Monday, March 5, 2012

የዋልድባ ገዳም በመንግስት እና በቤተክህነት ሰዎች ሲፈተን

ባለፈው ጥቂት ወራት ውስጥ እንደዘገብነው የብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ፣ የቅዱሳን ማረፊያ፣ እንዲሁም ለሃገራችን ኢትዮጵያ እና ለመላው ዓለም የሚማልዱ ገዳማውያን የጸሎት ቦታ እና የአምልኮ ቦታ የሆነው ጥንታዊው የዋልድባ ገዳም በገዛ ሀገራችን መንግስት ይልቁንም በቤተክህነት ውስጥ ባሉ የውስጥ የመናፍቃን ቅጥረኞች እና ሃይማቷን ለመበረዝ እና ታሪክን እና የታሪክ አሻራን ለማጥፋት የሚሯሯጡ ወገኖች በፈጠሩት ግልጽ ወረራ በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያኒቷን ያለ ተተኪ ሊቃውንት እና መነኩሳት ለማስቀረት የሞት ሽረት ትግላቸውን እየታገሉ ነው። በመሠረቱ የቤተክነቱ ሰዎች ለቅዱስ ፓትሪያሪኩ ጀምሮ በሞላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተከታታይ በተለያዩ በኢትዮጵያ ገዳማት ላይ መጠነ ሰፊ የሆነ ወረራ፣ ዘረፋ፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የተለያዩ የአብነት ት/ቤቶችን መዝጋት፣ አሁን ደግሞ ጭራሽ የገዳሙን ሕልውና ማሳጣት ይህ ሁሉ በደል ለቅድስት ቤተክርሲያናችን ተተኪ ጳጳሳትን፣ ፓትሪያሪክን እንዲሁም ባለ ብዙ ሙያ ሊቃውንትን የሚያፈሩት ገዳሞቻችን ሲፈተኑ ምነው ዝምታ አበዙ?


የቤተክርሲያኒቱ የመጨረሻው አካል ቅዱስ ሲኖዶስ እንደሆነ የታወቀ ነው፥ ታዲያ እንዲህ አይነቶችን ሥራ መንግስትም ይሁን ሌሎች በውስጥ ያሉ ቅጥረኞች መንግስት ከውጭ በማናለብኝነት፣ ሌላው ከውጪ ገንዘባቸውን ከእኛው እየሰጡ እና ሆዳችንን የሞኩ የራሳችንን ታሪክ በእነሱ ሊለውጡ በሚሞክሩ የምዕራባውያን ወረራ፣ ከውስጥ ጡቷን ጠብተው ባደጉ መነኩሳት እና ጳጳሳት፣ ከመቼውም በተለየ መልኩ ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ይገኛሉ ታዲያ ቤተክህነቱም፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ዝምታውን ቀጥሏል እስከ መቼ ይሆን ዝምታው፥ በፊት በርቀት ነበር ጥቃት ፈጽመው የሚሰወሩት ፈተኑን፣ ማንም ምንም ያለ የለም እውነትም እነዚህ ሰዎች ነገ ምንም ብናደርግ ምንም ሊሉን አይችሉም ብለው መዝነው አንጥረው አዩን አሁን ግን በግልጽ እነዚህን የብዙ ቅዱሳን አጽም የፈሰሰበትን ገዳም መንግስት በግሬደር እያረሰ እና የገለበጠ ለመንገድ ጥርጊያ ነው በሚል ሰበብ ብዙ በደል እያደረሰ ይገኛል። ዛሬ በፈታኝ መገንጠያ ላይ እንገኛለን በሁለት ምርጫ መካከል ዛሬ የምንወስነው ይህችን ርትዕይት ሃይማኖታችንን ከአባቶቻችን እንደወረስናት ለተተኪው ትውልድ የማድረስ ሃላፊነቱ በዚህ ትውልድ ላይ መሆኑን ሁላችንም ልብልንለው የገባል።

ዛሬ በቤተክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ችግሮች አይን አውጥተው መጥተዋል፣ እስቲ ለአብነት ጥቂቶቹን እንጥቀስ
  • የብዙ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ ገዳማውያን መፍለቂያ የዋልድባ ገዳም በመንግስት ማናለብኝነት በግሬደር ሲታረስ የንጹሓን እና የቅዱሳን ርስተ አጽማቸው በሰላም እንዳያርፍ ታርሶ ሲነሳ እና በግዞት ወደአልተፈለገ ቦታ ሲወሰድ ዝም ብለናል።
  • መንግስት ባላጣው መሬት ባላጣው ቦታ በምዕራብ የሃገራችን ክፍሎች ከ500 ሄክታር በላይ ለሕንዱ ባለሃብት እንደተሰጠ በተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች ተዘግቧል፣ ያሁሉ መሬት እና ያለማ ብዙ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መኖሩ እየታወቀ ዛሬ ለምን ወደዚህ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ገዳም እጃቸውን አነሱ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካላት ለምን ዝምታ መረጡ?
  • የተለያዩ የቤተክርስቲያናችን አዋልድ መጽሐፍት በትልቅ ችግር ውስጥ ገብተዋል ይልቁንም በትንሳኤ ዘጉባኤ ታትመው በቅርብ ከወጡት የጸሎት መጽሐፍቶች ብዙ ነቅ እና ሕጸጽ የሞላባቸው እንደሆኑ ልብ ልንል የገባል።
  • በቅርቡ ቤተክርስቲያኒቱ ያሳተመችው መጽሐፍ ቅዱስ እስጥ ባሉ ሰርገው በገቡ መናፍቃን እና ቅጥረኞቻቸው ብዙ እንክርዳድ ከጥሩው ዘር ጋር ተዘርቷል፣ ቤተክህነቱ ተመልካች አጥቷል ቅዱስ ሲኖዶስ የግል ቤት እስኪመስል ድረስ ብዙ በደል ሲደርስ ዝም ተብሏል።
  • በደብረ ሊባኖስ ገዳም የነበሩት ጥንታውያኑ የብሉይ እና የሐዲስ ትርጓሜ አብነት ት/ቤቶች በበጀት እጥረት በሚል ሰበብ በጸብአቴ ኃይለመስቀል መሳሪያነት ሲዘጋ ዝም ብለናል።
  • የአሰቦት ገዳም ከአንዴም ሦስት ጊዜ በእሳት ሲቃጠል ገዳማውያኑ በሰላም ከአምላካቸው የሚገናኙበት ቦታ እንዳይሆን በጥይት፣ በእሳት ጉዳት ሲደርስ ዝም ብለናል።
  • በደብረ ሊባኖስ ገዳም ዙሪያ በሰፈሩ የሙስሊም ወገኖቻችን በገዳማውያኑ ላይ ብዙ እንግልት እና ድብደባ ሲያደርሱ ቤተክርስቲያንም ሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ዝም እኛም ዝም።
  • በዝቋላ አቦ ገዳም አካባቢ ተመሳሳይ የእሳት እና የተለያየ ማስፈራሪያ ሲደርስ ቤተክህነቱም ሆነ ህዝበክርስቲኑ ያሰማው ድምጽ የለም ዝምታ ብቻ።
  • በጎንደር ቀደምት የነበሩት የንባብ፣ የድጓ፣ የትርጓሜ አብነት ት/ቤቶች በአውላላ ሜዳ በእሳት ሲጋዩ ሁሉም ዝም መንግስትም፣ ቤተክርስቲያንም፣ ሕዝቡም ዝምታ ብቻ።  
  •  ዛሬ በርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን እንሰራለን እየተባለ እላይ ታች የሚባልለት ቤተ-መጻሕፍት ወመዘክር እውነት አላማው ምንድነው? ለቤተክርስቲያን ታስቦ ነው ወይስ ለግል ጥቅም? አላማው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙትን የሃይማኖታችን አሻራ የሆኑትን ንዋየ ቅዱሳት በአክሱም ወስዶ ለምን? እውነት ግማደ መስቀሉ ከግሸን ደብረ ከርቤ ተነስቶ ወደ አክሱም፣ በጎንደር የሚገኙት እጹብ እና ድንቅ የሚባሉት የሃይማኖታችን ምልክቶች እና የታሪካችን መገኛዎች ወደ አክሱም? በጎንደር የሚገኙት በጎንደር ላይ ቤተ-መጻሕፍት ወመዘክር ለምን መሰራት አይችልም፣ በግሸን ደብረ ከርቤስ ለምን ሌላ መስራት አይቻልም በአንድ ቦታ ወስዶ ማስቀመጥ ለሌላ አላማ ካልሆነ እውነት ለሃገር እና ለቤተክርስቲያን ማሰብ አይመስለንም ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሁንም ዝም።
  • በምዕራብ ወሎ በጸበል ቤቶች ውስጥ የደረሰው ግድያ፣ በጥምቀት ወቅት ታቦተ ሕጉን ተሸክመው በሚሄዱ ካሕናት እና ምዕመናን ላየ የደረሰው የድንጋይ እሩምታ ዝምታ ብቻ።
  • በወልቂጤ አካባቢ በሙስሊም ጽንፈኞች የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን ስትቃጠል ሕዝበ ክርስቲያኑ ሲሰደድ እና በመንግስት ሃይሎች ሲደበደብ እና እንግልት ሲደርስበት ዝም።
  • በጅማ ሀገረ ስብከት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አይተናል፣ ሰምተናል መልስም የለም ለምን ብሎ የጠየቀም የለም ዝምታ፡፡
ልበ አምላክ ቅድስ ዳዊት እንደተናገረው
". . . ሕግህን አልጠብቅሁምና የውኃ ፈሳሽ ከዓይኖቼ ፈሰሰ፥ አቤቱ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ፍርድምም ቅን ነው። ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥ እጅግም ቅን ነው፥ ጠላቶቼ ቃልህን ረስተዋልና የቤትህ ቅንዓት አቃጠለኝ። ቃልህ እጅቅ የጠነከረ ነው፥ ባሪያህም ወደደው።. . ."
መዝሙረ ዳዊት ፻፲፱ ፥ ፻፴፮ - ፻፵

የክርስቶስ ቤተሰቦች የተዋሕዶ ልጆች እናቶች፣ አባቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶች ዛሬ ቤተክርስቲያናችን ላይ ትልቅ ፈተና ተጋርዶባታል የእኛተታችን ታሪክ ሊቀይሩ ሊያጠፉ እና እኛንም ወደ አልተፈለገ የሃይማኖት ትንቅንቅ ላይ እንድንገባ እየዳረጉን እና ጥርጊያውን እያዘጋጁልን ይገኛሉ፣ ዝምታችን ግን በጣም አስደንጋጭ እና አሳዛኝ ነው  እስቲ ከዋልድባ ገዳም ተወክለው ከመጡት ጥቂት አባቶች ዘንድ በራሳቸው አንደበት ምን እንደተባሉ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኮሚኒኬሽን ተወካይ ተብየው ሁለቱንም አዲሱ አበበ ከVOA ቃለ  ምልልስ አድርጎላቸው ነበር ተከታተሉት
ቸር ያሰማን አሜን
 

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment