Saturday, March 17, 2012

‹‹ራሳችንን ለሰይፍ አዘጋጅተን የተቀመጥን ሰዎች ነን›› የዋልድባ መነኮሳት


‹‹ራሳችንን ለሰይፍ አዘጋጅተን የተቀመጥን ሰዎች ነን›› የዋልድባ መነኮሳት

  • እኛ በዚህ ያለነው ማህበረ መነኮሳት አቅም የለንም ማድረግ የምንችለው ለሰይፍ ተዘጋጅተን መቀመጥ ብቻ ነው እኛን ገድላችሁ ፋብሪካውን መስራት  ችላላችሁ
  • እናንተ የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ ፤ እኛ ይግባኝ ለክርስቶስ ሰጥተናል››   
(አንድ አድርገን መጋቢት 7 ፤ 2004ዓ.ም)፡- ከቀናትበፊት በመንግስትና በዋልድባ ገዳም መካከል ስላለው ውዝግብ መረጃ  አቅርበን ነበር ፤ አሁን እንደሰማነው ቅዳሜ 01/07/2004ዓ.ም እና ማክሰኞ 04/07/2004ዐ.ም በሽሬ ከመንግስት የተወጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት የገዳሙን አባቶች ለማነጋገር ፕሮግራም ይዘው ነበር ፤ ነገር ግን ከአባቶች በኩል በእዚያ ያሉ ሰዎች ለእኛ ጥሩ አመለካከት የላቸውም ስለዚህ በአማካይ ቦታ በአድርቃይ ስብሰባውን እናድርግ ያሉ ሲሆን በዚህ ተስማምተው ስብሰባውን አድርቃይ አድርገዋል፡፡
·        ከቤተክህነት የተወከሉት አባት እንዴት ይህን ጉዳይ እኛ ሳናቀው የግል መገናኛ ብዙሀን ጋር ይዛችሁ ትሄዳላችሁ ይህ አግባብ ነው ወይ ? የሚል ጥያቄ የተጠየቁ ሲሆን የዋድባው አንድ አባት ‹‹መንግስት ለመገናኛ ብዙሀን የመፃፍም ሆነ የመናገር መብት እስከሰጣቸው ድረስ እኛ ጉዳዩን የፈለግነው ጋር ይዘን እንሄዳለን ፤ መብታችን ነው›› የሚል መልስ ሰጥተዋል ፤ መገናኛ ብዙሀን የህዝብን ድምጽ ተቀብሎ ለህዝብ እንዲያደርስ ፍቃድ ተሰጠው ህጋዊ ተቋም ነው ፤ እኛ ምንም ያጠፋነው ነገር የለም ፤ ቤታችን ሲፈርስ መሬታችን ሲታረስ እያየን ቤተክርነቱን መጠበቅ አይጠበቅብንም ተብለዋል ፤ ‹‹ነጻ ሚዲያ እስካለ ድረስ ጉዳዩን ነጻ ሚዲያ ላይ ማውጣት ህገ መንግስታዊ መብታችን  ነው›› ብለዋል፡
  • በተጨማሪ ከቤተክህነት የተወከሉ ሰው የዋልድባው አባት በሰጡት ሀሳብ ላይ ይህ የቤተክርስትያ አስተምህሮ አይደለም  ፤ ጉዳዩን አንድ ላይ ሆነን ነበር መንግስት ዘንድ ማቅረብ የነበረብን ሲሉ ፤ ‹‹ እናንተማ ቤተክርስትያኗን ለመንግስት አሳልፋችሁ ለመስጠት ፤ ከመንግስት ጎን ተሰልፋችሁ መጣችሁ ይህን ጉዳይ ከናንተ ጋር ሆነን መንግስት ዘንድ ይዘን መቅረብ አንችልም ፤ እናንተ ሲጀምር ለቤተክርስትያን ህልውና የቆማችሁ አይደላችሁም›› ተብለዋል፤  ከተሰብሳቢ አባቶች በኩል ተገቢ አፍ የሚያስይዝ መልስ ተሰቷቸዋል ፤

አይ ቤተክህነት ከአባቶች ጎን ቆሞ መንግስት ጋር ተገቢውን ጥያቄ ይዞ በመቅረብ ለዚህ የጭንቅ ጊዜ አጋር እደመሆን የራሷን አቋም ይዛ ከአባቶች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባት ምን ይሉታል?  ገዳም ያሉ አባቶች ለነፍሳቸው ያደሩ መሆናቸው ዘነጋችኋቸው እንበል?  ቤተክህነት የራሱን ውሳጣዊ ችግር ሳይፈታ ይህን የሚያህል ቤተክርስትያን ላይ ያጋረጠን ክፉ ጊዜ ማለፊያ መንገድ ይጠቁማል  ማለት ዘበት ነው ፤ ለነፍሳቸው ያደሩ አባቶች ከአምላካቸው ጋር ይፈቱታል ለእናንተ ለስጋውያን ግን ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ 
 ይህ ጉዳይ ለቢዮንሴ ወረብ ማስወረብን ያህል የቀለለ አይደለም ፤ ቆም ብላችሁ ተመልከቱ ፤ ነገንም አስተውሉ ፤ ከቤተክርስትያን ዘንድ ብቻም ወግኑ ፤ እናንተ ሀላፊነታችሁን መወጣት ቢያቅታችሁ ለባለቤቱ ተውለት ፤ የግብጽ መንግስት የኮፕቶችን ገዳም ለማደስ 14 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ መንግስተት ጋር ተነጋግሮ እርዳታ እንዲያገኙ ሲያደርግ ፤ የእኛው ደግሞ ገዳማችንን ህልውናችንን አፍርሶ ስኳር ፋብሪካ ሊያቋቁም ተነሳ  ይገርማ !!   
·        በስብሰባው ላይ የመንግስት ተወካዮች የስኳር ፋብሪካ ግንባታው ስራ አስኪያጅ እና የሚመለከታቸው አካሎች ከመንግስ በኩል የተገኙ ሲሆን ከአባቶች ወገን ደግሞ ሶስት አባቶች ተወክለው ስብሰባውን አድርገዋል፡፡ ስብሰባው ሲደረግ የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ‹‹ በከተሞች አካባቢ የሥኳር ችግር አለ ማህበረሰቡ ስኳር እጅጉን እየተቸገረ ነው፤ ኪሎ ስኳር 18-20 ብር ገብቷል ፤ ይህ ግንባታ ቢከናወን ለሀገርም ለህዝብም ጥሩ ነው የሚል የተሞላውን ዲኩር አሰምቷል ›› ቀጥሎም ምንድነው ችግሩ በማለት ችግሩን ያልታየው ይመስል በጣም በመቆጣት ጥያቄ አቅርቧል ፤ ቁጣ እንኳን አንዳንዴ ከዘር ሊተላለፍ ይችላል አንዳንዴም ደግሞ ግቡን እንዲመታ የሚፈልጉትን ጉዳይ ጽንፍ ይዞ ሲሟገቱ ሳያቁት ሊቆጡ ይችላሉ ፤ በአንድ ጥናት ላይ ስልጣን ያላቻው ሰዎች ለመናደድ ቅርብ ናቸው ይላል ፤ ከአባቶች ዘንድ የተሰጠው ምላሽ‹‹እኛን ገድላችሁ ፋብሪካውን መስራ ትችላላችሁ ራሳችንን ለሰይፍ ነው ያዘጋጀነው  ፤ እኛ የዋልድባ አፈር ጠባቂ ነን እንጂ  ጠባቂው መድሀኒአለም ነው ፡ ዋልድባን ብታከብሩት ትከበራላችሁ ዋልድባን ብታቀሉት ትቀላላችሁ ብለው በግልጽ ነግሯቿል›› ፡፡ እንዴት ደስ ይላል ቤተክርስትያ በአሁኑ ሰዓት እየተቸገረች ያለችው አቋም የሌለው ሰው በማጣቷ ነው ፤ ከመንግስት ፖሊሲ እና ከእድገትና ትራንስፎርምሽን እቅድ ጋር አብረው ራሳቸውን የሚቀያይሩ ሰዎች ተከባለች ፤ ቤተክርስያን አቋሟ ከመንግስ ጋር አብሮ የሚቀየር አይደለም ፤ የባለስልጣንን ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ የሚንቀሳቀስም አይደለም ፤ ስለምናከብረው እና ስለ ምንፈራው ሰው ብለን የምንለዋውጠውም መሆን የለበትም ፤ እንደ ዋልድባ ገዳም  አባቶች ብንኖርም ብንሞትም በእምነታችን ላይ አቋም ያስፈልገናል ፡፡ የእነሱ አቋም ‹‹አይሆንም ራሳችንን ለሰይፍ አዘጋጅተናል ፤ እኛን ሰውታችሁ አላማችሁን ማሳካት ትችላላችሁ›› የሚል ነው አራት ነጥብ፡፡
·        ስብሰባውን በተጨማሪ ለአንድ ቀን ሙሉ መነኮሳት ፤ አቡነ መርቃርዮስ ፤ ባሉበት ተካሂዷል በጊዜው የታረሱትን ቦታዎች ተመልክተዋል ፤ አቡነ መርቃርዮስ ስብሰባውን በጸሎት አስጀምረዋል ፤ በውይይቱ መሀል ላይ ውይይቱ እየጋለ መጥቶ እንደነበር ለማወቅ ችለናል ፤ በሁለቱም በኩል ከረር ያሉ ቃላትን የመመላለስ ነገር ይታይበት ነበር ተብለናል ፤ አባቶች ነገሩ አላምር ሲላቸው ‹‹እናንተ የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ ፤ እኛ ይግባኝ ለክርስቶስ ሰጥተናል ለምን ትጨቀጭቁናላችሁ ስራውን እየሰራችሁት አይደል ..››ብሎ ‹አሁንም እንሰየፋለን እንሰየፋለን ብሎ የመነኮሳት ማህበሩ ከስብሰባው ተነሳ ፤ በጊዜው የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት በአባቶች ሁኔታ በጣም መደንገጣቸውንም ለማወቅ ችለናል ፤ 18 ቤተክርስያ ፈርሰው ሸንኮራ ልማት የማይታሰብ ነው ፤ ብለው አቋማቸውን ገልጸውላቸዋል፡ 
·        በትግረኛ ፕሮግራም የገዢው ፓርቲ ሰዎች ቦታው ድረስ በመሄድ የማይመለከታቸውን ሰዎችን በማነጋገር የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለህዝቡ አናፍሰውለታል ፤ የገዳሙ አባቶች ልማቱ ላይ እንደማይቃወሙ በማስመሰል የምን ጊዜም ተግባሩ በቴሌቪዠን ያንጸባረቀ ሲሆን ፤ ይህን ጉዳይም አንስተው ጉባኤው ላይ ተነጋግረዋል ፤ የተሰራውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተመልክተናል ፤ የተሰራው ስራ እኛን አይወክልም የኛም ድምጽ አይደለም ብለዋቸዋል ፡፡ ይህ የህዝብን ድምፅ ለማፈን የሚደረግ ሴራ አጥብቀን እንቃወማለን ፤ ህዝቡ እያለ ያለው ልማታችን አይቋረጥ ገዳማችንንም አትንኩብን እንጂ ለልማት ከሆነ ገዳሙ ይፍረስ የሚል አቋም ያለው ማህበረሰብ የለም ፤ ይህን ነገር በህዝቡ ውስጥ አልሰማንም አላየንምም ብለዋል ፤
·        የልማት ስፍራው ላይ 3 መትረየስ ተጠምዶ በከፍተኛ ሁኔታ ፌደራል ፖሊስ እየጠበቀው ይገኛል ፤ በሁኔታው መወሰን ያልቻሉት ባለስልጣናት ፤ ጉባኤውን ለቅዳሜ አቦይ  ስብሀት ባሉበት ሽሬ ላይ ይደረጋል ብለዋል ፤ አንድ አባት በሰጡት አስተያየት አይደለም አቦይ ስብሀት ጠቅላይ ሚኒትሩም ቢያደራድሩን ከአቋማችን ፍንክች የምንል መነኮሳት አይደለምን ፤ ራሳችንን ለሰይፍ ያዘጋጀን ሰዎች ነን ያለነው ፤ እኛን ገለው ፋብሪካውን መስራት ይችላሉ ብለዋል ፡፡ እኝው አባት አያይዘው ይህችን ቤተክርስትያ እየሸጧት ያሉት አቡነ ጳውሎና መንግስት  ናቸው ማንም አይደለም ብለዋል ፤ በጉባኤው ሂደት ቅዳሜም ምንም አይነት ለውጥ ይመጣል ተብሎ አይጠበቅም ፤ ቅዳሜም ለውጥ ስለሌለ አንሰበሰብም የሚል አቋም እንዳለ ለማወቅ ችለናል ፤

  • እኛ መሳሪያ የለንም ፤ ከናንተ ጋር ግንባር የምንገጥም ሰዎችም አይደለንም ፤ እናንተ በጉልበታችሁ ሁሉን ማከናወን ትችላላችሁ እኛም ለመሰዋት ዝግጁ ነን ይህን ስለቤተክርስትያን የምንቀበለው ሰማእትነት ነው ፤ ዋልድባ በ4 ወንዞች የተከበበች ናት አይኗን፤ እግሯን ጥፍሯ ከአካላቷ አንዲቷም እንድትነካብን አንፈልግም ፤ የበፊት የዛሬ የወደፊት አቋማችን ይህው ነው ብለዋቸዋል ፡
·   እኛ በዚህ ያለነው ማህበረ መነኮሳት አቅም የለንም ማድረግ የምንችለው ለሰይፍ ተዘጋጅተን መቀመጥ ብቻ ነው ብለዋል ፤ አቅም ያላቸው በውጭ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስን አማኞች በያሉበት በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ጥያቄያችን ያቅርቡልን ፤  ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ሀሳባችንን ተጋርተው ከአጠገባችን እዲቆሙ መልእክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል፡፡

አባቶቻችን ይህችን እምነት ይዘው ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አያውቅም ፤ ለክርስትያን ፈተና የህይወቱ አንዱ ክፍል ነው ፤ ፈተናን መወጣት የሚቻለው በጉልበት ፤ በገንዘብ ፤ ባስልጣን  አይደለም ፤ እንደ ቤተክርስትያናችን አስተምህሮ ፈተናን ለመቋቋም ጾም ፤ ጸሎት ፤ ስግደት እና የትሩፋት ስራዎችን ከፅናት ጋር  መስራት ግድ ይላል ፤ በአሁኑ ሰዓት የኛ ፈተናችን ይህ ነው ፤ ፈተናችንን በድል እንድንወጣ ሁላችን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሆነን ከገዳማውያን አባቶቻችን ጎን መቆም መቻል አለብን ፤ እነሱ የመጣውን ሊቀበሉ ወስነው ተቀምጠዋል ፤ ቤተመንግስት ድረስ ሄደው ያተረፉት ስድብ ብቻ ነው ፤ ስለዚህ በጾምና በጸሎት ከገዳማቸው  ሆነው አምላክን ቢለምኑት ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ካልሆነም በህይወት እያለን ይህን ማየት ስለማንፈልግ እኛን ገላችሁ መስራት ትችላላችሁ የሚል አቋም ወስደዋል ፤ ቤተክህነቱም ከመንግስት ጎን በመቆም ሊያስማማ ወደ ቦታው ተወካዩን ልኳል ፤ ይህም አለመታደል ነው ፤ እኛስ ምን ማድረግ አለብን ? ለሁላችን የምጠይቀው ጥያቄ ነው፡፡ እስኪ በጸሎት እናስባቸው ፤ ይህንም የፈተና ጊዜ ቤተክርስትያን ታልፈዋለች  አንጠራጠርም ፤


‹‹መካሪ የሌለው ንጉስ ያለ አንድ ዓመት አይነግስ›› ይባላል ፤ እኛ አሁንም የአባቶቻችን ርዕስት ሲፈርስ የምናበት አይን የምንሰማበት ጆሮ የለንም ፤ ዋልድባ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ እንድናስረዳችሁ ከፈለጋችሁ መልካም ፤ ያለበለዚያ በሞላ ቦታ አይናችሁን ከዋድባ ላይ ብታነሱ መልካም ነው ፤ ከእኛ ጋር ሳይሆን የምትጋፈጡት ከባለቤቱ ጋር መሆኑንም አትርሱት ፤ ባለቤቱ ደግሞ የሰማይና የምድር ፈጣሪ መድሀኒዓለም ነው የራሄልን እንባ የተመለከተ አምላክ የእነሱንም ይመለከታል ፤ ዓይንን የፈጠረ አምላክ ያያል ፤ጆሮን የፈጠረ ጌታም ዘንበል ብሎ እሪታችችን ኡኡታችን ይሰማል አንጠራጠርም ፤ በእናንተ ጩህት የሚመጣ ነገር የሰው ጆሮ ማደንቆር እንጂ ሌላ ነገር አይደለም ፤ የቅዱሳንን አጽም እንደ አልባሌ ነገር አትቁጠሩብን ፤ ለእናንተ ምንም ሊሆን ይችላል ለእኛ ግን  ትርጉም ያለው ነገር ነው ፤ ለነገሩ መጠበቅ የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ ምን ዋጋ አለው የራስን ዝቅ አድርጎ የማየት ክፉ አመል ተጠናውቶናል እናም እኛ አንፈርድም፡፡ ገዳሙን ግን ለቀቅ አድርጉን ፤  ይህን ፅፌ ከጨረስኩኝ በኋላ ገዳሙ እየተጋፈጠ ያለውን  ፈተና አስቤ እንባዬ መጣ...... አይኔንም ሞላው……………


የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment