Monday, December 31, 2012

ላስ ቬጋስ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ለቅ/ሲኖዶስ የተማጽኖ ጥሪ አቀረቡ



(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 22/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 31/2012/ PDF)፦ በአሜሪካ ላስ ቬጋስ ከተማ የምትገኘው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ የሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስመልክቶ የተማጽኖ መግለጫ አወጡ፣ ለቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት እንዲደርስላቸውም ጠየቁ በእርቀ ሰላም የተጀመረውን ወደ አንድነት የመምጣት ጭላንጭል ማክሰም ለሚቀጥሉት የማይታወቁ አያሌ ዘመናት የምእመናንን አንገት የሚያስደፉ ሁኔታዎች እንደሚፈጥር ግልፅ ነው” ያለው መግለጫው ብፁዓን አባቶች ዕርቀ ሰላሙን ከግብ እንዲያደርሱ ጠይቋል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ተመልከቱ።
ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።

 የተፈረመበትን የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።

ቤተ ክርስቲያናችንን እንታደግ
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ።

ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ በሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ የተሰጠ መግለጫ።

ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን በቅድሚያ ቡራኬያችሁ ይድረሰን እያልን። እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት አሥርት ዓመታት በፈተና ውስጥ እንድትቆይ  ያደረገውን የልዩነት ግድግዳ አፍርሶ አንድ ሲኖዶስ አንድ ፓትርያርክ አንድ አስተዳደር እንዲኖራት ለማድረግ የተጀመረውን የእርቀ ሰላም አላማ በመደገፍ ልዑካንን በመሰየም የጀመራችሁት ሂደት አስደስቶናል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ መንበረ ፕትርክና ከማግኘቷ በፊት ለረጅም ዓመታት ከግብፅ በሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ማርቆስ ሥር ስትተዳደር መቆየቷ ይታወሳል። በነዚህ በሳለፈቻቸው ዘመናት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጠበቅ በነበራት ጽኑ አቋም ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች። ለብዙ ዘመናትም የነበረውን ችግር በማቃለል የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደተጠበቀ የራሷን መንበረ ፕትርክና እንዲኖራት እድርገዋል። የቀደሙት አባቶችችን በተግባር ያስተማሩን ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጠበቅ ሲባል የማይከፈል መሥዋእትነት አለመኖሩን ነው። ዛሬም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተኑ መዋቅራዊ አንድነትን የሚያናጉ አለመግባባት እና መለያየት የሚፈጥሩ ችግሮች እየታዩ ምመጣታቸውና ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች መብዛታቸውን ስንመለከት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ አመራር መዋቅራዊ ተዋረዱን ጠብቆ መጠናከር እንዳለበት የስገነዝበናል።

እንደሚታወቀው በሰሜን አሜሪካ ያለው የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጉዳይ መፍትሄ ተሰጥቶት ካህናትና ምዕመናን በአንድነት ለአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ማገልግል ባለመቻላቸው በርካታ ችግሮችን አስከትሎ ቆይቷል። እንዲሁም የካህናት እና የምዕመናን ሕሊና በብዙ ጉዳይ ተፈትኗል። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አንድነት መፈጠሩ በመላው ዓለም ለምንኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ ትልቅ የሊና እረፍት የሚሰጥና በአንድ ልብ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልል በር የሚከፍት ነው። በዚህም በአባቶች መካከል የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት ይህንን ተስፋ እውን ያደርጋል የሚል ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል።

እኛ የሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ የምንገኝ ካህናትና ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ልዩነት በጅጉ ገዝፎ በሚታይበት አኅጉር ውስጥ እንደመገኘታችን የእርቀ ሰላሙ ሂደት መደናቀፍ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ እንደሚጨምረው ለማወቅ አያዳግተንም። በእርቀ ሰላም የተጀመረውን ወደ አንድነት የመምጣት ጭላንጭል ማክሰም ለሚቀጥሉት የማይታወቁ አያሌ ዘመናት የምእመናንን አንገት የሚያስደፉ ሁኔታዎች እንደሚፈጥር ግልፅ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ቀጣዩን ፓትርያርክ በመንበር ላይ ለማስቀመጥ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ውስጥ ትገኛለች። የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመጨረሻ ወሳኝ አካል መሆኑን ሙሉ ለሙሉ የምንቀበል መሆናችንን በማስገንዘብ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ካለን ጽኑ አቋም እንዲሁም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ያሉ ካህናትና ምእመናን ስለቤተ ክርስቲያን አንድንት እያሳዩ ያለውን መጨነቅ በመገንዘብ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ስናቀርብ በታላቅ መንፈሳዊ አክብሮት ነው።

1ኛ. የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና በወቅቱ የነበረውን ታሪካዊ እውነት መሠረት ባደረገ መልኩ የመጨረሻ መፍትሄ እንዲያገኝ የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል።

2ኛ. የተጀመረው የእርቀ ሰላሙ ሂደት ሳይጠናቀቅ የፓትርያርክ ምርጫ በመጀመሩ የቀጣይ አገልግሎት ዘመናችንን በተገቢው ሁኔታ እንዳንጓዝ ምክንያት ሆኖብናል። ስለዚህ ለኛም ሆነ ለተተኪው ትውልድ ልጆቻችሁ ስትሉ የእርቀ ሰላሙ ሂደት እንዲጠናቀቅ እንድታደርጉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እንጠይቃለን።

3ኛ. እንደቀደሙት አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን እና ለመንጋችሁ ስትሉ ከቤተ ክርስቲያን እና ከመንጋው የሚበልጥ ምንም ስለሌለ ጉዳዩን በጥልቅ መክራችሁ የእርቀ ሰላሙን ሂደት ለፍፃሜ እንድታበቁት እንማጸናለን።

4ኛ. የተፈጠረው የአስተዳደር ልዩነት ተወግዶ ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድነት ሊያመጣ የሚችል ጥንቃቄ የተሞላበት የመፍትሄ ውሳኔ እንድትወስኑ አደራ እንላለን።

አምላካችን እግዚአብሔር የተፈጠረውን መለያይት አስወግዶ እና የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ወደቀደመ ቦታው መልሶ በአንድነት እንድናገለግል እና እንድናመሰግነው ያበቃን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁን።

እግዚአብሔር አምላካችን ሃገራችንን እና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ የሐመረ ኖኅ ኪዳነምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በላስ ቬጋስ ካህናት እና ምዕመናን።

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment