Thursday, March 29, 2012

በዋልድባ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ውይይቶች ቀጥለዋል


  • ሰላማዊ ሰልፎች ማድረጉ ይቀጥላል።
  •  “ሥር ነቀል የምእመናን እንቅስቃሴ ነው የሚያስፈልገው” ከተሳታፊ ምእመን
  •  ምእመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው መቆም ያለባቸው ጊዜ ላይ መደረሱ ተወስቷል፡፡
  • “ሁላችሁንም በእግዚአብሔር ስም አንድ ነገር እለምናችኋለሁ። ከዘረኝነት ራሳችንን እናጽዳ። ዘር ለዱባና ለድንች እንጂ ሁላችን ከአንድ ከክርስቶስ ከማይጠፋው ዘር የተወለድን ነን”
ዘገባው የደጀ ሰላም ነው::


በዋልድባ እና በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ህልውና ጉዳይ የተቀሰቀሰው ቁጣ በሕዝባዊ ውይይቶች ታጅቦ እየቀጠለ መሆኑን የሰሜን አሜሪካ ምንጮቻችን ገልጸዋል። በመላው የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በስልክ ኮንፈረንስ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ እያደረገ ባለው በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ የምእመናን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን ተሳታፊዎቹም ስለ ዋልድባ ይዞታ መደፈር ወይም ስለ ዝቋላ እና አሰቦት ገዳማት የእሳት አደጋ ብቻ ሳይሆን “በጠቅላላው ስለ ቤተ ክርስቲያን ህልውና ነው መነጋገር ያለብን” ወደሚለው ገዢ ሐሳብ በመምጣት ላይ ናቸው ተብሏል።



በዚሁ በፈቃደኛ ምእመናን በተጠራው እና በልባቸው በየቤታቸው ሲቃጠሉ የነበሩ ምእመናንን እየቀሰቀሰ በመጣው የስልክ-ጉባኤ አያሌ መሠረታዊ ጥያቄዎች በመነሣት ላይ ናቸው። “እኔ ምንም የሌለኝ አንድ ደካማ ሰው ነኝ” ሲሉ የጀመሩ አንድ ምእመን እንዲህ አሉ። “ስለ ዋልድባ ጉዳይ የአካባቢው ባለሥልጣን ሲናገሩ ሰምቻለኹ። መነኮሳቱም ሲናገሩ ሰምቻለኹ። እንግዲህ ይህ ገዳም ለሁለት ሺህ ዓመት የቆየ ነው። እንዲያው ምንም ችግር ከሌለ እንዴት ገዳማውያኑ እስከ አዲስ አበባ፣ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ ለመሔድ ይነሣሉ?” ሲሉ ተጠየቃዊ ሐሳብ አቅርበዋል። አክለውም “እኔ ስለዋልድባ ብቻ አይደለም የምናገረው። ከዚህ በፊት አኩሱም ላይ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ከዚያ ሰው ሞተ። የሚገርመው ገዳዩ ማን ነው ሳይባል ሁከቱን የቀሰቀሰው ማን ነው? ይቅርታ ይጠይቅ የሚል ነገር ተነሣ። ይህ መንግሥት (ኢሕአዴግ) ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ሀሳብ መጠየቅ አለብን። በዚህ በ20 ዓመት ውስጥ የሌሎች እምነቶች ንብረቶች እንዲህ ሆኑ ሲባል ሰምቼ አላውቅም። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብቻ ነው የሚጠፋው። የሚቃጠለው። ይህ እኮ ሕጋዊ ጥያቄም ነው። መንግሥት ለእምነቶች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ አለበት። ለዜጎች። የዋልድባ መነኮሳት ከተማን ሸሽተው፣ ዓለምን ንቀው ነው የሄዱት። ለከተማ ለከተማማ በየከተማው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት መኖር ይችሉ ነበር እኮ። እነርሱም ዜጋ ናቸው። መንግሥት ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል” ሲሉ ልብ የሚነካ ንግግር አድርገዋል።

“ሥር ነቀል የምእመናን እንቅስቃሴ ነው የሚያስፈልገው” ያሉ ሌላ ተናጋሪም ኮፕት ቤተ ክርስቲያንን በአብነት በመጥቀስ ምእመኑ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት፣ አባቶችን ብቻ በመጠበቅ ጊዜው እንዳያልፍበት፣ እስካሁን ጠብቆ ምንም ያገኘው ነገር አለመኖሩን፣ በመላው ዓለም ያሉ ኦርቶዶክሳውያን በአንድነት በመነሣት ቤተ ክርስቲያናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው አስረድተዋል። “ስደተኛ፣ ገለልተኛ፣ በአገር ቤት አስተዳደር ስር ያለ እያልን ተበታትነን ቀረን። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ፖለቲካ እየሠሩ ነው። እኛ እነርሱን ተከትለን መጥፋት የለብንም” ካሉ በኋላ “አሁንም በፍፁም ንጽህና ፣ በንፁህ ልብ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ መሥራት አለብን። ፖለቲከኞች አሁን እኛን ተዉን። ፖለቲካችሁን ሌላ ቦታ ውሰዱ። እኛ የምንሠራው ለቤተ ክርስቲያን ነው” ብለዋል።

አክለውም “ሁላችሁንም በእግዚአብሔር ስም አንድ ነገር እለምናችኋለሁ። ከዘረኝነት ራሳችንን እናጽዳ። ዘር ለዱባና ለድንች እንጂ ሁላችን ከአንድ ከክርስቶስ ከማይጠፋው ዘር የተወለድን ነን” ሲሉ በሰሜን አሜሪካ ትልቅ በሽታ የሆነውን የዘረኝነትን ጉዳይ በቀጥታ አንሥተዋል።ሌሎች ተናጋሪዎችም በይዘት ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ብዙ ሐሳብ ጠቅሰዋል።

ጉባኤው በዚሁ ቀጥሎ ሰላማዊ ሰልፎችን መቀጠል እንደሚገባ፣ በየአካባቢው የምእመናን አስተባባሪ ኮሚቴዎችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ሁሉ ችግር በእግዚአብሔር ቸርነት ይወገድ ዘንድ እና የተጀመረው እንቅስቃሴም ፍሬ እንዲያፈራ የምሕላ ጸሎት መደረግ እንዳለበት፣ ጊዜያዊ ችግር ያለባቸው ለዝቋላ እና ለደብረ አሰቦት ዓይነት ገዳማት የተጀመረው ርዳታ ማስተባበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በረዥም ጊዜም ዓለም አቀፍ የሆነ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ፋውንዴሽን መቋቋም እንዳለበት የቀረበው ሐሳብ በዓላማነት ተቀምጧል።

ይኸው የምእመናን መነሣሣት እና ሕዝባዊ ውይይት በሌሎች አህጉሮች ማለትም በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ እና በአረብ አገሮች ወዘተ ባሉ ምእመናን ዘንድም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

1 comment:

  1. egziabher yirdan! lepoletikegnoch degmo libona yistachew!

    ReplyDelete