Friday, February 24, 2012

ምክር

፩፦ ምክር



          የሰው ልጅ ከልጅነት እስከ እውቀት፥ ከኲተት እስከ ሽበት ምክር ያስፈልገዋል። ጳጳስም ሆነ ካህን፥ ባዕለጸጋም ሆነ ደሀ፥ ባዕለ ሥልጣንም ሆነ ተርታ ሰው፥ ምክር የማያስፈልገው የለም። ማንም ይሁን ማን፥ በጎ ኅሊና ያለው መካሪ ከሌለው ከሚያለማው የሚያጠፋው ይበዛል። አበው፦ «መካሪ የሌለው ንጉሥ ያለ አንድ ዓመት አይነግሥ፤» ያሉት ለዚህ ነው። ከዚያ በላይ ቢነግሥ እንኳ በኃይል እንጂ በፍቅር ሊነግሥ አይችልም። እያሠረ፥ እየገረፈ፥ እያፈናቀለ፥ እየገደለ፥ ግፍ በግፍ ይሆናል።
በጎ ምክርን የሚሰማ እንዳለ ሁሉ፥ የማይሰማም አለ። ቅዱስ ዳዊት ከበጎ ኅሊና የሚመነጭ ምክር ለሰው ሕይወት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ሲናገር «ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት፥ ምስጋናውም ለዘለዓለም ይኖራል።» ብሏል። መዝ ፩፻፲፥፲። ልጁ፥ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞንም፦ «አስተዋይ ግን ምክርን ገንዘብ ያደርጋል። ምሳሌንና የተሸሸገውን ነገር፥ የጠቢባንን ቃልና ዕንቆቅልሾችን ያውቃል። . . .  ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ ለራስህ የክብር ዘውድ ለአንገትህም የወርቅ ድሪ ይሆንልሃል።» በማለት መስክሯል። ምሳ ፩፥፭-፱።


በጎ ምክር ከእግዚአብሔር በመሆኑ በታናናሾችም ሆነ በታላላቆች አድሮ ሲመክረን በማስተዋል መስማት ይገባል። ይኽንን በተመለከተ «እኔ ጥበብ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ምክርን አሳደር፤» ል ምሳ ፰፲፪ ነዩ ዳንኤል በሌሊት ምሥጢር የገለጸለትን እግዚአብሔርን ሲያመሰግን «ጥበብና ምክር ይልም ለእርሱ ነውናየእግዚአብሔር ስም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይመስገን።» ያለው ለዚህ ነው። ዳን ፪፥፳ በመሆኑም በጎ ምክር አለመቀበል በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ነው። ይንንም፦ «ሆ የቃሌን መንፈስ እነግራችኋለሁ፥ ቃሌንም አስተምራችኋለሁ። በጠራሁ ዜ አልሰማችሁምና እጄን ዘረጋሁ ማንም አላስተዋለም ነገርንም አበዛሁ አልመሳችሁልኝምምክሬንም ሁሉ ናቃችሁ ዘለፋዬንም አልተመለከታችሁም፤» በማለት ነግሮናል። ምሳ ፩፥፪።
                የጥበብ የምክርና ይል ባለቤት እግዚብሔር አዳምን «በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ ነገር ግን መልካምንና ክፉውን ከሚያሳየው ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ትሞታለህና» ሲል መክሮት ነበር እርሱ ግን «ሞትን አትሞቱም ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚብሔርም እንደምትሆኑ መልካንና ክፉውን እንደምታውቁ እግዚብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ» በሚለው በሰይጣን ምክር ተሸነፈ። በዚህም ተሰጥቶት የነበረውን ጸጋ ክብር ሁሉ አጣ ከአባቱ ከእግዚብሔር ተለየ ከርስቱም ከገነት ተፈናቀለ መርገመ መርገመ ነፍስ ወደቀበት ላይ ሞተ ነፍስ በር መቃብር ላይ ነም ተጨምሮ ተፈረደበት ዘፍ ፫፡፭-፳፬።
ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በጎ ምክርን የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን እያነጻጸረ ሲናገር፥ «ምክር በመካሮች ልብ ትኖራለች፥ ክፉ ሰው ግን ምክርን አይሰማትም።. . . ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ፥ በፍጻሜህም ጠቢብ ትሆን ዘንድ በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ። የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘለዓለም ይኖራል።. . . ምክር በሰው ልብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፥ አእምሮ ያለው ሰው ይቀዳዋል። . . . ቅጥር እንደሌላት እንደፈራረሰች ከተማ ያለምክር የሚኖር ሰው እንዲሁ ነው ብሏል።» ምሳ ፲፭፥፳፪-፳፬ ፤፲፱፥፳-፳፩፤ ፳፥፭፤ ተግ ፩፥፳፰፡፡
፩፥፩ ፦ ምክረ ኢዮናዳብ
          ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፥ የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት፥ አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እስከሚታመም ድረስ እጅግ ተከዘ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ነገር ያደርግባት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፥ እጅግም ብልህ ሰው ነበረ። እርሱም፦ «የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለምን በየቀኑ እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን?» አለው። «የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት እወድዳታለሁ፤» አለው። ኢዮናዳብም፦ «ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ ይመጣል፥ እኅቴ ትዕማር እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታበስልልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ፥ በለው፤» ሲል መከረው። አምኖንም የተመከረውን ሁሉ አደረገ። ኢዮናዳብ እንደመከረው በአባቱ ፈቃድ ልታስታምመውና ልትመግበው የመጣችውን እኅቱን፥ «ተው አይሆንም፤» እያለችው በጉልበት ደፈራት። ፈቃዱን ከፈጸመ በኋላ ግን ፈጽሞ ጠላት፤ «አስቀድሞ ካፈቀራት ፍቅር ይልቅ በኋላ የጠላት ጥላቻ በለጠ፤» ይላል። ከቤትም በዘበኛ አስጎትቶ አስወጣት፤ «ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት፤» አለው። ዘበኛውም የተባለውን አደረገ። ትዕማርም አመድ ወስዳ በራሰዋ ላይ ነሰነሰች፥ ብዙ ኅብር ያለውን ልብሰዋንም ቀደደችው፥ እጅዋንም በራሰዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች። ምንም እንኳ የክፋቱ ምንጭ አምኖን እራሱ ቢሆንም ገፋፍቶ ለዚህ ያደረሰው የወዳጁ የኢዮናዳብ ምክር ነው፡፡
          አቤሴሎም በእኅቱ ላይ የደረሰውን ሰምቶ ከልቡ ቢጠላውም፥ የሆዱን በሆዱ ይዞ (ቂም ቋጥሮ)  አምኖንን ክፉም ሆነ መልካም አልተናገረውም። ንጉሡ ዳዊትም ይህንን ነገር ሰምቶ እጅግ ተቆጣ፤ ነገር ግን የበኵር ልጅ (አልጋ ወራሽ) ነበርና ስለወደደው የልጁን የአምኖንን ነፍስ (ሰውነት) አላሳዘነም። አቤሴሎምም ለሁለት አመታት ቂም ቋጥሮ ከቆየ በኋላ በምክንያት ታላቅ ድግስ በቤቱ ደገሰ፤ ድግሱም እንደ ቤተመንግሥት ድግስ ነበር፡፡ አባቱንም በግድ አስፈቅዶ አምኖንን በድግሱ ላይ እንዲገኝ አደረገ። አገልጋዮቹንም፦ «አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ፡- አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁ ጊዜ ግደሉት፡፡ አትፍሩም፥ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝና፥ በርቱ፥ ጽኑም።» ብሎ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም የተባሉትን በአምኖን ላይ አደረጉ፥ አቤሴሎምም ኮበለለ። ንጉሡም ይህንን ሰምቶ ልብሱን ቀደደ። በምድር ላይም ወደቀ፥ እጅግ ታላቅ ለቅሶም አለቀሰ። ፪ኛ ሳሙ፲፫፥፩-፴፮፡፡
          የአንድ የኢዮናዳብ ክፉ ምክር ስንት ነገር እንዳጠፋ ተመልከቱ! ብልህነቱን ለክፋት በመጠቀሙ፥ በፍቅር የኖረውን ቤተሰብ ደም እንዲፋሰስ አደረገው። ንጉሡም ቢሆን አምኖንን ምን ቢወድደው ስለ ክፉ ሥራው መቅጣት ነበረበት። እግዚአብሔር በእስራኤል ዙፋን ያስቀመጠው ለማንም ሳያደላ አስተካክሎ እንዲፈርድ መሆኑን መርሳት አልነበረበትም፡፡ ንጉሡ ዳዊት ለአምኖን ቢያደላም ልጁን ከሞት አላዳነውም። ትናንትም ሆነ ዛሬ ብዙ ባለሥልጣኖች ቤተሰቦቻቸው፣ የሥጋ ዘመዶቻቸው፣ ዘሮቻቸው፣ ባልንጀሮቻቸው፣ ምን ቢያጠፉ እርምጃ አይወስዱባቸውም። በሌላው ግን ውሃ በቀጠነ ወይም በዓላማ ከእነርሱ ጋር ስላልተሰለፉ ብቻ በእስራትም በሞትም ሲቀጡ ይታያሉ። በዚህ ዓለም በክፉ ምክራችን የሰውን ሕይወት ወደ ኃጢአት የምንገፋ ብዙ ኢዮናዳቦች፥ ከክፉ መካሪ ጋር የምንኖር ብዙ አምኖኖች፥  ቂም ቋጥረን ሰላማዊ መስለን የምንታይ ብዙ አቤሴሎሞች እንዳለን የዕለት ዕለት ሥራችን ያሳብቃል። የዳኝነቱም ነገር ከምድር ላይ ፈጽሞ ጠፍቷል የሚያስብል ደረጃ እየደረሰ በመምጣቱ እርም አውጥቶ መቀመጡ የተሻለ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሥጋውያን ዳኝነትን ሲያጣ በእግዚአብሔር ያስፈርዱልኛል ብሎ ወደ መንፈሳውያን ይሄዳል። ከሥጋውያኑ በባሰ ኹኔታ ከመንፈሳውያኑ  ፍርድ ሲያጣ ግን የት ይደርሳል?
፩፥፪፦ ምክረ ኢኪጦፌል፤
          ኢኪጦፌል የንጉሥ ዳዊት አማካሪ ነበር። በዚህም ምክንያት የንጉሡ ምሥጢረኛ ሆኖ በነገር ሁሉ አይለየውም ነበር። ክፉ ቀን በመጣ ቀን ግን ንጉሡን ካደው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሁልጊዜ የሚቆሙት ከጥቅማቸው ጋር እንጂ ከእውነት ጋር አይደለም። በመሆኑም፦ «ድሮውንም እኔ አምኜበት አይደለም፥ ለእንጀራዬ ስል ነው።» እያሉ አዲስ ከመጣው ጋር ይለጠፋሉ፡፡ ትናንት ሲመርቁት የነበረውን ዛሬ ይረግሙታል፥ ትናንት ሲረግሙት የነበረውን ደግሞ ዛሬ ይመርቁታል። ዓላማቸው እውነት ስላልሆነ ለመገለባበጥ ችግር የለባቸውም።
          የአኪጦፌል ክዳት የተገለጠው፥ አቤሴሎም አባቱን ዳዊትን ባሳደደው ጊዜ ነው። አቤሴሎም ከሦስት ዓመታት ስደት በኋላ በኢዮአብ አማላጅነት በአባቱ ምሕረት ቢመለስም ልቡ ከክፋት አልጸዳም ነበር። ከማለዳ ጀምሮ ከቤተመንግሥቱ ደጃፍ ቆሞ፥ ከንጉሡ ዳኝነት ለማግኘት ደጅ የሚጠኑትን ሰዎች፥ «ነገርህ መልካም ነው፥ ቀላልም ነው፥ ነገር ግን ከንጉሡ ዘንድ የሚሰማህ የለም። . . . ነገርና ክርክር ያለው ሁሉ ወደ እኔ ይመጣ ዘንድ፥  ቅንም ፍርድ እፈርድለት ዘንድ በሀገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?» እያለ ልባቸውን ይማርክ፥ እጁንም ዘርግቶ አቅፎ ይስማቸው ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላም «ለእግዚአብሔር የተሳልኩትን ስእለት በኬብሮን አደርግ ዘንድ ልሂድ፡፡ . . . እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ቢመልሰኝ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርባለሁ ብዬ ስእለት ተስዬ ነበር።» ብሎ በእግዚአብሔር ስም ዋሸ። በአባቱ ፈቃድ ከሔደ በኋላ ግን በኬብሮን «ነገሥኩ፤» ብሎ መለከት አስነፋ፡፡ ህዝቡም ዳዊትን ከድተው ከአቤሴሎም ጋር ሆኑ፥ አኪጦፌልም የሴራው ተባባሪ ሆነ፡፡
ንጉሡ ዳዊት ቤተሰቡን እና ታማኞቹን ይዞ ሸሸ፥ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበትም ወጣ፥ ሲወጣም ያለቅስ ነበር፥ ራሱን ተከናንቦ ያለጫማ ይሔድ ነበር፥ የሚወዱትም እያለቀሱ ተከተሉት። አኪጦፌል በሴራ ከአቤሴሎም ጋር አንድ መሆኑንም ለዳዊት ነገሩት። አቤሴሎም አኪጦፌልን፦ «ምን እንደምናደርግ ምከሩ፤» ቢለው፥ «ቤት ሊጠብቁ ወደተዋቸው ወደ አባትህ ቊባቶች ግባ፥ እስራኤል ሁሉ አባትህን እንዳሳፈርኸው ይሰማሉ፥ ከአንተም ጋር ያሉት ሁሉ እጃቸው ይበረታል።» ብሎ መከረው። አቤሴሎምም እንደተመከረው በእስራኤል ሁሉ ፊት አስነዋሪ ሥራ ሠራ። በእነዚያ በመጀመሪያው ወራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደመጠየቅ ነበር።  የአኪጦፌል ምክር አስነዋሪ ሥራ አሠርቶ ዳዊትን በማዋረድ ብቻ አላበቃም። «አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ልምረጥና በዚህች ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን ላሳድድ። ደክሞና እጁ ዝሎ ሳለ እወድቅበታለሁ፥ ንጉሡንም ብቻውን እገድለዋለሁ። ሙሽራው ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ሕዝቡንም ሁሉ ወደአንተ እመልሰዋለሁ፥ የአንድን ሰው ሰውነት ብቻ ትሻለህና፥ ለሕዝቡ ሁሉ ግን ሰላም ይሆናል።» ብሎ በነፍሱም ላይ መከረበት። ነገሩም በአቤሴሎም ፊትና በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት ደስ አሰኘ። በክፉ ቀን ሽማግሌም አይገኝም። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦ «ወጣት ወደ ሽምግልና ዕድሜ ደረጃ ሲደርስ፥ ሽማግሌ ሊሠራ የሚገባውን ሥራ ይወቅ፥ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሠራሁትን ኃጢአቴን ይቅር በለኝ ብሎ ይጸልይ፥  አለበለዚያ ሽማግሌ ይባል ዘንድ አይገባውም፤» ያለው ለዚህ ነው። ይህ ዓለም እንዲህ ነው፥ እምነት አይጣልበትም፥ ክፉ ቀን አይምጣ እንጂ ሁሉም ጠላት ነው፥ ከተመቸው ለነፍሳችንም አይሳሳም፥ እኛም እንዲሁ ነን፥ ቀን ዘንበል ያለበትን አንምረውም፥  የትናንት ወዳጅነታችን ፈጥኖ ይረሳል፥ «እግዚአብሔርስ ምን ይለናል?» አንልም። ፪ኛ ሳሙ ፲፭፥ ፩-፴፯፤ ፲፮፥፩-፳፫፤ ፲፯፥፩-፬።
፩፥፫፦ ምክረ ኲሲ፤
ኲሲ፥ የአኪጦፌልን ምክር ከንቱ ያደረገ የዳዊት ወዳጅ ነው። ንጉሡ ዳዊት፦ ለእግዚአብሔር ወደ ሰገደበት ተራራ ራስ በመጣ ጊዜ፥ ወዳጁ ኲሲ ልብሱን ቀደደ፥ በራሱም ላይ ትቢያ ነስነሶ ሊገናኘው መጣ፡፡ «ከእኔ ጋር ብትሻገር ሸክም ትሆንብኛለህ፥ ወደ ከተማ ግን ተመልስህ ለአቤሴሎም፦ ወንድሞችህ፥ ንጉሡም መጡ፤ እነሆ በኋላዬ ናቸው። ንጉሥ ሆይ፥ አገልጋይህ ነኝ፤ አስቀድሞ ለአባትህ አገልጋይ ነበርሁ፥ እንዲሁ አሁንም  ለአንተ አገልጋይ ነኝ፥ ተወኝ ልኑር፥ ብትለው የአኪጦፌልን ምክር ትለውጥልኛለህ። እነሆ ካህናቱ ሳዶቅና አቢታርም በዚያ ከአንተ ጋር ናቸው። ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ንገራቸው። እነሆ፥ የሳዶቅ ልጅ አኪማኦስና የአብያታር ልጅ ዮናታን ልጆቻቸው በዚያ ከእነርሱ ጋር አሉ፥ የምትሰሙትን ሁሉ በእነርሱ እጅ ላኩልኝ።» አለው። ኲሲም ለዳዊት ብሎ ከኢየሩሳሌም እንደወጣ፥ ለዳዊት ብሎ ወደ ከተማ ተመለሰ። ፪ኛ ሳሙ ፲፭፥፴፪-፴፯። ሳዶቅና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ይዘው ከንጉሡ ጋር ለመሰደድ ተነስተው ሳለ፦ «የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ከተማ መልሱ፥ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ አግኝቼ እንደሁንሁ፥ መልሶ እርሷንና ክብሯን ያሳየኛል፥ ነገር ግን አልወድህም ቢለኝ፥ እነሆኝ በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ያደርግብኝ።» ብሎ የመለሳቸው እርሱ ነው ፪ኛ ሳሙ ፲፭፥፳፬-፳፱፡፡
          አቤሴሎም የአኪጦፌልን ምክር ከሰማ በኋላ፦ «አርካዊውን ኲሲን ጥሩት፥ ደግሞም እርሱ የሚለውን እንስማ፤» አለ። ኲሲም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ፦ «አኪጦፌል ያለው ይህ ነው፥ ነገሩን እናደርገው ዘንድ ይገባልን? ባይሆን ግን አንተ ንገረን፤» አለው። ኲሲም አቤሴሎምን፦ «አኪጦፌል በዚህ ጊዜ የመከራት ምክር መልካም አይደለችም፥ ይህቺውም አንዲት ናት፡፡ . . . በሜዳ እንዳለች አራስ ድብ እና እንደ ተኳር የዱር እርያ በልባቸው መራሮችና ኃያላን መሆናቸውን አባትህንና ሰዎቹን ታውቃለህ። አባትህ አርበኛ ነው፥ ሕዝቡንም አያሰናብትም።  በተራራው ላይ፥ ያም ባይሆን በአንድ ቦታ ተሰውሮአልና ከእነርሱ ፊተኞች ቢወድቁ የሚሰማው ሁሉ አቤሴሎምን የተከተለ ሕዝብ ተመታ ይላል፡፡ እርሱ ኃይለኛ ሰው ነውና፥ ልቡም እንደ አንበሳ ልብ ፈጽሞ ይናደዳልና፤ እስራኤልም ሁሉ አባትህ ጽኑዕ፥ ከእርሱም ጋር ያሉት ሰዎች ኃያላን እንደሆኑ ያውቃሉ። እኔ እንዲህ እመክርሃለሁ፥ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤልም ሁሉ ብዛታቸው እንደ ባህር አሸዋ ሆኖ ወደ አንተ ይሰብሰቡ፥ አንተም በመካከላቸው ትሄዳለህ። እርሱንም ወደ ምናገኝበት ወደ አንድ ስፍራ እንደርስበታለን፥ ጠልም በምድር ላይ እንደሚወድቅ እንወርድበታለን፥ እርሱንና ከእርሱም ጋር ያሉ ሰዎችን ሁሉ አንድስ እንኳ አናስቀርም። ወደ ከተማም ቢገባ እስራኤል ሁሉ ወደዚያች ከተማ ገመድ ይወስዳሉ፥ እኛም አንድ ድንጋይ እንኳ  እስከ ማይገኝበት ድረስ ወደ ወንዙ ውስጥ እንስባታለን።» ብሎ መከረው። አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ «የአርካዊው የኲሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይሻላል፤» አሉ። እግዚአብሔር ለአቤሴሎም መልካም ለዳዊት ግን ክፉ የነበረውን የአኪጦፌልን ምክር ለወጠው። ሃይማኖቱ ካለ በጠላት መንደር የተመከረውን ሁሉ እግዚአብሔር ይለውጠዋል።
          ክፉ ቀን ያልለወጠው ኲሲ ከንጉሡ ከዳዊት እንደተማከሩት፥  የተመከረውን ምክርና ፈጥኖም ዮርዳኖስን ተሻግሮ እንዲያድር የሚነግሩት መልዕክተኞችን ላከበት። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ አንድም ሳይቀር ዮርዳኖስን ተሻግረው አደሩ፡፡ አኪጦፌልም ምክሩ እንዳልሠራ ባየ ጊዜ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፡፡ ፪ኛ ሳሙ ፲፯፥፭-፳፫። አቤሴሎምም ከአባቱ ጋር  ሲዋጋ ሞተ፡፡ ምድራዊ ሥልጣን ክፉ ነው፡፡ በእናትና በአባት፥ በወንድምና በእህትም ላይ ያስጨክናል፡፡ ንጉሡ ዳዊት እንደ ሐሳቡ አልሆነለትም እንጂ፥ «ለብላቴናው ለአቤሴሎም ስለ እኔ ራሩለት፤» ብሎ ኢዮአብንና አቢሳን ኤቲንም አዝዟቸው ነበር፡፡ ኢዮአብ ግን አቤሴሎም የራስ ፀጉሩ በዛፍ ቅርንጫፍ ተይዞ ተንጠልጥሎ እንዳለ በሰማ ጊዜ በሦስት ጦር ወግቶ ገደለው፡፡ አቤሴሎም ወንድሙን አምኖንን በጦር እንዳስገደለው እርሱም በጦር ተወግቶ ሞተ። ሰው ሁሉ የሚያገኘው የእጁን ነውና፡፡ ኢዮአብ በአቤሴሎም የጨከነበት ከምህረትና ከይቅርታ የማይማር ብላቴና በመሆኑ ነው፡፡ ንጉሡ ዳዊት የአቤሴሎምን ሞት በሰማ ጊዜ፥ «ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፈንታ እኔ እንድሞት ቤዛህም እንድሆን ማን ባደረገኝ ልጄ፥ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥» እያለ አለቀሰ። ፪ኛ ሳሙ ፲፰፥፩-፴፫። ንጉሡ ያለቀሰው ለወዳጁ ሳይሆን ለጠላቱ ነው፥ እኛ ብንሆን እንደሰታለን እንጂ አናዝንም ነበር፥ ብሶብንም ለወዳጆቻችን እንኳ የማናዝን ሰዎች ሆነናል።    
፩፥፬፦ ምክረ አረጋውያን፤
          ዕድሜ የጠገቡ አረጋውያን በአብዛኛው በጎ በመምከር ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም ክብር ይገባቸዋል፡፡ በዳዊትም በሰሎሞንም ዘመነ መንግሥት አማካሪ ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ንጉሡ ሰሎሞን ከሞተ በኋላ፥ ሮብዓምን በአባቱ ምትክ ሊያነግሡት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ በሴኬም ተሰበሰቡ፡፡ ሮብዓምንም፦ «አባትህ ቀንበር አከብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን፤» አሉት፡፡ እርሱም፦ «ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ፤» ብሎ ካሰናበታቸው በኋላ፦ «ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድነው?» በማለት፥ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩ ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። እነርሱም፦ «ለዚህ ሕዝብ አሁን አገልጋይ ብትሆን፥ ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትነግራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ አገልጋዮችህ ይሆናሉ፤» ብለው ተናገሩት።
ከሽማግሌዎቹ ምክር የምንማረው፥ ባለሥልጣን መሆን ለመገልገል እና ለመግዛት ሳይሆን፥ ሕዝብን በትህትና ለማገልገል እና ለሕዝቡ ፈቃድ ለመገዛት መሆኑን ነው። በዓለም የሚታየው ግን እንዲህ አይደለም። ሥልጣን፦ ሕዝብን እንደባሪያ ለመግዛት፥ ፈቃዱንም በኃይል ለመጨፍለቅ የማጥቂያ መሣሪያ ሆኖአል። ሮብዓም የሽማግሌዎችን ምክር አልተቀበለም። ዛሬም፦ «ሕዝቡ ሸክም ከብዶበታል፥ ቀንበር ጠብቆበታል፥ ኑሮ ወድዶበታል፤» ብሎ ከልቡ የሚናገር ሰው አልፎ አልፎ ቢገኝም ሰሚ አልተገኘም። ችግሩን መናገር በራሱ ችግርን ያመጣል፡፡ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም። ሰቆቃወ ኤርምያስ ላይ፦ «ከራብ የተነሣ ሰውነታችን ጠወለገ፥ ቁርበታችንም (ቆዳችን፣ መልካችን) እንደ ምድጃ ጠቆረ፥ በጽዮን ሴቶች፥ በይሁዳ ከተሞችም ደናግል ተዋረዱ። አለቆችም በእጃቸው ተሰቀሉ፥ የሽማግሌዎችንም ፊት አላከበሩም። ጎልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም በእንጨት ደከሙ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ ጠፉ፥ ጎልማሶችም ከበገናቸው ተሻሩ። የልባችን ደስታ ተሽሮአል፥ ዘፈናችን ወደ ለቅሶ ተለውጧል። የራሳችን አክሊል ወድቋል፥ ኃጢአትን ሠርተናልና ወዮልን! ስለዚህ ልባችን ታምሞአል ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤ የጽዮን ተራራ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮዎችም ተመላልሰውባታልና። አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፥ ዙፋንህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። ስለምን ለዘለዓለም ትረሳናለህ? ስለምንስ ለረዥም ዘመን ትተወናለህ? አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፥ ዘመናችንን እንደቀድሞ አድስ። ፈጽመህ ጥለኸናልና፥ እጅግም ተቆጥተኸናል።» የሚል አለ። ሰቆ ኤር ፭፥፲-፳፪፡፡
፩፥፭፦ ምክረ ወራዙት፤
          ሮብዓም የሽማግሌዎችን ምክር ንቆና አቃሎ፥ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩ ብላቴኖች ጋር ተማከረ። እርሱም፦ «አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቃልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?» አላቸው። እነርሱም፦ «ታናሺቱ የእጄ ጣት ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፥ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፥ አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ፥ በላቸው፤» አሉት። ሮብዓምንም ከሽማግሌዎቹ ምክር ይልቅ የአድር ባይ ወጣቶች ምክር ደስ አሰኘው። በቀጠሮውም ቀን ባልንጀሮቹ በመከሩት ቃል ህዝቡን አሳዘነ። ሕዝቡም አዝነው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ ሮብዓም በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ላይ ነግሦ፥ አስገባሪውን አዶኒራምን ቢልክባቸው በድንጋይ ቀጥቅጠው ገደሉት። እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ፥ ከብቻው ከይሁዳና ከብንያም ነገድ በቀር የተከተለው አልነበረም፡፡ በሽማግሌዎቹ ምክር ከብሮ መኖር ሲችል ተዋረደ። በተቀሩት በአሥሩ ነገድ ላይ የአባቱ ባሪያ የነበረ ኢዮርብዓም ነገሠ፡፡ ፩ኛ ነገ ፲፪፥፩-፴፫።
          የዚህ ዓለም ገዢዎች ለሕዝብ ተሹመው ሳለ፥ ለምን በሕዝቡ ላይ ሸክም እንደሚያከብዱበት፥ አእምሮ ላለው ሰው መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፡፡ ዓላማቸው ሁሉ፥ ሕዝቡን አስፈራርተው፥ አዳክመውና አስጨንቀው መግዛት ነው፡፡ ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ የሚሰጡት ሁልጊዜ የትዕቢት ነው፡፡ በውስጣቸው ያለው የሮብዓም ልብ ነው፡፡ ይህ ነገር በመንፈሳዊ ዓለም አለን በሚሉ ባለሥልጣኖችም ዘንድ ብሶበት ይታያል፡፡ «እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር፥ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እማልዳቸዋለሁ። በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔር መንጋዎች ጠብቁ፥ ስትጠብቋቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኃይል አትግዙ። የእረኞችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።» የሚለው ተዘንግቷል።  ፩ኛ ጴጥ ፭፥፩-፬፡፡ «የመሰማሪያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው፤» ያለ እግዚአብሔርም አልተፈራም፡፡ ኤር ፳፫፥፩፡፡ በነቢዩ በሕዝቅኤልም አድሮ፥ «ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች ራሳቸውን ያሰማራሉን? እረኞች በጎችን ያሠማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ወተቱን ትጠጣላቸሁ፥ ጠጉሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትንም ታርዳላችሁ፥ በጎቹን ግን አታሰማሩም፡፡ የደከመውን አላጸናችሁትም፥ የታመመውንም አልፈወሳችሁትም፥ የተሰበረውንም አልጠገናቸሁትም፥ የባዘነውንም አልመለሳችሁትም፥ የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም፥ በኃይልና በጭቆናም ገዛችኋቸው።» ብሎአል። ሕዝ ፴፬፥ ፩-፬፡፡ ዳሩ ግን ሥጋውያንም መንፈሳውያንም ባለሥልጣኖች፥ በእግዚአብሔርም በሰውም ቃል ተመክረን አልተመለስንም፡፡
፩፥፮፦ ምክረ ኤልዛቤል፤
          ኤልዛቤል የንጉሡ የአክዓብ ሚስት ናት፡፡ አክዓብ በእስራኤል መንግሥት ሰባተኛ ንጉሥ ነው። ዘመኑም ከ፰፻፸፬-   ፰፻፶፫ ዓ.ዓ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፡፡ በመንግሥት አስተዳደር በኩል ጠንካራ ቢሆንም እግዚአብሔርን የማይፈራ ንጉሥ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት «አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።» ተባለ፡፡፩ኛ ነገ ፲፮፥፴። የእርሱ ድካም እንዳለ ሆኖ ሚስቱ ኤልሳቤጥ በምክሯ ወደ አምልኮተ ጣዖትና ወደ ክፉ ሥራ ሁሉ ትገፋፋው ነበር። ፩ኛ ነገ ፳፥፳፭፡፡ የጣዖቱን ነቢያት ትቀልብ፥ የእግዚአብሔርን ነቢያት ትገድል ነበር። ፩ኛ ነገ ፲፰፥፩-፵፮ ነቢዩ ኤልያስንም ልትገድለው አሳዳዋለች፡፡ ፩ኛ ነገ ፲፱-፪፡፡
          ንጉሡ አክዓብ የንግሥቲቱን የአክዓብን ቃል ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም ነበር። ናቡቴንም ያስገደለው በእርሷ ምክር ነው፡፡ ለኢይዝራኤላዊው ለናቡቴ በሰማሪያ ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን ቦታ ነበረውና ካልሸጥክልኝ አለው።ናቡቴ ግን፦ «የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እግዚአብሔር አያምጣብኝ፤ (እንዲህ አይነቱን ክፉ ሐሳብ እግዚአብሔር ያርቅልኝ)፤» አለ። አክዓብም አዝኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፥ ምግብም አልበላ ብሎ ተሸፋፍኖ ተኛ። ሚስቱም ኤልዛቤል የሆነውን ነገር በጠየቀችው ጊዜ በናቡቴ  ምክንያት መሆኑን ነገራት። እርሷም፦ «አሁንም አንተ የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንደዚህ ታደርጋለህ? ተነሣ፥ እንጀራንም ብላ፥ ራስህንም አጽና፥ ልብህንም ደስ ይበላት፥ የኢይዝራኤላዊውንም የናቡቴን የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፤» አለችው፡፡ በአክዓብም ስም ደብዳቤ ጻፈች፥ በማኅተሙም አተመችው፥ በከተማውም ወደነበሩትና ከናቡቴም ጋር ወደ ተቀመጡት ሽማግሌዎችና አለቆች ደብዳቤውን ላከች። የዚያች ደብዳቤም ቃል፥ «ጾምን ጹሙ፥ ናቡቴንም በህዝቡ መካከል በከፍተኛ ቦታ አስቀምጡት፥ ሁለት የሐሰት ምስክሮችንም በፊቱ አስቀምጡና፦ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቧል ብለው ይመስክሩበት፥ አውጥታችሁም እስኪሞት ድረስ በድንጋይ መትታችሁ ግደሉት።» ይላል። የከተማይቱ ሰዎችና ሽማግሌዎች ባለሥልጣኖቹም የታዘዙትን ሁሉ አደረጉ፡፡ ናቡቴ ያለኃጢአቱ በድንጋይ ተደብድቦ ሞተ። ፩ኛ ነገ ፳፥፩-፲፫። በዚህ ዓለም ስንት ሰዎች በሐሰሰት ተከሰው፥ በሐሰት ተመስክሮባቸው፥ በሐሰት ይፈረድባቸው ይሆን? የዚህ ዓለም መሪዎች የስንቱን ደም በግፍ አፍስሰው ይሆን? ዛሬም የኤልዛቤል ምክር በየቤቱ አለ። «ተው፥ ግፍ ነው፤» የሚል አልተገኘም፥ «ተው፤» የሚል  ከተገኘም ዕጣ ፈንታው እንደዚያው ይሆናል። ምድሪቱ የብዙ ንጹሐንን ደም ጠጥታለች። የበታች ሹማምንትም «ለምን?» አይሉም፡፡
          ሰው ዝም ቢል እግዚአብሔር ዝም አይልም። ንጉሡ አክዓብ፦ «ናቡቴ ሞቶአል እንጂ በሕይወት አይደለምና በገንዘብ ይሰጥህ ዘንድ እንቢ ያለውን የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ቦታ ተነሥተህ ውረስ።» የሚለውን የኤልዛቤልን ምክር ተቀብሎ ወደ ናቡቴ የወይን ቦታ ወረደ። እግዚአብሔርም፦ ቴስብያዊውን ኤልያስን ወደ እርሱ ላከው። ነቢዩም እግዚአብሔር እንደነገረው፥  «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ጅቦችና ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል፥ አመንዝራዎችም በደምህ ይታጠባሉ።. . . በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ ኤልዛቤልን ውሾች ይበሉአታል።» ሲል ለንጉሡ ነገረው። ንጉሡ አክዓብ ለጊዜው ነቢዩን «ጠላቴ ሆይ! አገኘኸኝን?» ቢልም ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ ደንግጦ በፍጹም ሐዘን ልብሱን ቀደደ፥ እያለቀሰም ሄደ፥ በሰውነቱም ላይ ማቅ ለበሰ፥ ጾመም፥ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ባሪያው ወደ ኤልያስ፦ «አክዓብ በፊቴ እንደ ደነገጠ አየህን? በፊቴ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም።» ሲል መጣ። ፩ኛ ነገ ፳፥፲፯-፳፱። በዚህም፦ «የአክዓብን ዘር አጠፋዋለሁ፥ በእስራኤል ውስጥ ያሉትንም የሌሉትንም እነቅላለሁ፥ በሥራህም አስቆጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና፥ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።» ያለውን ፍርድ ለጊዜው አነሣለት። እኛ ትንሽ ስንጸጸት፥ እግዚአብሔር ብዙ ምሕረት ያደርግልናል። እንባችንን፥ ማቅ መልበሳችንን፥ መጾማችንን አይቶ ይራራልናል። ጊዜው ሲደርስ ንጉሡ አክዓብ ከሶሪያው ንጉሥ ከወልደ አዴር ጋር ሲዋጋ በጽኑ ቆስሎ ደሙ ቀኑን ሙሉ በሰረገላው ላይ ፈሶ ሞተ፥ በሰማርያም ቀበሩት። ሰረገላውንም በሰማርያ ምንጭ ባጠቡት ጊዜ፥ እግዚአብሔር እንደተናገረ፥ ውሾችና ጅቦች ደሙን ላሱት፥ አመንዝሮች ሴቶችም በደሙ ታጠቡበት። ፩ኛ ነገ ፳፩፥፳፱-፵። በኤልዛቤልም ላይ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ተፈጽሞባታል፡፡ ፪ኛ ነገ ፱፥፴- ፴፯።
                             ፩፥፯፦ ምክረ ውሉደ ያዕቆብ፤
                    የያዕቆብ ልጆች በወንድማቸው በዮሴፍ እጅግ አድርገው ይቀኑ ነበር። የቀኑበትም አባታቸው ያዕቆብ ከእነርሱ አብልጦ ስለወደደውና እግዚአብሔርም ህልም የማለም ጸጋ ስለሰጠው ነበር። የህልሙ ትርጓሜም ዮሴፍ ወደፊት እጅግ ታላቅ ሰው እንደሚሆን የሚያሳይ ነበር፡፡ «እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበር፥ እነሆ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፥ የእናንተም ነዶዎች በዙሪያው ከበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።» ቢላቸው፥ «በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ገዢ ትሆነን ይሆን?» አሉት። ስለ ህልሙና ስለነገሩ የበለጠ ጠሉት። ደግሞም ሌላ ህልም አለመና ለአባቱ እና ለወንድሞቹ፥ «ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ክዋክብትም ይሰግዱልኝ ነበር፤» አላቸው። አባቱም ገሠጸውና «ይህ ያለምኸው ህልም ምንድን ነው? በውኑ እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?» አለው። ወንድሞቹም ቀኑበት፥ አባቱ ግን ይህን ነገር በልቡ ይጠብቀው ነበር፡፡
          በሌላ ቀን ዮሴፍ አባቱ ልኮት፥ ስንቅ ይዛላቸው፥ በጎቻቸውን ወደ አሰማሩበት ወደ ዶታይን ቢሄድ ከሩቅ አይተው ሊገድሉት ተማከሩ፡፡ «ያ ባለህልም ይኸው መጣ፥ ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንጣለው፥ ክፉ አውሬም በላው እንላለን፥ ህልሞቹም ምን እንደሚሆኑ እናያለን?» አሉ። ሮቤል ግን «ሕይወቱን አናጥፋ፥ ደም አታፍስሱ፥  በዚህች ምድረበዳ ባለችው ጉድጓድ  ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት፤» አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልስው ነበር፡፡ ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ  የለበሳትን በብዙ ህብር ያጌጠችውን ቀሚሱን ገፈፉት፥ ወደ ጉድጓድም ጣሉት፥ ጉድጓዱ ውሃ የሌለበት ባዶ ነበረ። ይህንን የጭካኔ  ሥራ ከሠሩ በኋላ እንጀራ ሊበሉ ተቀመጡ። በዚህን ጊዜ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ሲመጡ ከሩቅ በማየታቸው ይሁዳ ባመጣው ሃሳብ መሠረት በሃያ ብር ሸጡት። ሮቤል ከጉድጓድ አውጥቶ በሥውር ወደ አባቱ ሊሰድደው ቢሄድ አጣው፥ ከሐዘንም የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደው። ሌሎቹ ግን የዮሴፍን ልብስ በደም ነክረው ወደ ቤት በመመለስ «ዮሴፍን ክፉ አውሬ በላው፤» ብለው አባታቸውን አስለቀሱ። ዘፍ ፴፯፥፩-፴፭። ዛሬም እንዲሁ ነው፥ ምድሪቱ በቅናትና በምቀኝነት፥ በግፍና በበደል ተከድናለች። የሚመከረው ሁሉ ወንድም ወንድሙን፥ ወገን ወገኑን ለማጥፋት ነው። በሥጋዊ በረከትም ሆነ በመንፈሳዊ ጸጋ የወንድሙን ከፍ ማለት የሚወድ የለም።  ይሁን እንጂ የእግዚአብሔርን እቅድ ማስቀረት ዓላማውንም ማሰናከል አይቻለም። ዮሴፍ፥ ያውም በባዕድ ሀገር  ከንጉሡ በታች ታላቅ ባለሥልጣን ሆኖአል። እነዚያ የቀኑበትና የጠሉት፥ የገፈፉትና ወደ ጉድጓድ የጣሉት፥ አውጥተውም ለባእድ የሸጡት ወንድሞቹም ሰግደውለታል፡፡ ዘፍ ፵፩፥፴፯-፵፭፤ ፵፪፥፮፡፡
          ወንድሞቹ መክረው ያዋረዱትን ዮሴፍን፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን «በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ፤» አለው።ወንድሞቹ የገፈፉትን፥ ቀለበቱን አውጥቶ በእጁ ላይ አደረገለት፥ የነጭ ሐር ልብስም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍ አደረገለት፥ የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፡፡ ይህንን ሁሉ ያደረገ እግዚአብሔር  ነው፡፡ እርሱም ለወንድሞቹ ስለክፉ ፈንታ በጎ አደረገላቸው፥ ተቸግረው ሲመጡ በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ «ወደ እኔ ቅረቡ፥ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፥ አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፥ አትቆርቆሩም፥ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። . . . እግዚአብሔርም በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤»  አላቸው።  ዘፍ ፵፭፥፩-፰፡፡
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment