Sunday, March 25, 2012

መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም. ነገ march 26, 2012 ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊትለፊት


የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ!


ዋልድባ ገዳም በሰሜን ኢትዮጵያ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር ወይም በአሁኑ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ የሚገኝ በመጀመሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ የስደት ዘመን በእርሱ በራሱ የተባረከና በኋላም 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእርሱ በጌታ መሥራችነት የድንጋይ ቆብ ቀርጾ ባመነኮሳቸው መነኮሳት አፅናነት የተመሰረተ ታላቅና ታሪካዌ ገዳም ነው፡፡እመቤታችን ከልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመዋዕለ ስደት ወቅት በኪደተ እግር ከረገጧቸው መካናት አንዱ ሲሆን፣ የእመቤታችን ስም የሚያመሰግኑ ቅዱሳን እንደ አሸን የሚፈሉበት ቦታ መሆኑንም ለእመቤታችን ትንቢት የተናገረው እዚሁ ገዳም ነው፡፡
ይህ ገዳም በስፋቱ፣በመነኰሳት ብዛቱ፣በፍጹማን ባሕታውያን መሸሸጊያነቱ፣ ለስዉራን ቅዱሳን መናኸርያነቱ፣ በበረሃነቱና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ታላቁ ገዳም ሲሆን፣ በዓለም ደረጃም ሲታይ ከግብጹ አስቄጥስ ገዳም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ የቅዱሳን በአት ነው፡፡በአሁኑ ሰአት የተሰወሩ ቅዱሳንን ሳይጨምር 3000 በላይ መነኰሳት በቋሚነት ለመላው ዓለምና ለአገራቸው ቀን ከሌሊት ስብሐት ወአኮቴት ወደ አምላካቸው የሚያቀርቡበት ቦታ ነው፡፡

በዚህ ገዳም እልፍ አእላፍ የተሰወሩ መናንያን እንዳሉ በአንድ ወቅት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ስለተሰወሩ መነኮሳት ተጠይቀው የሰጡትን ማንሳቱ በቂ ነው፡፡እንዲህ ነበር ያሉት፤ "ግብፅ ውስጥ የማይታወቅ (የተሰወረ) መነኩሴ በአሁኑ ጊዜ የለም፤ ኢትዮጵያ ብትሄዱ ግን ብዙ የተሰወሩ መናንያንን ታገኛላችሁ" ነበር ያሉት፡፡እነዚህ የዋልድባ መነኰሳት የሚመገቡት ጌታ የባረከላቸውን በቀን አንድ ጭብጥ ቋርፍ ሲሆን፣ የዓመት ልብሳቸውንም የሚሸፍኑት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ከሚያገኙት ስጦታ ነው፡፡ ታዲያ በዓይን የማይታይ ምግብ ይሁን እንጂ ሰማያዊውን ምስጋና እየተመገቡ ፀባ አጋንንቱን፣ ግርማ አራዊቱን በተለይም አንድ ቀን ለመዋል እንኳ የሚከብደውን ያን ከባድ የበረሃ ዋዕይ ታግሰው ለራሳቸውና ለዓለም ድህነትን ( ይዋጣል) ሲለምኑ ኖረዋል ፣እየኖሩም ነው፣ይኖራሉም፡፡
የዋልድባ ገዳም እንዲህ በቀላሉ ዘርዝረን የማንጨርሰው ብዙ ታሪክና ቃልኪዳን ያለው ቦታ ነው፡፡ጌታም ዋልድባን "እህልና ኃጢያት አይሻገርብሽ"ብሎ ለመናንያን መጠጊያና የምስጋና ማቅረቢያ ቦታ እንድትሆን ምግባቸውም መራራው ጣፋጭ እንዲሆን በቦታው ተገኝቶ ባርኮላቸዋል፡፡በዚህም ምክንያት ላለፉት እስራ ምእት (2000 ዓመታት) ለገዳሙ መነኰሳት ምግብነት ከተፈቀደው የሙዝ ተክል ውጭ ምንም አይነት እህል መሬቱን ሳይደፍር ቃልኪዳኑ ተጠብቆ እስካሁን ቆይቷል፡፡


እንግዲህ በዚህ ገዳም ላይ ነው መንግሥት የሰሜን ተራሮችን አቋርጦ የሚሄደውን የዛሪማን ወንዝ በመጥለፍ ለስኳር ፋብሪካ ግባት የሚሆን የሸንኮራ አገዳ ሰብል ለማልማትና የተወሰነውን ደግሞ በፓርክነት ከልሎ ለመጠቀም ሥራውን የጀመረው፡፡ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ በግሬደር የቅዱሳን አፅም እየፈለሰ መሆኑ ነው፡፡ 2000 ዓመታት ተከብሮ የቆየ ገዳም ነው እንግዲህ እንዲህ አይነት አደጋ የተጋረጠበት፡፡ አባቴ ዱሮ ሲተርት " ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ "ይል ነበር፡፡ 

ጎበዝ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶና ጠግቦ ነው ወይ እያደረ ያለው፡፡ኢትዮጵያዊ እኮ ሃብቱ ሳይሆን እምነቱና ባህሉ፣ የአባቶቹ ጸሎት ነው እያኖረው ያለው፡፡አመንም አላመንም የእኛ በሰላም ውሎ ማደር፣ ጤንነት ፣ኑሮ በእኛ ኃይል ብቻ የመጣ ሳይሆን እንደኛ አጥንትና ደም ሳይቆጥሩ ሌት ከቀን በሚፀልዩት አባቶቻችን ጭምር የመጣ ነው፡፡
ይህንንም መንግስት የሚያደርገውን የግዛት መጋፋት እና የሃይማኖት ማጥፋት ሥራ ለመቃወም በነገው ዕለት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ተጠርቷል። አዘጋጆቹ እንደገለጹልን የምንወክለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞችን እና ማንኛውንም ሃገር ወዳድ፣ ለቅርስ፣ተቆርቋሪ፣ ለትውፊት አሳቢ የሆኑትን በሙሉ ነው ብለውናል፣ ከቦታው በደረሰን ሪፓርት ማንኛውም ያፖለቲካ ድርጅት እንደኢትዮጵያዊነቱ ሊሳተፍ ይችላል፥ ነገር ግን እንደ አሁን ቀደሙ ከመንግስት ጋር ተሰዳድቦ እና ጮሆ መመለስ የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑ ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ልጆች ገልጸውልናል። በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችንን እንዳይዘነጋ ብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈውልናል።
በነገው ዕለት በሚደረገው ትዕይንት ላይ በቁጥር ከ500 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያየ ስቴት የሚመጡ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ገልጸውልናል፣ በተያያዘ ዜና በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ቤት ፊትለፊት ተመሳሳይ ሕዝባዊ ሰልፍ እንደተጠራ ዘግይቶ ደርሶናል፣ በኒውዮርክ አካባቢ የምትገኙ ወገኖችም በተመሳሳይ ሁኔታ በኒው ዮርክ እንድትገኙ እና ተቃውሞአችንን በአንድነት እንድናሰማ ከአካባቢው አዘጋጆች ነግረውናል።
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment