Saturday, December 22, 2012

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ።



ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።”
      (DEC. 21/2012ታኅሣስ 12/2005 ዓ/ም/PDF):- በዚህ ታሪካዊ የዕርቀ ሰላም ንግግር ላይ ከኢትዮጵያና ከአሜሪካ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተሰይመው የተላኩት ልዑካን በፍጹም መከባበር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት በስፋት ተወያይተዋል።

በውይይቱም ወቅት ሁለቱም ወገኖች ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገራቸው መመለስ ለዕርቀ ሰላሙ ስኬታማነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን በጋራ ተስማምተዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ቅድስት አገራቸው ገብተው፣ ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው እርሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ”፤ የሚል ሲሆን የዚህ ፍሬ ሐሳብ አመክንዮ ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ ታሪክ ይፋለስብናል የሚል ነበር።  

በአንጻሩ ደግሞ በውጭ አገር ያሉት ልዑካን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሲባል “ቅዱስነታቸው ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው” ሲሉ አያይዘውም ፓትርያርክ እያለ ሌላ አዲስ ፓትርይርክ መሾም ነገም በቤተ ክርስቲያን ላይ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ይደርጋል፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ በማን አለብኝነትና በግድ የሌሽነት የሚሾመውም ሰው ፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፤ ይልቁንም ሹመቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን  አንድነት ፈጽሞ ያጠፋል፣ ልዩነቱንም ያከፋዋል የሚል ነበር። ስለዚህ ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ አሁን በራሳችን ለመወሰን ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ሰይሞ ወደላከን አካል ተመልሰን ጉዳዩን በስፋት አስረድተን እንደገና የምንገናኝበትና የዕርቀ ሰላሙን ውይይት የመጨረሻ ምዕራፍ የምናደርስበት ቀጣይ አራተኛ ጉባኤ በቅርቡ ያስፈልገናል ሲሉ ለሰላምና አንድነት ጉባኤው ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ጉባኤው ከልዑካኑ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት አራተኛው ጉባኤ ከጥር 16-18 ቀን 2005 ዓ.ም(Jan 23-26/2012) በሎስ አንጀለስ፤ ካሊፎርኒያ እንዲካሔድ ሐሳብ አቅርቧል፤ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያቀረበውን ሐሳብ  የሁለቱም ወገን  ልዑካበአንድ ድምፅ ተቀብለው ተስምተውበታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የግራ ቀኙን ፍሬ ሐሳብ በጥሞና አዳምጦና ጉዳዩንም በጥልቀት መርምሮ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሥምረት ይበጃል ብሎ ያመነበትን ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ለልዑካኑ በጽሑፍ አቅርቧል።

የሰላም ልዑካኑም በንባብ የቀረበላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ እኛ ወሳኝ አካላት ባለመሆናችን በሁለታችንም በኩል በቅርቡ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲደረግና የሰላምና አንድነት ጉባኤው ሦስት ሦስት ልዑካንን ወደ ሁለታችንም ልኮ የመፍትሔ ሐሳቦቹን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅርበው እንዲያስረዱና ተገቢው የማግባባት ሥራ እንዲሠሩ እንዲደረግ በፍጹም ቅን ልቡና አስተያየታቸውን በመስጠት በወርኃ ጥር በሚካሔደው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሲሉ ስምምነታቸውን በአጽንዖት ገልጸዋል። ከዚህም ጋር የዕርቀ ሰላሙ ድርድር ከፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ በሁለቱም በኩል ለሰላምና አንድነቱ ሒደት እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም ድርጊቶች ከመፈጸም በተለይም ደግሞ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትና ሢመተ ፓትርያርክን የመሰሉ ተግባራትን ከማከናወን እንዲቆጠቡና በትዕግሥት እንዲጠብቁ በጋራ ተማምነውና ተስማምተው በፊርማቸው አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያሉት አባቶች ሰይመው የላኳቸው የሰላም ልዑካን እንኳን ገና ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለሱ፣ የዕርቀ ሰላሙን ውይይት ሪፖርት ሳያቀርቡና በቀጣዩ ጉባኤ አበው ላይ በጋራ የሚመከርባቸውን ዐበይት ጉዳዮች ሳያቀርቡ ኃላፊነት በማይሰማቸውን የመንጋው እንባና ጩኸት በማይገዳቸው ጥቂት የሲኖዶስ አባላት ግፊት አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ ከትናንት በስቲያ በመሰማቱ የሰላሙ ሒደት ከፍተኛ እንቅፋት ገጥሞታል። የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ተስፋም እንዲጨልም እየተደረገ በመሆኑ በእጅጉ አዝነናል።

የሰላምና አንድነት ጉባኤውን የሦስት ዓመት ጥረት ዋጋ ለማሳጣት  ጥረት በሚደርጉ ጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ጉባኤው በእጅጉ አዝኗል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በእኒህ ጥቂት ግለሰቦች አማካይነት አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ወደከፋና መፍትሔ ወደማይገኝለት ችግር እዳያስገቧት ከፍተኛ ሥጋት አድሮበታል። ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን የሰላምና የአንድነት በር ለመዝጋት ከመጣደፍ  እንዲታገሡና ወደማስተዋል እንዲመለሱ በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም በአጽንዖት እናሳስባቸዋለን። ይልቁንም የሀያ ዓመታቱ የልዩነት ችግሩ ሳይፈታ ሌላ ፓትርያርክ መሾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትንና በመላው ዓለም የሚገኙትን ኦርቶዶክሳውያን ካህናት፣ ምእመንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን የመከራ ቀን ማራዘምና የክርስቶስን መንጋ ከመበተን ያለፈ አንዳችም ፋይዳ እንደማይኖረው እየታወቀ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚለው ኢቀኖናዊ አመለካከት ሊታሰብበት ይገባል። ስለሆነም ሰላምና አንድነት የራበው፣ ፍቅርና መተሳሰብ የጠማው፣ መለያየት የሰለቸው መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድምፁን አሰምቶ እያለቀሰና እየጮኸ በማን ላይና ለማንስ ነው አባት የሚሾመው! አሁንም አባቶች የሕዝባቸውን ድምፅ በማስተዋል እንዲሰሙ በአጽንኦት እንጠይቃለን።
በመሠረቱ ሰላምና አንድነት የማንንም ክብርና ታሪክ አያጎድፍም፤ ይልቁንም የአባቶችን ሕልውናና ክብር የሚሽረው ሕያው ታሪካቸውንም የሚያጠፋው ሰላም ባጣችና በተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር ነው። በመሆኑም አባቶቻችን ላከበረቻቸው ቤተ ክርስቲያን ዋጋ ሊከፍሉ፣ ለአንድነቷና ለክብሯ ፍጹም ጸንተው ሊቆሙና ስለ ነገውም ትውልድ ሊያስቡ ሲገባቸው አለመታደል ሆነና እያየንና እየሰማን ያለነው ግን የተገላቢጦሽ ነው። “የአባቶችን ልጅ ለልጆች፥ የልጆችን ልብ ለአባቶች” ተብሏልና። አባቶች አደራቸውን ለመወጣት ጥረት ሊያደርጉና ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ተግተው ሊሠሩ ሲገባ የቤተ ክርስቲያንን የሰላምና አንድነት በር ለመዝጋት የሚተጉ ጥቂት ሊቃነ ጳጳሳት ታላቋን ቤተ ክርስቲያን ወደ ከፋ የችግር አዘቅት ውስጥ ለማስገባት ሲታገሉ ማየት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በእጅጉ የሚያሳፍር ሆኗል። የሊቃነ ጳጳሳቱንም የአመራር ብቃትና የቅዱስ ሲኖዶስን አርቆ አሳቢነትም ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

ጥንታዊት ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን በታላቅ ፈተና ላይ ናት። ላለፉት 21 ዓመታት ያንገላት ልዩነት እንዲወገድና ለዘለዓለም በአንድነቷ እድትጸና ማድረግ ሲገባ ልዩነቱ ህልውናዋን እንዲፈታተን  የሚያደርግ ተግባር እየተካሄደ በመሆኑ ሁላችንም ስለቤተ ክርስቲያናችን ዝም ልንል አይገባም፣ ልዩነት ሰልችቶናል፣ አባቶቻችው እንተወጋገዙና ሕዝባቸውን እንደበተኑ ሲያልፉ ማየት ሰልችቶናል፤ የተከፋፈለችን ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን አላወረሱንም፤  እኛም የተለያየች ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ ልናስተላልፍ አይገባም እንላለን። ከ40 ሚሊዮን በላይ የሁነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ሕዝበ ክርስቲያን በጥቂት አባቶች አለመግባባት ምክንያት ለልዩነትና ለሰላም እጦት ሊጋለጥ አይገባውም፤ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኑ  ጉዳይ የማይመለከተው የቤተ ክርስቲያን ልጅ የለምና በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት፣ ሕዝበ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችናሁሉ፣ እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከዚህ የሚከተለውን መልክታችንን  በአክብሮት እናስተላልፋለን።

1)             የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድት ጉባኤ ባቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት ሁለቱም  አካላት መክረውና ተስማምተው ቤተ ክርስቲያንን እንድ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
2)             ቤተ ክርስቲያንን ከፋፋሎ ለማስቀረት የሰላምንና አንድነትን በር ለመዝጋት የሚደረገው ማምንኛውም ሩጫ ተገቶ፣ አባቶች ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ እንዲሰሩ  እንጠይቃለን።
3)           በመልካም ሂደት ላይ የሚገኘው የእርቀ ሰላም ድርድር ለፍጻሜ ሳይበቃ ስድስተኛ ፓትርያሪክ ለመሾም መዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንን ለዘለዓለም  እንደ ተለያየች እድትቀር የሚያደርግ በመሆኑ ድርጊቱ እንዲቆም በእንባና በጸሎት ሰላምን በሚጠባብቀው ሕዝብ ስም በአጽንኦት እንጠይቃለን፤ 
4)           ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነትና ሲባል መንግሥትም ባለው ኃላፊነት የዕርቀሰላሙ ድርድር ለፍጻሜ እንዲደርስ ይተባበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፤
5)            በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምዕመናን በማንቸውም ሰለማዊ መንገድ  ስለቤተ ክርስቲያን አንድነት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድትም ተገቢውን ሁሉ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
6)           የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ፍጻሜ ላይ እንዲደርስ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምዕመናን  ጸሎተ ምህላ በያሉበት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እስተላልፋለን።
«ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ስለቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ»
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment