Monday, March 12, 2012

የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ለወረዳው መስተዳድር ደብዳቤ ጻፈ

 




READ THIS ARTICLE IN PDF
· ገዳሙ በውሳኔው ጸንቷል፤
· “በእኛ በኩል በዚህ ቦታ ላይ ልማት ይሰራ ብሎ መወሰን ፈጽሞ የማይታሰብና የማይታለም ነው። ቦታውም በቅዱሳን መካነ መቃብር የታጠረና የተከለለ ነው” (ገዳሙ)፤
· በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ነው፤
(ደጀ ሰላ መጋቢት 3/2004 ዓ.ም፤ ማርች 12/2012)፦ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላላቅ እና ታሪካዊ ገዳማት አንዱ ነው፤ ለግሑሳን(ፍጹማን) ባሕታውያን መሸሸጊያ፣ ለስውራን ቅዱሳን መናኸርያ፣ በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ መነኮሳት፣ መነኮሳይያት እና መናንያን መጠጊያ፣ ለምእመናኑንም መማፀኛ እና ተስፋ የሆነው የዋልድባ አብረንታንት ገዳም ለፀለምት ወረዳ መስተዳድር በጻፈው ደብዳቤ ለስብሰባ ወክሎ እንዲልክ የተጠየቀውን መቶ መነኮሳት በጾሙ ምክንያት መላክ እንደማይችል አስታወቀ፡፡

በወልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ አበምኔት በመምህር ገ/ጊዮርጊስ ገብረ አረጋዊ ተጽፎ ማይ ፀብሪ ለሚገኘው መስተዳድር ጽ/ቤት የተላከው ደብዳቤ መስተዳድሩ “መንግሥት በቅድስት ዋልድባ ገዳም ላይ በጀመረው የስኳር ልማትና ግድብ …” በተመለከተ “መናንያን እና መነኮሳት ባደረግነው ምልዓተ ጉባዔ መሠረት በአሁኑ ወቅትና ሰዓት ወደ ማይጸብሪ ወጥተን በጉዳዩ ላይ ውይይትና የመፍትሔ ሐሣብ ለማግኘት ባቀረባችሁት ጥያቄ መሠረት … በዚህ ከባድ የሆነ የሱባዔ ሰዓት ላይ መቶ መነኮሳትን ወደ ማይፀብሪ ለመላክ በጣም አስቸጋሪና አዳጋች ሆኖብናል። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ አባቶች እርጋታና በአርምሞ ላይ በመሆናቸው” ነው ብሏል።
ስለ ገዳሙ አቋምና ውሳኔም ሲያትት “ከዚህ በፊት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስገባነው ደብዳቤ በሰፊው ተገልጿል” ሲል ያስረግጣል። “አሁንም ቢሆን ዚህ አንጋፋና ታሪካዊ ገዳም ህልውናውና ክብሩ ግርማውና ሞገሱ ተጠብቆ እንዲኖር መንግሥትም ሆነ መነኮሳቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን። እኛም የዚህ ገዳም ባለቤት የነገሥታት፣ የመኳንንት ወይም የመሣፍንት ሳይሆን እራሱ ባለቤቱ መድኃኔ ዓለም የገደመው ገዳም ነው” ካለ በኋላ ቦታው “የቅዱሳን መናኸሪያ፣ የዕውራንና የግሁሳን ባሕታውያን መስፈሪያ” በመሆኑ “በእኛ በኩል በዚህ ቦታ ላይ ልማት ይሰራ ብሎ መወሰን ፈጽሞ የማይታሰብና የማይታለም ነው። ቦታውም በቅዱሳን መካነ መቃብር የታጠረና የተከለለ ነው” ብሎታል። አክሎም “ቦታውን የሚያዝበት የቦታው አስተዳዳሪ እራሱ መድኃኔ ዓለም ነው። እኛም ብንሆን በዚህ ቅዱስ ቦታ ላይ ማንኛውንም የልማት ሥራ እንዲሠራ ፈጽሞ ፈቃደኞች አይደለንም” ብሏል።
ደብዳቤ ለወረዳው መስተዳድር በአድራሻ ከተመለከተ በኋላ “ለመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጸ/ቤት” እና “ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት” ግልባጭ ተደርጓል። ገዳሙ ለጠ/ሚኒስትሩ ያስገባውን ደብዳቤ በተለመለከተ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የተጠየቁት በመ/ፓትርያርክ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ስታሊን ገ/ሥላሴ ደብዳቤው በቀጥታ ለቤተ ክህነቱ እንዳልተላከ በማውሳት “ጉዳዩ በቀጥታ አልተገለጸልንም” የሚል ሐሳብ ለማስተካለፍ መሞከራቸው ይታወሳል። ይኸው ገዳሙ ለመስተዳድሩ የላከውን ደብዳቤ ከዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ማግኘት ይቻላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስለ ዋልድባ ገዳም ሁኔታ ደጀ ሰላም አብሪውን ዘገባ ካወጣች እና አሜሪካ ድምጽ እና ሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን ተከትለው ስለ ጉዳዩ ከዘገቡ በኋላ ምዕመናን በከፍተኛ ሐዘን እና ቁጭት ላይ እንደሚገኙ ከሚደርሱን መልእክቶች የተረዳን ሲሆን በአሜሪካ አገር የሚገኙ ምዕመናን በበኩላቸው የተሰማቸውን ቅሬታ እና ተቃውሞ ለመግለጥ አሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል። መጋቢት 17 /2004 ዓ.ም (ማርች 26/2012) ከጠኋቱ 3 ሰዓት (9 ኤ.ኤም) ጀምሮ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ሰላማው ሰልፍ ላይ እንዲገኙ የሰልፉ አስተባባሪዎች በፌስቡክ ጥሪዎችን በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን በዲሲና አካባቢው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለአባሎቻቸው ጥሪውን ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በስልክ ቁጥሮች 571-224-2869 እና 703-956-0513 እንደሚገኙ ያስታወቁት የሰልፉ አስተባባሪዎች ሰልፉ የሚካሔድበት አድራሻ ኤምባሲው (3506 International Dr NW Washington, DC 20008) መሆኑን ጠቅሰው በባቡር ለሚመጡ UDC Metro Stop ሁለት ደቂቃ የእግር ጉዞ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል። በትራንስፖርት አቅርቦት መራዳት የሚፈልጉ ምዕመናን ካሉም ርዳታቸውን በደስታ እንደሚቀበሉ ገልፀው ከቨርጂኒያ፣ ከሜሪላንድ ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ከዲሲ ርዕሰ አድባራት ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢዎች ትራንስፖርት ለሚፈልጉ ሰላማዊ ሰልፈኞች መኪናዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቸር ወሬ ያሰማን

አሜን

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment