አቡነ ፋኑኤል ሀ/ስብከት በማፍረስ ጎዳና ላይ ይሆኑ?
(ደጀ ሰላም፣ ጥር 24/2004 ዓ.ም፤ February 2/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ በብፁዕ አቡነ አብርሃም ምትክ የዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የሀ/ስብከቱን መኖር እንደማያውቁ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በተናገሩ ማግስት ለቅ/ፓትርያርኩ የላኩት ደብዳቤ ለድረ ገጻችን በአድራሻ ተልኮልናል፡፡ ደብዳቤውን ያደረሱንን ደጀ ሰላማዊ ከልብ እናመሰግናለን።
ሊቀ ጳጳሱ አስቀድሞ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ሀ/ስብከት መኖሩን አላውቅም” ማለታቸውን ሰምተናል። ያንን አስከትለው ደግሞ የለም ያሉትን ሀ/ስብከት “በሕግ ለመጠየቅ” ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ባልሸሸጉበት ሁኔታ በሀ/ስብከቱ ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ሰብሳቢነት ባደረጉት ዓመታዊ ጉባኤ የተቋቋመውን የሀ/ስብከቱን ሥራ አስፈጻሚ “ሕገ ወጦች” እና “የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች” በሚል ጠርተዋል።
ከዚያም አልፎ “ማኅተም በሕገ ወጥ መንገድ በማሳተም” እንደሚሠራም በግልጽ ተናግረዋል። ብፁዕነታቸው ሀ/ስብከቱን ዕውቅና ካለመስጠት ጀምሮ በሕግ ወደመጠየቅ ለመሔድ ከማስፋራራታቸው ባሻገር ቅ/ሲኖዶስ ያፈረሰውን “በሰሜን አሜሪካ የውጪ ግንኙነት ጽ/ቤት” ከሞት በመቀስቀስ ነፍስ ሊዘሩበት ሞክረዋል። እንግዲህ ሕገ ወጡ ማነው? የቅ/ሲኖዶስን ውሳኔ ያስተሃቀረውስ ማነው?በቪኦኤ ሲናገሩ እንደሰማነው ሀ/ስብከቱ መኖሩን አላውቅም ያሉት “አውሮፕላን ማረፊያ መጥቶ” ስላልተቀበላቸው መሆኑን አብራርተዋል። አውሮፕላን ማረፊያ አልተቀበለኝም ያሉት በወቅቱ በአካባቢው የነበሩትን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ይሁን የሀ/ስበከቱን ሥራ አስፈጻሚ በግልጽ አላስቀመጡም። አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ካልተደረገላቸው ተቋሙ አይኖርም ማለት ነው። ታዲያ ሹመቱን ሲቀበሉ የየትኛው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ እሆናለሁ ብለው ነበር? ዘይገርም ነው።
ብፁዕነታቸው የዲሲና አካባቢውን ሀ/ስብከት ለማፈራረስ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ወጣቶች የተሰባሰቡባቸውን የማኅበረ ወልድ እና የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነትንም እንደማያውቁ ሰሞኑን በጠሩት የካሊፎርኒያ ሀ/ስብከት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። በስብሰባው ላይ ሲነገር እንደተሰማው “ማኅበራቱ የተቋቋሙት ለአቡነ አብርሃም” ነው። የሚገርመው ግን ማኅበራቱ የተቋቋሙት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሀ/ስብከቱ ሳይቀመጡ መሆኑ ነው።
ብፁዕነታቸው ደብዳቤያቸው ላይ ገለፁት ሌላው ዐቢይ ነጥብ “ተከፋፍለው የነበሩ ካህናትን፣ ምዕመናንና ምዕመናትን …” አንድ ለማድረግ በመጣር ላይ መሆናቸው ነው። ከሆነ መቸም አንድነትን የሚጠላ ማንም የለም ነበር። ነገር ግን አንድነት ያሉት ሳራቸውም በተቀመጡበት አጥቢያ የማያከብሩት እና ሌሎቹም “ባያከብሩት ችግር የለውም” የሚሉትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ከሆነ አንድነቱ አንድነት ሳይሆን መላ ቅጡ የጠፋ ውጥንቅጥ ነው ማለት ነው። እርሳቸው ሰሞኑን በቆሙባቸው መድረኮች ሁሉ ሲያንቆለጳጵሷቸው የሚውሉትን ቅዱስ ፓትርያርኩን ስም በቅዳሴ ሳይጠሩ፣ ራሳቸው በቃለ ዐዋዲ ሳይመሩ፣ ራሳቸው የተሰጣቸውን የዲሲ እና አካባቢውን ሀ/ስብከት ጥለው ሌላ “ተለጣፊ” ሀ/ስብከት ለማቋቋም ደፋ ቀና እያሉ፣ የወጣቶች ማኅበራትን ለመዝጋት፣ ሌሎችንም ለመክሰስ እያስፈራሩ አንድነት አመጣለሁ ማለታቸው በእጅጉ የሚያስገርም ሆኗል።
እንግዲህ ማንን እንስማ የሚለውን ጥያቄ የምንጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በተለይም በአሜሪካ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ምእመናን ቅ/ሲኖዶስን ወይስ አቡነ ፋኑኤል ይስሙ? ቅ/ሲኖዶስ የዘጋውን እርሳቸው ከከፈቱ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለራሳቸው በሚመች መልኩ ቅምጥል ጥብቆ አድርገው ለመስፋት ከታተሩ፣ በሐዋሳ ያሳዩትን አዋኪነት በአሜሪካም ከገፉበት፣ "This is America" እያሉ አሜሪካዊ ዜጋ መሆናቸውን እንዲሁም በእጅ አዙር የሚያስተዳድሩትና ለቤተ ክህነቱ የማይገዛ አጥቢያ ያለቸው መሆናቸውን ከተመኩበት፣ የሚያዋጣቸውን እርሳቸው ያውቃሉ።
ደጀ ሰላምም በዚህ ጉዳይ ላይ በሰፊው እንደምትመለስበት ቃል እየገባች፣ ተያያዥ ማስረጃዎችን እና የዲሲ ሀ/ስብከት የሔደባቸውን መስመሮች በሰፊው እንደምታቀርብ ታስታውቃለች።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
No comments:
Post a Comment