Friday, March 23, 2012

“እሳት በመንደርም ይነሣል፤ በቤተ ክርስቲያን ሲሆን ለምን ይገናል?” (የጠ/ ቤተ ክህነቱ መግለጫ)


(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 14/2004 ዓ.ም፤ ማርች 23/2012. READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ሁሉም ሓላፊዎች በዋልድባ ገዳማት፣ በአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴ ወአባ ሳሙኤል ገዳም እና በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከተፈጠረው ችግር ጋራ በተያያዘ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምላሽ ተመጣጣኝና ፈጣን እንዳልሆነ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ላይ የሚሰነዘረውን ወቀሳ በማጣጣል አስተባብለዋል፡፡
 
ንት ከቀትር በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአስተዳደር አዳራሽ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው የተመራው በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ የኋላ እሸት ነው፡፡ ከእርሳቸውም ጋራ የአጣሪ ቡድን አባላት በመሆን ወደ ዋልድባ እና ዝቋላ የተጓዙት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ እና የአስተዳደር መምሪያ ሓላፊው ቀሲስ ዮሐንስ ገብረ መስቀል፤ ወደ አሰቦት ሄደው የነበሩት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊው መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ሓላፊ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ በመግለጫው ላይ ዘገባዎቻቸውን አቅርበዋል፤ ለጥያቄዎችም ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡
“የምንመሰክርላችሁ ያየነውን ነው” ያሉት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በዋልድባ ገዳማት ጉዳይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና የገዳሙ ማኅበረሰብ ጋራ ከተደረገው ውይይትና በመስክ ከተመለከቱት ‹እውነታ› በመነሣት “ልማቱ በገዳሙ ክልል እንደማይካሄድና ገዳሙን እንደማይነካ አረጋግጠናል፤ ልማቱን እንደ ስጋት የሚያራግቡት ገዳሙን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግና ሕዝበ ክርስቲያኑን የማደናገር ዓላማ ያላቸው መነኰሳት ናቸው፤” ብለዋል፡፡ ይልቁንስ “ግድቡ ለገዳሙ ልማት ዕድል /Opportunity/ በመሆኑ የገዳማት አስተዳደሩ በዚህ ዙሪያ መሥራት አለበት፤” የሚል ማሳሰቢያም ሰጥተዋል፡፡

በብዙ ተፋልሶዎች በተሞላውና ለጋዜጠኞች አሰልቺ በነበረው በዚሁ ጋዜጣዊ ጉባኤ “የዋልድባ ገዳም ትውፊቱን ጠብቆ መሄድ አለበት፤” ያሉት ሓላፊዎቹ ከገዳማዊ ሥርዐቱና ትውፊት ጋራ የሚጋጩ ምላሾችን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ‹ልማቱ› ለገዳሙ ዕድል ስለመሆኑ ባብራሩበት ምላሻቸው፡- “ግድቡ ገዳሙን የመክበብ ቅርጽ አለው፤ ይህም የግድቡን ውኃ ለመጠቀም ያስችለዋል፤ በዚህም የዓሣ ርባታና መስኖ ልማት ያካሂዳል፤” ብለዋል፡፡

ከዘላቂ ሥነ ልማት ኀልዮት አኳያ በቂ ወይም ትክክለኛ ትንተና ያልተሠራበት የስኳር ልማቱ ግዙፍነት የአካባቢውን ተፈጥሯዊ ገጽታ፣ ማኅበረ - ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በመሠረቱ በመለወጥ የሚፈጥረው ግዙፍ የከተሜነት ተጽዕኖ ከገዳማውያኑ ጥብቅ የምንኩስና ሥርዐትና ትውፊት ጋራ የዕሴት ግጭት እንደሚፈጥር የገባቸው መነኰሳቱ ግን በደብዳቤያቸው እንደገለጹት፣ በብዙኀን መገናኛም ቀርበው እንደተናገሩት በመንግሥትም ይሁን በቤተ ክህነቱ መግለጫ እንደማይስማሙ ነው - “የተቀደሰችው የዋልድባ ገዳም ኀጢአት የማይሻገርባት፣ ዘር የማይዘራባት፣ እህል የማይበላባት ናት፡፡”

በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች መግለጫ መሠረት በ‹ልማቱ› ምክንያት የሚነሡት አብያተ ክርስቲያን ቁጥርም ሁለት መሆኑ ተገልጧል፡፡ እኒህም ቢሆኑ የገጠር አብያተ ክርስቲያን እንጂ የገዳሙ አካላት አይደሉም፡፡ በአንጻሩ በመንግሥት ሳይቀር የተነገረውና በገዳማውያኑ መግለጫ የተቀመጡት አብያተ ክርስቲያን ቁጥር አራት ነው፡፡ እኒህ አብያተ ክርስቲያን ምእመኑ ከቦታው ቃል ኪዳን የተነሣ የሚሰጣቸው ከፍተኛ መንፈሳዊ ዋጋ በሓላፊዎቹ መግለጫ ውስጥ ተገቢው ቦታ አልተሰጠውም ወይም አልገባቸውም፡፡ ከጀርመን ድምጽ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ አንድ የመንግሥት ሐላፊ “ተራ አብያተ ክርስቲያናት” በሚል ሲገልጿቸው እንደተሰሙት ማለት ነው።

የዋልድባ ገዳማትን የመጀመሪያ ዜና ከደጀ ሰላም በማግኘት ወደማጣራቱ መግባታቸውን ቢናገሩም ደጀ ሰላምን ጨምሮ፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን፣ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮንና የማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን በ‹አራጋቢነት› እና በ‹ማስጮኽ› ወንጅለዋል፡፡ በምእመናኑ ‹ይግባኝ› የተባለባቸው ሚዲያዎቹ “እነርሱ ናቸው የቤተ ክርስቲያን አሳቢዎች!!” በሚልም ተላግጦባቸዋል፡፡

ሓላፊዎቹ አቤቱታውን ለማቅረብ በመላው የገዳሙ ማኅበር ስምምነት ተወክለው ወደ አዲስ አበባ የመጡትንና በእኒህ ሚዲያዎች ቀርበው ቃላቸውን የሰጡትን ተወካዮችንም “ማንነታቸውን ማወቅ አልቻልንም” ሲሉ ክደዋቸዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች የማኅበረ መነኰሳቱን ሙሉ ስምምነት አግኝተው የተላኩትን ተወካዮች እንዲህ ካሏቸው ተነጋግረናል የሚሉት ከማን ጋራ ነው? ፈጣን መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ አንዱ የሆኑትና “እውነተኛ መነኩሴ አይደሉም፤ በገዳሙም አይኖሩም” በሚል የተዘለፉት አባት ከቀናት በፊት ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት ምላሽ ግን “የእኔ ቆብ ከመርካቶ የተገዛ አይደለም፤ እውነተኛ መነኩሴ ነኝ፤ ያመነኮሱኝም አባት በገዳሙ ይገኛሉ፤ በማኅበሩ የተላኩት ጥያቄውን አድርስ ተብዬ ነው፤ ለሚዲያም የተናገርኹት ሃይማኖቴ አስገድዶኝ ነው፤” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህንኑም ቃላቸውንም መምህር አባ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ የገዳሙ የቀድሞ አበምኔት አረጋግጠዋል፡፡

በአሰቦት ገዳም በቃጠሎ የደረሰውን ጉዳት የማኅበረ ቅዱሳን ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ “ተቃጠለ ብሎ በመሥራት አጩኾታል” ያሉት አንድ ሓላፊ “ችግሩን ለመፍታት ቀድመን ወደ ስፍራው ሄደናል፤” ብለዋል፡፡ በቅርቡ በገዳሙ መንፈሳዊ ትምህርት የሚከታተል የሰባት ዓመት ልጅ በአካባቢው ታጣቂ ጎሳዎች መገደሉንም አስታውሰዋል፡፡ ከአፋር፣ ከሶማሌ እና ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ጋራ በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸውንና በአካባቢው የሚታየው የጎሳዎች የርስ-በስ ግጭት ለክልሎቹም አሳሳቢ መሆኑን ጠቅዋል፡፡

ገዳሙን ለቃጠሎም ይሁን ለእንዲህ ዐይነቱ የግፍ ግድያ ያጋለጠው ከዐፄ ኀይለ ሥላሴ ጀምሮ ለገዳሙ ይደረግ የነበረው ቋሚ የፖሊስ ጥበቃ ባለመኖሩ በመሆኑ ወደፊት የጋራ ግብረ ኀይል ተቋቁሞ ለገዳሙ ቋሚ የፖሊስ ኀይል በሚመደብበት ሁኔታ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ ጋራ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ጉዳይ በዕለቱ በተሸጠው መግለጫ ላይ ነጭ ውሸት ሆኖ የተገኘውና “ለችግሮቹ ሁሉ ቀድመን ተገኝተናል” የሚለውን የቤተ ክህነቱን መቃወሚያ የሚያስተባብለው የዝቋላ ገዳምና አካባቢው እሳት በደጀ ሰላም ቀዳሚ ዜና እንደተገለጸው መጋቢት ስምንት ሳይሆን መጋቢት 10 ነው መባሉ ነው፡፡ በአሰቦት ገዳም የካቲት 20 ቀን የጀመረው ቃጠሎ ለሁለተኛ ጊዜ በተደገመበት የካቲት 23 ቀን በመድረሳቸው “ቀድመን ተገኝተናል” እንዳሉት ሁሉ!!

ቢደርሱስ ይህ ነው የሚባል የገቢ ምንጭ ከሌለው ከዚሁ ገዳም አበል መጠየቅስ በመሠረቱ አግባብ ነውን? እነርሱ አበል ከጠየቁ በበጎ ፈቃድ (በራሳቸው ወጭ) በእግርም በተሽከርካሪም ገስግሰው መጥተው ቃጠሎውን እናጠፋለን ሲሉ የእሳት እና የኢሳዎች ጥይት ራት ሊሆኑ የነበሩት ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ምን ይከፈላቸዋል?!

ለማንኛውም የዝቋላው ቃጠሎ የተነሣበት ቀን መጋቢት 10 ነው መባሉ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊዎች መጋቢት 11 መሄዳቸውን ምክንያታዊ ለማድረግና ዘግይታችኋል ከሚለው ተወቃሽነት ለመዳን ታስቦ ይመስላል - ማስተባበያቸው ከእነርሱ ጉዞ አራት ቀናት አንሥቶ የወደመውን ሀብት ባይመልሰውም!!

የዝቋላን ቃጠሎ ለማጥፋት ለአየር ኀይሉ የሄሊኮፕተር ርዳታ ጥያቄ ማቅረባቸውን የተናገሩት ሓላፊዎቹ፡- ሄሊኮፕተሮች ለሌላ ግዳጅ መሰማራታቸው፣ ሄሊኮፕተሮቹ ቢኖሩም ለዚህ ዐይነቱ የቃጠሎ መከላከል ተግባር የተዘጋጁ አለመሆናቸውንና ቃጠሎውን ለማጥፋት የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች አለመኖራቸውን፣ ከዚህ ቀደም የተከሠቱትን ተመሳሳይ ችግሮች ለመከላከል የተቻለው ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት በተደረገው እገዛ መሆኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሐላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቃጠሎው በሰው ኀይል (በምእመናን፣ በኦሮሚያ ፖሊስ፣ በፌዴራል ፖሊስ) ርብርብ ለመከላከል እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ማለፊያ! ቃጠሎውን አስመልክቶ ከሓላፊዎቹ ንግግር በእጅጉ የሚነካውና ጆሮን ጭው የሚያደርገው ግን “እሳት በመንደርም ይነሣል፤ በቤተ ክርስቲያን ሲሆን ለምን ይገናል?” የመባሉ እብሪት ነው !!! አንቶኒ ደምሴ የተባሉ የፌስቡክ ፀሐፊ እንዳሉት “ታዲያ ይህ ኮሚቴ አጣሪ ወይስ አደናጋሪ” ኮሚቴ? 
 

ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment