Wednesday, December 26, 2012

የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኅኒዓለም ያወጣው መግለጫ


ቀን ታህሣሥ 14, 2005 . .
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

·         ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ - አዲስ አበባ 
·         ለሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብጹአን አባቶች - አሜሪካ
·         ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራዲያዊ ሪፖብሊክ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ - አዲስ አበባ

ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ሃያ ዓመታት ሢመተ ፓትሪያርክን ተከትሎ ባጋጠማት የአስተዳደር ክፍፍልና መለያይት ምክንያት፥ እስከ አሁን በታሪኳ አጋጥሟት የማታውቀው ትልቅ ችግር ውስጥ ትገኛለች። በዚህም ምክንያት፥ ቀኖና ቤተክርስቲያን ፈርሶ በሃገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙት ብፁዓን አባቶቻችንም ተወጋግዘው በመለያየት የቤተክርስቲያናችን ካህናትና ምዕመናንም ከሦስትና ከዚያ በላይ ተከፋፍለው መንፈሳዊና ማሕበራዊ ህይወታቸው ተቃውሶ ይገኛል።

በረከታቸው ይድረሰንና በብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍት ምክንያት የተሰባሰቡ ካህናት አባቶቻችን፥ ለቤተክርስቲያናቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ በብጹአን አባቶቻችን መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት በቅድሚያ የሰላምና አንድነት ኮሚቴን መሠረቱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መላውን ሕዝበ ክርስቲያን በማስተባበርና የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ በግልም ሆነ በጋራ ታላቅ ታሪካዊ መስዋዕትነትን ለቤተክርስቲያናቸው በመክፈል ላይ ይገኛሉ።

እስከ አሁን ድረስ ከተደረጉት የዕርቀ ሰላም ድርድር ጉባኤዎች ሁሉ በተለይ ከህዳር 26 እስከ ህዳር 30, 2005 . . በዳላስ ቴክሳስ የተደረገው ሦስተኛው ጉባኤ የተሻለ ተስፋ የሚሰጥ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦች የተሰነዘሩበትና ግልጽ ውይይት የተደረገበት ቢሆንም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ለምንገኝ የቤተክርስቲያናችን ልጆች፥ ልንሰማው የናፈቅነውን የምሥራች ባለማሰማቱ ቀጣዩን ጉባኤ በሥጋት እንድንጠብቀው አስገድዶናል።

ስለዚህ እኛ በዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ታህሳስ 14, 2005 . . ባደረግነው ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የዕርቀ ሰላሙ ሒደት ያለበትን ሁኔታ በጥልቀት በማገናዘብ የሚከተለውን አቋም መግለጫ አውጥተናል።

1.
በሀገር ቤት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሳችን ከማንኛቸውም ጉዳዮች በላይ ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ በመስጠት በሙሉ ልብና ለቤተክርስቲያናችን ችግር መፍትሄን ሊያስገኝ በሚያስችል መልኩ እንዲሰራ በአክብሮት እንጠይቃለን። ይህ ጥያቄ፥ የኛ ብቻ ሣይሆን በመላው ዓለም ያሉ ካህናት እና ምዕመናን ጭምር በመሆኑ፥ ብጹአን አባቶቻችን የእኛ ልጆቻችሁን ልመናና ተማጽንዖ እንድትቀበሉ፥ በድጋሚ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

2.
በአሁኑ ወቅት ሰላምና አንድነት ሳይመለስ በውጭ ሀገርና በሃገር ውስጥ የሚገኙ ብጹአን አባቶቻችን ሳይስማሙ፥ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ለመሾም፥ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደረገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሰላምና አንድነት ሣይገኝ ስድስተኛ ፓትሪያርክ ቢሾም የችግሩ ግንባር ቀደም ሰለባ የምንሆነው እኛ በውጭው ዓለም የምንገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ስለሆንና ወደ አልተፈለገ መንገድ ከመሄድ እንድንድን ከሁሉም በፊት ሰላምና አንድነት እንዲቀድምልን አጥብቀን እንጠይቃለን።

ከዚህ በተጨማሪም፥ በተለይ በውጭው ዓለም በእናት ቤተክርስቲያን ሥር የምትገኙ ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምዕመናን፥ በጥር 16, 2005 ዓ. ም. ሊደረግ ከታሰበው የዕርቀ ሰላምና አንድነት ጉባዔ በፊት ፥ ይህ ጉዳይ ከሚመለታቸው ክፍሎች ጋር ሁሉ በመነጋገር ፥ ተመሳሳይ የአቋም መግለጫ ታወጡ ዘንድ ፥ በእናት ቤተክርስቲያን ስም ፥ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። 

3. በውጭው ዓለም የምትገኙ ብጹአን አባቶቻችንም ፥ ከሁሉም በላይ ለቤተክርስቲያናችሁ አንድነትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠትና የሚፈለገውን መስዋዕትነት በመክፈል ፥ ታሪክ እንድትሰሩና ፥ ቤተክርስቲያናችንን ከመከፋፈል አደጋ ትታደጉ ዘንድ ፥እኛ ልጆቻችሁ በአክብሮት እንጠይቃለን።

4. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራዲያዊ ሪፖብሊክ መንግስትም ባለበት ሕዝባዊና ታሪካዊ ኃላፊነት፥ የቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ፥ ለሀገራችን ልማትና ዕድገት የሚሰጠውን ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ በመክተት፥ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ብጹአን የቤተክርስቲያናችን አባቶች በጋራ ተስማምተው ለሚደርሱበት አቋም ሁሉ፥ ያለውን ድጋፍ በይፋ እንዲገልጥና ፥ ለሰላምና አንድነት ኮሚቴ ተፈላጊውን እገዛ እንዲሰጥ ፥ በአክብሮት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር የሀገራችንንና የቤተክርስቲያናችንን፥ ሰላምና አንድነት ፥ ይጠብቅልን።

ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ
የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ዋና አስተዳዳሪ 

ግልባጭ

ለሰላምና አንድነት ኮሚቴ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment