታወቁ ሲሆኑ በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የመጻሕፍት ሊቃውንት ትርጓሜ፣ በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ፣ በጻድቁ አቡነ ዐቢየ እግዚእ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጓሜ፣ በተቃጠለው የሐመረ ኖኅ ሠለስቱ ምእት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የመጻሕፍተ መነኮሳት ትርጓሜ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
v  በጎንደር ከተማ የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘውና በዐፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት(17ው መ.ክ.ዘ) በኖሩት የቅኔ ሊቅ መምህር ክፍለ ዮሐንስ የተመሠረተው የገለአድ የቅኔ ቤተ ጉባኤ የካቲት ሁለት ቀን 2004 ዓ.ም በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደሙ
v  በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት፣ በዲታ ወረዳ፣ ጋና ደሬ ቀበሌ፣ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 29 ቀን 2004 .. ከሌሊቱ በስድስት ሰዓት አካባቢ በእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰበት፡፡
v  በስልጤ ሃዲያ ከንባታ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ቅበት ከተማ ቆቶ ባሎሶ ቀበሌ ቆቶ መንደር የምትገኘው የጋሮሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን እስላማዊ አክራሪዎች በቀሰቀሱት የግፍ ድርጊት በሕዳር 19 ቀን 2004 ተቃጠለች።
·  የጅማውን ጭፍጨፋ የፈጸሙ እንደሆኑ የተነገረላቸው እስላማዊ አክራሪዎች በወራቤ ደብረ ኀይል ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሌላ የማቃጠል ሙከራና በዞን ደረጃም ቅስቀሳ በማካሄድ የምእመኑን ትዕግሥት እየተፈታተኑ ነው፡፡

·  “ምንም እንዳትሰጉ፤ ከክልል እስከ ፌዴራል ድረስ መደወል ያለብን አካላት ጋር ሁሉ ደውለን ጨርሰናል፤ እጃችን ረጅም ነው፤ የፈለጉበት ሊሄዱ ይችላሉ” (የስልጢ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን ሐሰን ሾሞሎ የሰበሰቧቸው የወረዳው ፖሊስ አባላት ርምጃ እንዲወስዱ ለማደፋፈር ከተናገሩት)::
·  በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት “ጉዳዩ አስቸጋሪ ቢሆንም ባለው መረጃ ላይ እየሠራሁ ነው” ብሏል፤
·  ዳይሬክቶሬቱ በቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን መቃጠል ያዘኑ ምእመናንን ለማጽናናት ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ወደ ስልጢ ከተማ/ቅበት/ እየተደረገ ያለውን ሐዋርያዊ ጉዞ “ችግሩን ማራገብ ነው” በሚል ተችቷል::
v  ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘውና ደጋግ አበው ሊቃውንትና ካህናት የወጡበት የደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም መጽሐፍ ትርጓሜ ቤት ከሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተዘጋ።
·  ከአራት ዐሥርት ዓመታት በላይ ከዘለቀው ከደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም የመጽሐፍ ትርጓሜ ት/ቤት አሁን የደቡብ ኦሞ/ ጂንካ/ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም (ሊቀ ጉባኤ ነበሩ)፤ የሰሜን ምዕራብ - ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ወጥተውበታል፤ ከቀድሞዎቹም እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ያሉት ይገኙበታል፡፡
v  በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ደሴ ከተማ በተለምዶ አሬራ እየተባለ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኘው የደብረ ሣህል ቅዱስ ዐማኑኤል እና ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኝ ፀበል ተፀብለው ወደ መኖሪያ ቤታቸው እየተመለሱ በነበሩ ወጣቶች ላይ፣ ዛሬ ጳጉሜን 3 ቀን 2003 ዓ.ም ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በደረሰ ድንገተኛ ጥቃት ሁለት ወጣቶች ሞቱ፡፡
ዝምታው ቆሞ ለእምነታችን፣ ለቤተክርስቲያናችን ልንቆም እና እንደ አንድ ልብ ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ቃል መስካሪ እንድንሆን የአምላካችን ቅዱስ ፍቃዱ ይሁን እያልን። ትክክለኛው የሰላማዊ ሰልፉ ቀን እንደደረሰን ለአንባቢያን እንደምናደርስ ቃል እየገባን በመቀጠል ስለ ወቅቱ ችግር በ"አንድ አድርገን" የቀረበውን ዘገባ እንድትከታተሉ እንጋብዛለን መልካም ጊዜ።
(አንድ አድርገን የካቲት 28 ፤ 2004ዓ.ም)፡- ከቀናት በፊት በዋልድባ ገዳም አካባቢ መንግስት ላሰበው ትልቅ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም ስራውን መጀመሩን አስመልክቶ የገዳሙ መነኮሳት ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ(ቤተመንግስት) መምጣታቸውን ከደጀ ሰላም ፤ እና ከተለያዩ ጋዜጦች ላይ አንብባችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የተባለው ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት ብዙ አብያተክርስትያናት እንደሚፈርሱ ለገዳሙ መነኮሳት መረጃ ደርሷችዋል ፤ መንግስት የሚለው ነገር ‹‹ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል መንግስት ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጥ ምንም አይነት የቤተክርስትያኗ ቦታ ለልማት አያውልም ›› የሚል ሲሆን ፤ መነኮሳቱ ‹‹እኛ ከአባቶቻችን የተረከብነውን የቤተክርስትያ ቅዱሳት ቦታዎችን በገንዘብ እና በሌላ ተለዋጭ ቦታ አንለውጥም›› የሚል ነበር፡፡ እውነት ነው ይህ የቤተክርስትያኗ የእምነት ቦታ በምንም አይነት አላፊ እና ጠፊ በሆነ ነገር አንለውጥም ፤ ደብረሊባኖስ ገዳም እና አካባቢው ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለኃይማኖት በህይወት በኖሩባቸው 98 ዓመታት ብዙ ገቢረ ተዓምራትን በእግዚአብሔር ረዳትነት ያደረጉበት እና እኛም ቦታውን ረግጠን ፤ ቤተክርስትያኗን ስመን ፤ ቦታው ላይ የፈለቀውን ጸበል ጠጥተን እና ተጠምቀን ከስጋ በሽታችን እንድንፈወስ ለእኛ ለሃጥያተኞቹ የተሰጠን ድንቅ ቦታ ነው፡፡ መንግስት እያለ ያለው ይህን የመሰለውን በዋልድባ አካባቢ የሚገኙትን የቅዱሳን ቦታዎችን በሌላ ቦታ ልቀይራችሁ ተመጣጣኝም ብር ልስጣችሁ ነው የሚለው፡፡


ይህ ነገር እንደተሰማ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚታተሙ ጋዜጣ እና መፅሄቶች አንስቶ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚዘጋጀው የአሜሪካ ድምፅ ድረስ መረጃው ሰዎች ዘንድ ለማድረስ ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ከሸገር 102.1 በቀር ሌሎቹ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል ፤ ለምን ቢባል ነገሩ ከመንግስት የሚያጋጭ ስለሆነ አብዛኞቹም ጣቢያዎች ይህን ለማውራት መረጃውንም ምዕመኑ ዘንድ ለማድረስ ሲጥሩ አልተመለከትንም፡፡ ባለፈው ግብረሰዶማውያን አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ ሲያደርጉም ከመንግስት መጣላት ነው ብለው ዝምታቸውን መርጠዋል ፤ የአርሰናል ወይም የማንችስተር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ተጨዋቾቹ የበሉትና የጠጡት ነገር ሳይቀር ይነግሩን ነበር ፤ ይህ ጉዳይ ግን ሚዛን አልደፋም መሰል ጸጥ ብለዋል ዝምታን መርጠዋል ፤ አስተውሎ ለተመለከተው ሀገራችን በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ በኩል አልታደለችም የሚያስብል ነው፡፡ ጋዜጠኛ ጉዳዮችን ሰዎች ዘንድ ካላደረሰ ማን ሊያደርስ ነው ፤
ይህን ጉዳይ ይዘው ከ1000 በላይ ኪሎ ሜትር ጋራ ሸንተረርና ሜዳውን አቋርጠው አዲስ አበባ 4ኪሎ ቤተመንግስት አቤቱታቸውን ለማቅረብ በገዳሙ የተወከሉ ጥቂት መነኮሳት አባቶች በቤተመንግስት በር ላይ ተገኝተዋል፡፡ የበር ዋርድያ (ዘብ) ምን እንደሚፈልጉ እና ማንን ማነጋገር እንደሚፈልጉ ሲጠይቃቸው ‹‹ ክቡር ጠቅላይ ሚኒትር መለስ ዜናዊን ›› ማነጋገር እንደሚፈልጉ ፤ ከየት እንደመጡ ፤ ለምን ጉዳይ እንደሚፈልጓቸው ገለጹላቸው ፡፡ ወዲያው የበር ላይ ዋርድያው ስልኩን ብድግ ያደርግና ወደ ውስጥ ይደውላል ፤ ከቤተመንግስት አንድ ሰው ስልኩን ያነሳና ከየት እደመጡ ጉዳያቸው ምን እንደሆነ ዘቡ ያስረዳላቸውና ስልኩን ይዘጋዋል ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከቤተመንግስት ከውስጥ አንድ ስልክ ይደወልና ዘበኛው ያነሳዋል ፤ የመጡትንም ባለጉዳዮች እንዲያገናኝው ትዕዛዝ ያዘዋል ፤ የበር ዘቡም ከአባቶች አንዳቸው እንዲመጡ እና ስልኩን እንዲናግሩ ይነግራቸዋል ፤ አባቶችን የሚወክሉ አንድ አባት ወደ ስልኩ ይጠጉና ስልኩን ተቀብለው ‹‹ሀሎ›› ይላሉ ፤ ከወዲያ የሚሰማው ግን ያልጠበቁት ነገር ነበር ፤ ከሰላምታ በፊት የስድብ መዓት ሲወርድባቸው ይሰማሉ ‹‹ እናንተ ደፋሮች ይህን ጉዳይ ብላችሁ የአንድን ሀገር መሪ ለማናገር የፈለጋችሁት ፤ ደፋር በሉ አሁኑኑ ሂዱ ….›› ሌሎችንም ነገሮች በቀጭኑ ሽቦ ተነገራቸው ፤ ሀሳባቸውን ለመስማት ምንም የአየር ጊዜ አልሰጣቸውም ፤ ተናግሮ ሲጨርስ ብቻ ጆሯቸው ላይ ስልኩን ዘጋው ፤ በጊዜው በሰሙት ነገር በጣም ገረማቸው ፤ ያገኙትንም መልስ ተገርመው ምን ማድረግ እንዳለባቸው በመወያየት ከ4ኪሎ ቤተመንግስት በር ፊታቸውን አዙረው ሄዱ፡፡
(ይህን ነገር ቪኦኤ ላይ ስልክ ያናገሩትን አባት የካቲት 23 /2004 ቃለ መጠይቅ አድርገውላቸዋል ፤ ከድምጽ ክምችታቸው  ማድመጥ ችላሉ)

በአሜሪካ ሊደረግ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ... 
እኛስ በአዲስ አበባ መች ይሆን የምናደርገው?

ለዚህ ጉዳይ የመጡት መነኮሳት አባቶች ቤተመንግስት ገብተው ጠቅላይ ሚንትሩን ማነጋገር ባይችሉም እንኳን መልዕክታቸውን በምን መልኩ እሳቸው እጅ እንደሚያደርሱ ጊዜ ወስደው ተወያዩ ፤ በመጨረሻም በፖስታ ቤት አማካኝነት መላክ እንደሚችሉ ተረዱ ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ ፖስታቸውን ለማግኝት ብዙ አልተቸገሩም ነበር ፤ ፖስታውን በመያዝ ቀጥታ ወደ ዋናው ፖስታ ቤት በማምራት በአካል ለመስጠት ያሰቡትን ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ስማቸውን ፅፈው በአስቸኳይ እንዲደርሳችው 30 ብር ከፍለው ሊልኩ ችለዋል ፤ በመጨረሻም ግልባጩን ለጠቅላይ ቤተክህነት የፓትርያርክ ፅ/ቤት አመሩ ፤ እዚያም ለማስገባት ከጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ያልተናነሰ ነገር አጋጥሟቸው ደብዳቤውን አስገቡ፡፡

እንደ እኔ እምነት ይህ ደብዳቤ ደርሷልም አልደረሰምም ሳይባል መንግስት ዝም እንደሚል እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁኝ ፤ ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ የሚላኩ ደብዳቤዎች የት እንደሚደርሱ የሚያወሳ የግል ጋዜጣ ላይ አንድ ፅሁፍ ወጥቶ ማንበቤን አስታውሳለሁ ፤ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከተላኩ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ደብዳቤዎች ውስጥ ለአንዱም መልስ መስጠት አልቻሉም ፤ ይህ የሚያሳየው የደረሰው ደብዳቤው መልስ ካገኝ እንደ እድለኝነትም ይቆጠራል ፤ እኛ ለማንኛውም ትክክለኛና ፤ ሚዛናዊ መልስ የምንጠብቀው ከላይ ነው ፡፡ 

በኦሪት ዘመን እግዚአብሔር እንደ ልቤ ያለው ንጉስ ዳዊት ፤ ካንተ በኋላ ሌላ ጠቢብ አይነሳም የተባለው ጠቢቡ ሰለሞን ፤ እና አያሌ ነገስታት ህዝብን ለማስተዳደር እግዚአብሔር ሾሟቸዋል ፤ ጊዜውም ሲደርስ የሾማቸውን ሽሯቸዋል ፤ አሁንም ይህ የመንግስት ወንበር ከዘመናት በፊት ያለፉት ነገስታት ተቀምጠውበታል ፤ ህዝብንም በህግና ከህግ ውጪ አስተዳድረውበታል ፤ እግዚአብሔር በዘመናቸው ሾሞ ፤ ቀብቶ አስቀምቷቸዋል ፤ ዘመናቸው ሲያበቃ አውርዷቸዋል ፤ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ይህች አሁን ያለችው ቤተክርስትያን እንዳለች አለች ፤ ዛሬ የምናያቸው ባለስልጣናት ጠዋት ታይተው ከሰዓታት በኋላ እደሚደርቁ የሳር ላይ ውሃዎች ናቸው ፡፡ ዛሬ መጥተዋል ነገ ደግሞ ወደ ማይቀርበት ሞት ይነጉዳሉ ፤ አሁንም ግን ቤተክርስትያን እንዳለች ትኖራለች ፤ ነገ ደግሞ የተሻሉት አልያም የባሱት መንግስታት ወንበሩን ስልጣነ መንግስቱን በእጃቸው ሊይዙት ይችላሉ ፤ ቤተክርስትያን ላይም መከራዋን ሊያበዙባት አልያልያ ሸክሟን ሊያወርዱላት ብቅ የሚሉ ሌሎች ሊመጡ ይችላሉ እነሱም ግን እንደ አመጣጣቸው ተመልሰው ይሄዳሉ ፤ የማይሞት ባለስልጣን የማያልፍ መንግስት አላየንምም አልሰማንምም ፤ በእምነታችንና በወንጌል እንተነገረው የማያልፍ መንግስት የምናውቀው በሰማይ ያለውን ብቻ ነው ፤ ይህች ንፅህት አንዲት ቤተክርስትያ ግን ጌታችን መድሀኒታን እየሱስ ክርስቶስ በዳግም እስኪመጣ ድረስ ከነፈተናዋ ሳትጠፋ ትጠብቀዋለች ፤ ትቆያለች፡፡ 

ከ20ዓመት በፊት አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር እንዲወጡ በጊዜው የነበረው ጠቅላይ ሚኒስቴር ታምራት ላይኔ ፊርማ አማካኝነት ከጀርባ በተሰራ ሴራ አማካኝነት ከሀገር እንዲወጡ ማድረጉን ሰውየው ከእስር ከሰነበተበት ከቃሊቲ ሲለቀቅ ራሱ በአንደበቱ መስክሯል፡፡ እሱም አንድ ወረቀት ላይ ሲፈርም የአቡኑን መሰደድ ቀድሞ ሲያውቅ የርሱ ህይወት ወደ ወህኒ እንደሚወርድ አያውቅም ነበር ፤ ለኛ አይመስለንም እንጂ ሁሉን የሚያይ አምላክ ግን ሰው የሰራውን ስራ ፤ በምድር ያደረገውን ግፍ በምድር አጸፋውን ሳይሰጠው እንዳይመለስ አይጠራውም ፤ ቤተክርስትያን ላይ እጃቸውን ያነሱ ካሉበት ቁልቁል ሲንሸራተቱ እንጂ በሞገስ በግርማ ከፍ ሲሉ አላየንም ፤ ቤተክርስትያን ቅዳሴ እንቅልፌን ነሳኝ ያለውም ኮለኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ቤቱን ከአስራዎቹ  ዓመት በላይ አልኖረበትም ፤ ሀገር ለቆ ተሰዷል ፤ አጠገቡ ያለውን ቤተክርስትያን ለዓመታት ማዘጋቱን እናስታውሳለን ፤ የህውሐት ከፍተኛ ባለስልጣን ከደደቢት በርሀ ጀምሮ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንን ቤተክርስትያንን የማፈራረስ ሴራን›› ከቀናት በፊት አስነብቦን ነበር ፡፡ እኔ የምፈራው ለእናንተው ነው የምትቆፍሩትን ጉድጓድ አታርቁት ማን እንደሚገባበት አይታወቅም፡፡ እኛ ግን ለባለስልጣኖቻችን ሀገርን የሚመሩበት ፤ ህዝብን ያለ አድልዎ የሚያስተዳድሩበት ፤ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑበት ፤ ለትውልድ ጥሩ ስራን ሰርተው ማለፍ የሚችሉበት የስልጣን ዘመን ያደርግላቸው ዘንድ ‹‹ለሰለሞን ማስተዋልና ጥበብን የሰጠህ አምላክ ለመሪዎቻችንም ማስተዋሉን አድልልን›› እያልን እንጸልያለን ፤ እግዚአብሔር ማስተዋልን ካላደለ የኛን ማስተዋል ወንዝ እንደማያሻግረን እናውቃለን፡፡ መሪዎቻችን ማስተዋሉን ካደላቸው ሀገር ሰላም ይሆናል ፤ ሰዎች ተከባብረው ይኖራሉ ፤ ቤተክርስትያንና ምዕመኑም የሰላም አየር ይተነፍሳል ፤ በእምነቶች መካከል የመከባበር መንፈስ ይመጣል መጪውም  ዘመን ብሩህ ይሆናል ፤ ያለበለዚያ ደግሞ የተገላቢጦሽ……..

ይህን የመሰለ ቤተክርስትናችን ላይ ፤ ገዳሞቻችን ላይ ያጋረጠ አደጋ እያየን ከዚህ በላይ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ከወዴት ሊመጣ ነው ፤ ይህ ለእኛ እረፍት የሚሰጠ ለነገ የምንለው ጉዳይ አይደለም ፤ በዶዘር የቅዱሳን አባቶቻችን አጽም እየታረሰ እንደ አልባሌ ነገር ወደ ሌላ ቦታ ሲወሰድ እያየን እንቅልፍም አይወስደን ፤ እረፍትም አይሰጠን ፤ ለብዙ መቶ ዓመታት በአባቶቻችን ጽኑ ተጋድሎ እና ጸሎት የቆየው የሰነበተልን ገዳም ሲፈታ እያየን ዝም አንልም ፤ ይህ የዋልድባ ገዳም አባቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም ፤ ይህ 4 ኪሎ የሚገኝው የጠቅላይ ቤተክህነት ጉዳይ አይደለም ፤ ይህ በሰሜኑ ክፍል የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ጉዳይ አይደለም ፤ ይህ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኝው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የሁላችን ጉዳይ ነው ፡፡ ይህ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ጥያቄ ነው ፤  አቡነ ጳውሎስ ይህን ጉዳይ እንደ ቤተክርስትያኗ የበላይ ሀላፊ ሞግተው ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የለንም ፤ ባይሆን ለትራንስፎርሜሽን የ5ዓመት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ከማድረግ ውጪ ፤ እኛ ሀገሪቱ ላይ ልማት አይካሄድ ፤ ድህነታችን ይሻለናል የሚል አመለካከት የለንም ፤ ነገር ግን ገዳሞቻችን ተፈተው ፤ አብያተክርስትያኖቻችን ፈርሰው ፤ የቅዱሳን አፅም እንደ አልባሌ ሁኔታ በዶዘር ታርሶ ፤ ቅዱሳን ቦታዎችን በብር ለውጠን ከምናመጣው እድገት ይልቅ አሁን ‹‹ያለን እምነት ከድህነታችን ጋር›› አስር እጅ ይሻለናል የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ይህችን እምነት አባቶቻችን ሲያስረክቡን የስጋ ድሎት እንድናገኝባት ፤ ስለ አላፊው ምድራዊ ነገር እንድናስብባት ሳይሆን መሰረታዊውን መንግስተ ሰማያትን እንድንወርስባት ነው ፡፡ እምነት እና ገንዘብን ለየቅል ተመልከቱልን ፤ ስለ እምነት ስናወራ ስለ አላፊ ጠፊ ብር አታውሩብን ፤ ስለ ቅዱሳን ቦታዎች ስናወራ ስለ ሌላ ተለዋጭጭ ቦታ አታውሩብን ፤ ይህን የምናይበት አይን የምንሰማበት ጆሮ የለንም፡፡

ኢትዮጵያ እምነት ያለውም የሌለውም መሆኗን ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በአንድ ወቅት ተናግረዋል ፤ የአንድ እምነት አይደለም የአንድ ሰው መብት በህገ-መንግስቱ መሰረት መከበር አለበት ፤ ይህ ጥያቄ ግን ግለሰባዊ አይደለም ፤ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲህ ብለው ይናገራሉ ብለን አንገምትም፤ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ለጥያቄዎችም መልስ ይሰጣሉ የሚል እምነት የለንም ፤ ከእሳቸው በታች ያሉት ሰዎች ግን በእውቀት ማነስ ተናግረውታል ይሆን ይሆናል ፤እነርሱም ቢሆኑ ቦታውን የሚመጥን መልስ መመለስ አለባቸው እንጂ እንደ መንደር ጎረምሳ መልስ መስጠት የለባቸውም ፤ ይህን የመሰለ ዜና  ሰዎች ቢያዳምጡት ለሀገርም መልካም አይደለም ፤ ጥያቄዎቻችን መሰረታዊ ናቸው ፤ መንግስትን የሚወክል መፍትሄ የሚሆን መልስ እንሻለን ፤ አባቶቻችሁ ገዳማትን ሰርተው አቆይተውልናል ፤ እናንተ ልጆቻቸው ገዳሙን የመጠበቅ ታሪካዊ አደራም እንዳለባችሁ አትዘንጉ ፤ ከአስር መቶ አመታት በላይ ተጠብቆ ሲወርድ ሲዋረድ ያለውን ቦታ በልማት ሰበብ ድንበሩን አታፍርሱብን፡፡

ባያውቁት ነው እንጂ ይህች ቤተክርስትያን ስለ ምዕመኗ ፤ ስለ ሀገር ሰላም ፤ ስለ አገልጋዮች ፤ ስለ ሀገር ድንበር ፤ ስለ እሰር ላይ ስለሚገኙ ሰዎች ፤ ስለ ዓለም ሰላም ፤ ስለ ዝናብ ብቻ ስለሁሉም ነገር ሳትጸልይ የኖረችበት ጊዜ የለም ፤ ትላንትና ጸልያለች ፤ ዛሬም ትጸልያለች ፤ ነገም እንደዚያው ፤ ቤተመንግስቱ  ዙሪያውን ከበውት የሚገኙት የቅዱስ ገብርኤል ፤ የበአታ ለማርያም ፤ የኪዳነምህረት ፤ የስላሴ ፤ የእግዚአብሔር አብ አብያተ ክርስትያናት የነግህ ኪዳን ፤ የጠዋት ጸሎት ፤ ቅዳሴ ፤ ለሀገር ለህዝበ ክርስትያን እንደሚተርፍ የተረዱት አይመስለኝም ፤ በዱር በገደሉ ያሉ የአባቶች እንባ ለሀገር ሰላም የጀርባ አጥንት መሆኑም አልገባቸውም ፤ አንድ ምሳሌ ብቻ እናንሳ ፤ በ1997 ዓ.ም ሚያዚያ 30 ቀን ቅንጅትን በመደገፍ በመስቀል አደባባይ የተሰበሰበው ሰው (በጊዜው የነበራችሁ ሰዎች ታስታውሱታላችሁ ) እግዚአብሔር ያንን ለተቃውሞ የወጣ ህዝብን በጠራራ ጸሀይ ዶፍ ዝናብ ከሰማይ አውርዶ ባይበትነው ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቦት የሚያውቅ ሰው አለ? የትኛው ጦር ፤ የትኛው ፌደራል ፖሊስ ነው የሚበትነው? ከዚያን ቀን በፊትም ሆነ በኋላ እንደዚያ ያለ ዝናብ አላየሁም፡፡ እንኳን በዝናብ አለፈ ፤ እንኳን ደም ያልፈሰሰ ፤ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ ‹‹እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ ሰራተኞች በከንቱ ይደክማሉ እግዚአብሔር ከተማ ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል›› መዝሙረ ዳዊት 127 ፤ 1  ይላል፡፡ እኛ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ሐገረ እግዚአብሔር የምንለው ፤ የእኛ ሀጥያት ቢበዛ የበደላችን ፅዋ ሞልቶ ቢፈስ እንኳን እግዚአብሄር ይችን ሀገር አይተዋትም ፤ እርሱ ለቤቱ ከእኛ በላይ ይተጋል ቤቱንም ይጠብቃል ፤ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ስለ ሀገር ፤ የሚጸልዩ የአባቶቻችን  ባእት ሲፈርስ እያየን ዝም አንልም፡፡ የሰማዕቱን የቅዱስ ጊዮርጊስን የአድዋ ውለታ ሚኒሊክ ከመቃብር ተነስተው ቢናገሩ ደስ ይለን ነበር ፤ በጊዜው የነበሩ የጣልያን ወታደሮችን ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሰከሩት በታሪክ መዛግብት ተፅፎ ተቀምጧል፡፡ አሁን እያልን ያለነው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሀገራቸው እና ለእምታቸው ሰማዕት የሚሆኑ የአባቶቻችንን ማረፊያ ፤ የቅዱሳንን መናህሪያ አትንኩብን ፤ ለትውልድ የሚተርፍ ስህተት አትስሩ ነው የምንለው፡፡

መሪ ማለት ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ድረስ ሄዶ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የራሱን ጥረት ያደርጋል ፤ እንደ አለመታደል ሆኖ እኛ ጥያቄያችንን ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መሀል አዲስ አበባ ድረስ ስናመጣ መልሳቸው ስድብ ሆነብን ፤ ችግሩን አያውቁትም ብለን አይደለም ጥያቄውን እዚህ ድረስ ያመጣነው ፤ ድምጻችን ቢሰማ መፍትሄ ብናገኝ ብለን እንጂ ፤ ታዲያ ይህችን ሀገር የሚያስተዳድራት ህዝብ በየ5 ዓመቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እያደረኩ ህዝቡ 99.6 በመቶ መረጠኝ ለሚለው መንግስት ጥያቄያችንን ከአፈር ከደባለቀብን ሌላ የት ሄደን አቤት ማለት እንችላለን ፤ የእስራኤል አምላክ እንደማይተወን እርግጠኞች ነን ጸሎታችንን አናቋርጥም ፤ እንባችንንም ወደ ላይ እንረጫለን ራሄልን የተመለከተ አምላክ እኛንም ይመለከተናል አንጠራጠርም ፡፡ 
ቸር ወሬ ያሰማን አሜን
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment