Friday, February 24, 2012

የቦረና ጉጂና ሊበን ዞነን ሃገረ ስብከት በኪዳነምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል ቀን በተነሳው ግጭት ከ40 በላይ ክርስትያኖች ታሰሩ

የቦረና ጉጂና ሊበን ዞነን ሃገረ ስብከት በኪዳነምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል ቀን በተነሳው ግጭት ከ40 በላይ ክርስትያኖች ታሰሩ


  • በግጭቱ ምክንያት ንግስ አልነበረም ፤ ቅዳሴም ሳይቀደስ ቀርቷል
  • የሚጠቡ ህፃናት ቤት አስቀምጠው በእስር የሚገኙ እህቶች አሉ
  • አራት ሰዎች ያህል ከአንድ ቤት የታሰሩም ይገኛሉ
  • ምሽቱን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በእስር ላይ ከሚገኙት ምዕመናን ውስጥ የወረዳው ሊቀ ካህን መሪጌታ ልሳነወርቅ ወልዴ ፤ ቀሲስ ወርቁና  የ80 ዓመት እድሜ አዛውንት አቶ ዘውዴ አበሩ በእስር ላይ እንደሚገኙ  ለማወቅ ችለናል


(አንድ አድርገን የካቲት 16 ፤2004ዓ.ም) የቦረና ጉጂና ሊበን ዞኖች ሃገረ ስብከት የክብረመንግስት ከተማ  ህዝብ ትግል የተባረረውና ዛሬም የሃገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ነኝ የሚለው ተሾመ ሃይለማርያም አሁን መሽጎ በሚገኝበት በክብረመንግስት ከተማ ሌላ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ሳይጠሩ አቤት ሳይላኩ ወዴት የሚሉ ሰዎች ቤተክርስትያንን ከበዋት ይገኛሉ፡፡ የተሀድሶያውያን ርዝራዦች በየቦታው ጊዜ ጠብቀው በማድባት ቤተክርስትያናችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ፤ ከበላይ ያለው አመራር ንዝህላልነት በጉዳዩ ዙሪያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል ፤ ችግሮች ሲፈጠሩ ለችግሮቹ ወቅታዊ መፍትሄ አለመስጠት ችግሮችን ሌላ ችግር እንዲፈጥሩ እድል እየሰጠ ይገኛል፡፡

በየኣመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የካቲት 16 የእመቤታችንን በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ምእመን፤ ያለ ህግና ስርአት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ተሾመ ሃይለማርያም አጥቢያቸውን ሊረብሽ እነደሚመጣ ሰምተው ግቢያቸውን እንዳይረግጥ እንዲደረግ ለአካባቢው አስተዳደርና የጸጥታ አካል አስታውቀው መፍትሄ በማጣታቸው በራቸውን ዘግተው አናስገባም በማለት ኡኡታቸውን ለማሰማት ቢሞክሩም ከሌላ ደብር ፤በተለይም የግለሰቡ መፈንጪያ ከሆነው ቅዱስ ሚካኤልና ከማርያም ቤተክርስቲን ባሰባሰቧቸው የአላማ ተጋሪ ጎረምሶች ታግዘው በጉልበት ለመግባት ሙከራ በማድረጋቸው ህዝቡ በመጮሁ ሰውየው በቦታው ላይ እንዳይመጣ ከመከልከል ይልቅ የረብሻውን መነሳት ይጠባበቅ የነበረው  በአካባቢው የነበረው የፌዴራል ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሺያ ከአርባ በላይ በአሉን ለማክበር የተሰበሰቡ  ቀናኢ ክርስቲያኖች በዱላ በመደብደብ በመኪና ጭኖ በከተማው ውስጥ በሚገኙ እስር ቤቶች አጉሯቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ የእመቤታችንን ንግስ ማክበር ሳይቻል ቀርቷል ፤እመቤታችን ቃል ኪዳን በተቀበለችበት ቀን ፤  ቅዳሴ ሳይደረግ ተስተጓጉሏል ፤ ስለ ቤተክርስትያን የተቆረቆሩ ሰዎች ከየቤቱ ሶስት እና አራት ሰዎች ድረስ የታሰረባቸው መኖራቸውን ሰምተናል ፤ ቤታቸው የሚጠቡ ህፃናት አስቀምጠው ስለቤተክርትያን ብለው እስር ቤት የታሰሩ እህቶች በእስር የሚገኙም መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል ፤ በሀገራችን ላይ ሁለተኛ ዜጋ ሁነን የምንኖረው እስከመቼ ነው ? በቤተክርስትያናችን ላይ ይህን የመሰለ ህገወጥ ተግባር እየተከናወነ እያየን የምንታገሰውስ ?  ቤታችንን ከእነዚህ አይነት ሰዎች የምናፀዳውስ?  ቤተክህነቱስ በስልጣን ተዋረዱ መሰረት የሰዎችን ጥያቄ በጊዜው እና በሰዓቱ መፍታ የሚችለውስ ? በጠቅላላው  ከአርባ በላይ ክርስትያኖች በአሁኑ ሰዓት በእስር ቤት መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል ፤ ቦታው ላይ የሚገኝው ሚኒሻም ሆነ ፌደራል ፖሊስ ችግሩ ሳይፈጠር መከላከል እየተቻለ ሰዎች በቤተክርስትያን ላይ ችግር እስኪፈጥሩ ድረስ መጠበቅ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለንም ፤ ቤተክርስትያኗ ይወክሉኛል ያለቻቸው የወንጌል መምህራን አሏት ፤ እሷን የማይወክሉ ፤ ተጠግተው ጥቅም ለማግበስበስ የሚፈልጉ ሰዎችም በርካታ ናቸው ፤ 


በቤተክርስትያናችን በቤታችን ላይ በዓላችንን በህገወጥ ሰዎች አማካኝነት ማክበር አልቻልንም ፤ ቀድሞ ቤተክህነቱም ጉዳዩን አይቶ እንዳላየ የማለፍ ነገር ነገሩን ለዚህ ደረጃ አድርሶታል ፤ ችግሮችን መፍታት አይቻሉም ወይስ እንዲፈቱ አይፈለጉም? ይህ የኛ ጥያቄ ነው ፡፡ ዛሬ በነገሌ ቦረና ላይ የተደረገው ነገር በጊዜው የነበረውን ህዝበ ክርስትያኑን ክፉኛ ልቡ እንዲደማ አድርጎታል ፤ በሁኔታውን እንባውም እንዲያፈስ ግድ ብሎታል ፤ እኛም ሲበዛ አዝነናል ፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደም ሲኖዶሱ ለአካባቢው ተገቢውን ሊቀ ጳጳስ ይመድብ ፤ የምዕመኑን ችግሮቻቸውን የሚናገሩበት መፍትሄም የሚሰጥበት መድረክ ይፈጠርላቸው ፤ የቤተክርስትያን አማኝ ያልሆነ ጎረምሳ በብር እየገዙ እንደዚህ አይነት ቀውስ እየፈጠሩ የሚገኙትን ሰዎች መንግስት ዱካቸውን ተከታትሎ ለሀገር ፤ ለቤተክርስትያንና ለህዝብ ሰላም ሲባል ከእኩይ ተግባራቸው ያስታግሳቸው ፤ ካልሆነም ሀገሪቱ የምትተዳደረው በተፃፈ ህግ ስለሆነ ፍርድ ቤት ያቅርብልን ፤ ነገሮችን ዝም ብሎ ማለፍ ግን ነገሩን ይባስ ስለሚያከረው መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ችግር ችግርን እንዲወልድ ማመቻቸት ነውና ይታሰብበት ፤  


ቆይ አስኪ የኛ የቤተክርስትያን ልጅነት እስከምን ድረስ ነው ? ለችግሯ ካልደረስንላት ፤ የመፍትሄ አካል ሆነን ከፊት ካልቆምንላት ፤ በዚህ አይነት ችግር ውስጥ ያሉትን እህት ወንድሞቻችንን አኛም አለን ካጠገባችሁ ነን ካላልናቸው ፤ ነገ የሚመጣውን ችግር አውቀን ቀድመን የመፍትሄ አቅጣጫ ካላስቀምጥንላት ፤ ችግር የሚያደርሱትን ሰዎች ፊት ለፊት ተጋፍጠን የቁርጥ ቀን ልጅነታችንን ካላስመሰከርን ምኑን የቤተክርስትያን ልጆች ሆንን? የቤተክርስትያናችን ችግር የኛ የእያንዳንዳችን ችግር መስሎ ሊሰማን ይገባል ፤ እንደ ጉጂና ሊበን ዞኖች ሃገረ ስብከት ዳር ያሉትን አብያተክርስትያናት መጠበቅ ካልቻልን መሀሉ ዳር የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም ፤ ይህን ችግር አውቆ የሚፈታ ቤተክህነት ባይኖረንም ፤ መረጃው ጋዜጦችና ኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ላይ እንዲወጣ ችግሩን ምዕመኑ እንዲያውቀው ለማድረግ በአድራዎቻቸው ልከናል፤ይህን መረጃ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ የታሰሩት ሰዎች አልተፈቱም ፤  ምን ደረጃ እንደደረሱ ተከታትለን እናቀርብሎታለን ፤


ከዚህ በፊት አካባቢው ላይ ያለውን ችግር አንድ ሳናስቀር ከቀናት በኋላ ሙሉ መረጃውን እናቀርብሎታለን

ሠላምና ፍትህ ለቤተክርስቲያን መች ይመጣ ይሆን!?
‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስትያንን ይጠብቅልን››
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment