“የአባቶቻችን ርስት እና ቅርስ ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፍ” የሚል መሪ ቃል ያለው የአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፍ የአሜሪካን መንግስት መቀመጫ በሆነችው በዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ መጋቢት17፣2004 ዓ/ም በአካባቢው የሰዓት አቆጣጠር 9am ላይ ተካሄዶዋል:: በአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፉ ላይበቦታው የተገኙ አባቶች በጸሎት አስጀምረዋል:: በሰልፉም ከአንድ ሺህ በላይ ክርስቲያኖች እንደተገኙ በአካባቢው የነበሩ ዘጋቢዎቻችን ገልጸውልናል:: በአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፉም በአስተዳደር ምክንያት የተለያዩ ወገኖች በአንድነት የቤተ ክርስቲያን ህልውና የሚፈታተኑን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል:: ለአራት ሰዓታት ያህል የቆየው የአቤቶታው ሰልፍ በተለያዩ መዝሙራት የታጀበ ነበረ:: ተሳታፊዎቹም ጥያቄዎቻቸውን በእንባ እና በጩኸት ለኤምባሲው አሰምተዋል::
የጠቅላይ ሚንስተሩ ጽ/ቤት ከዋልድባ ገዳም በተወከለቱ የገዳሙ አባቶቻችን ላይ ያሳየውን ንቀት የዋሽንግተን ዲሲው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለአቤቶታ በወጡ ክርስቲያኖች ላይ ንቀቱን ደግሞታል:: አቤቶታ አቅራቢዎች ለሦስት ሰዓታት ተኩል ያህል በኤምባሲው በር ላይ መብታችውን ሲጠይቁ ከኤምባሲው ማንንም ምንም የመንግስት ተወካይ ወጥቶ ሊያናግራቸው አልቻለም ነበር:: በመጨረሻም አንድ ተላላኪ ወጥቶ “ዛሬ ሳይሆን ነገ እናግራችኋለን” በማለት አሳፋሪ ምላሽ እንደሰጣቸው ዘጋቢዎቻችን ገልጸውልናል:: መንግስት በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ላይ እያደረገ ያለውን ንቀት በዋሽንግተን ዲሲ ባስቀመጣቸው ተወካዮቹ ጭምር ደግሞታል:: ታድያ ንቀቱ እስከ መቼ ድረስ ይሆን? 

ክርስቲያኖች በአላውያን ነገስታት ወይም በእምነት የለሽ ገዢዎቻቸው ጭቆና ሲበዛባቸው በጸሎት አምላካቸውን ከመማጸን በተጨማሪ ድምጻቸውን ለመንግስታት ማሰማት በአሐት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተለመደ ነው:: የግብጽ፣ የአርመን እና የሶርያ ክርስቲያን ወንድሞቻችን በተለያዩ ጊዜያት በገዢዎቻቸው ጭቆና ሲደርስባቸው ለዓለም መንግስታት እና ለራሳቸውም መንግስታት በአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፍ ጩኸታቸውን እንደሚያሰሙ በተለያዩ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ እንሰማለን:: በሕገ ክርስትና በኢ-አማኞች ጭቆና ሲደርባችሁ የአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፍ አትውጡ የሚል ነገር የለም:: ስለዚህ ክርስቲያኖች የአቤቶ ታሰላማዊ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታችው ተገቢ ነው:: 
አቤቶታን ለዓለም መንግስታት ማቅረብ በአሐት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንደተለመደው ሁሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ዘንደም መለመድ አለበት በማለት የሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጆቹ በቦታው ለተገኙ ዘጋቢዎቻን ገልጸውላቸዋል:: 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያ ከአርባ ዓመት ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ክርስቲያኖች ሲታረዱ፣አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለወህኒ ወርደው በግፍ ሲገደሉ እንደሌሎች እሕት አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ድምጻቸውን ለዓለም መንግስታት አላሰሙም ነበረ:: ይህ ዛሬ የተካሄደው የአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፍ ከእንግዲህ ወዲህ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች “ዝምታው በቃን ድምጻችን እናሰማለን” በማለት የተጀመረ ይመስላል:: ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ የተዋሕዶ ልጆች በጥታውያን ገዳማቶቻችን እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለማስቆም የአቤቶታ ሰላማዊ ሰልፍ እንቅስቃሴ ለማካሄድ የዛሬው አቤቶታ መልካም ጅምር ነው:: በሰላማዊ ሰልፉ የተነሱ ጥያቄዎች እንደሚከተለው ቀርቧል:: 

- · ክርስቲያኖች ዋልድባን ነጻ ያወጣሉ፣
 - · በዋልድባ ጉዳይ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድነት እንቆማለን፣
 - · ጳጳሳት ውሳኔያችሁ ይሰማ፣
 - · የአባቶቻችን ርስት ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፍ፣
 - · የገዳማት አባቶቻችን መብት ይጠበቅ፣
 - · ዋልድባ ነጻ ትውጣ፣ መንግስት የመነኮሳቱ ድምጽ ይስማ፣
 - · ዋልድባ የቅዱሳን እንጂ የኢንቨስተር አይደለችም፣
 - · አባቶቻችን ያስቀመጡልን ገዳማት ሲፈርሱ ዝም አንልም፣
 - · የቤተ ክርስቲያን መሪ አባቶች ዝምታችሁ ይብቃ፣
 - · ገዳማትን የሚያፈርስ መንግስት አንፈልግም፣
 - · የስልጣኔ ምንጭ የሆነች ቅድስ ቤተ ክርስቲያን መብቷ ይከበር፣
 - · ገዳማት የጸሎት ቦታ እንጂ የመዝናኛ ቦታ አይደሉም፣
 - · ክርስቲያኖች የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ፣
 - · አድባራትንና ገዳማትን ማጥፋት ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው፣
 - · የአባቶቻችን ተረፈ አጽማቸው ይከበር፣ አጽማቸው ቆፍሮ ማውጣት ይቁም
 - · ልማት ገዳማትን በማፍረስ አይመጣም፣
 - · ሃይማኖታችን የማንነታችን መገለጫ ናት ስለዚህ መንግስት ይህንን ያክብር፣
 - · ሃይማኖት ከሌለ ሀገር አይኖርም፣
 - · ገዳማት የሚያፈርስ መንግስት ተቀባይነት የለውም፣
 - · አብያተ ክርስቲያናት ያቃጠሉ ለፍርድ ይቅረቡ፣
 - · ቅዱስ ሲኖድ የገዳማትን ይዞታ የማስከበረ ግዴታ አለበት፣
 - · ገዳማትን ማጥፋት በታሪክ ያስጠይቃል፣
 - · ገዳማቱ እንዲከበሩ እንፈልጋለን፣
 - · ገዳማትን የሚያፈርሱ አይከበሩም፣
 - · ዋልድባን ለማጥፋት የሚሞክሩ ይጠፋሉ፣
 - · ገዳማቶቻችን ታሪካችን ናቸው፣
 - · የአብነት ተማሪው ናታንን የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ፣
 - · የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ለሃይማኖታቸው ዝም አይሉም፣
 - · መንግስት ሃይማኖታችን ከማጥፋት ይቆጠብ፣
 - · አጥፊዎች ለፍርድ ይቅረቡ፣
 

የሚሉ ናቸው:: የጥንታውያን ገዳማት ህልውና ማስጠበቅ የቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ማስጠበቅ ነውና በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የተዋሕዶ ልጆች በአጠቃላይ የፖለቲካ እና የዘር ልዩነታቸውን ትተው የአንድነት ድምጻቸውን ለሚመለከተው ሁሉ እንዲያሰሙ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች አደራ ብለዋል:: አሐቲ ተዋሕዶ ይህንን የአደራ ቃል ለምእመኑ ሁሉ እንዲዳረስ የበኩሏን ጥረት ታደርጋለች::
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:
Post a Comment