Thursday, December 20, 2012

ሰበር ዜና - ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ ሠየመ - ቤተ ክርስቲያን በከፋ የመለያየት አደጋ ውስጥ ትገኛለች !!

  • የፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቁን አጽድቆ ተፈራርሟል
  • ጠቅላላ ሂደቱ በመንግሥትና የመንግሥትን አቋም በሚደገፉ ጳጳሳት ቁጥጥር ሥር ገብቷል
  • ለዕርቀ ሰላም ንግግር ወደ አሜሪካ ያመሩት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ‹‹መግለጫ እንሰጣለን፤ ከሲኖዶሱ ጋራ አብረን አንቀጥልም፤ ወደ ገዳም እንገባለን›› ማለታቸው እየተሰማ ነው
ከታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት ያህል በፓትርያሪክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ ላይ ሲወያይ የቆየው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ የሕጉን ረቂቅ አሻሽሎ አጽድቋል፤ ለዕርቀ ሰላሙ ዕንቅፋት እንዳይኾን ትዕግሥት እንዲደረግበት ብርቱ ክርክር የተካሄደበትን አስመራጭ ኮሚቴም ሠይሟል፤ እንደ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ያሉት አባቶች ከሂደቱ ራሳቸውን ማግለላቸው እየተነገረ ነው፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ኾነው የተመረጡት ከሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ አቡነ ቄርሎስ፣ አቡነ እስጢፋኖስ እና አቡነ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መመሪያ ሓላፊዎች ውስጥ ደግሞ የዕቅድና ልማት መምሪያ ሓላፊው ሊቀ ትጉሃን ኀይለ ጊዮርጊስ ዳኜ፣ የሰበካ ጉባኤው መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ ይገኙበታል፡፡ አቶ ባያብል ሙላቴ (ከማኅበረ ቅዱሳን)፣ ከታዋቂ ምእመናን መካከል ደግሞ እንደ አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬ (ከኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት) የመሳሰሉት ሰዎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡


የሲኖዶሱን ውሳኔዎች በተመለከተ በነገው ዕለት በጽሑፍ የተዘጋጀ መግለጫ እንደሚወጣ የተመለከተ ሲኾን አጠቃላይ ሂደቱ የዕርቀ ሰላሙን በር የዘጋ፣ ቤተ ክርስቲያን ወደ ከፋ የመከፋፈል አደጋ ውስጥ እንደሚከታት ተገልጧል፡፡ ለዚህም ሲኖዶሱ ዛሬ፣ ታኅሣሥ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ አስመራጭ ኮሚቴ የመሠየሙ ዜና ወደ አሜሪካ በተላኩትና በቅ/ሲኖዶሱ የተሰጧቸውን ተጨማሪ ተግባራት ለመፈጸም በዚያው በሚገኙት ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ እንደተሰማ የተወሰደው ጠንካራ አቋም በማስረጃነት ተጠቅሷል፡፡
የዜናው ምንጮች እንደሚናገሩት÷ ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ ከመሠየም ታግሦ የጥሩን የሎሳንጀለስ የሰላም ጉባኤ ውጤት እንዲጠብቅ ሲያሳስቡ የቆዩት የልኡካን ቡድኑ አባላት በዛሬው የሲኖዶሱ ውሳኔ እንባቸውን እስከማፍሰስ ደርሰው ክፉኛ አዝነዋል፤ ‹‹አንድነቱ እንዲሠምር ላይ ታች እያልን እነርሱ ይህን ከወሰኑ ከሲኖዱሱ ጋራ አብረን አንቀጥልም፤ ስለ ዕርቀ ሰላሙ ለሚዲያ መግለጫ ሰጥተን ከሲኖዶሱ እንለያለን፤ ወደ ገዳም እንገባለን›› በሚል አቋማቸውን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱ አሠራርና የውሳኔ አሰጣጥ የመንግሥት እጅ በከበደበትና የመንግሥት ድጋፍ ባላቸው ከስምንት በማይበልጡ ጳጳሳት ቁጥጥር ሥር መዋሉ ውሎ አድሮ ገሃድ ወጥቷል፤ የዕርቀ ሰላሙን በር በመዝጋት በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ የሚመራው የቀጣይ ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደትም ሳይጀመር የተቋጨ መስሎ ታይቷል፤ በግለሰብነቱ ማንም ይኹን ማን በአስተሳሰቡና በአቋሙ ምን ዐይነት አባት እንደሚፈለግም ከወዲሁ የጠቆመ ኾኗል፡፡
ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment