Thursday, December 20, 2012

6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም የሚደረገውን ሩጫ ለማትደግፉ በሙሉ



መፈክራችን - “የቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ያገባኛል” የሚል ነው።

(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 11/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር20/2012/ PDF)፦ በጥቂት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፍላጎት በመዘወር ላይ ያለው የ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ተጠናክሮ በመቀጠል አሁን “አስመራጭ ኮሚቴ” በማቋቋም ትልቅ ርምጃ ተስፈንጥሯል። ለዕርቅና ለሰላም ወደ አሜሪካ የላካቸውን ልዑካን መምጣት ሳይጠብቅ፣ ይዘው ለሚመጡት ምላሽ ቦታ ሳይሰጥ አዲስ ፓትርያርክ ወደ መምረጡ እየተጓዘ ነው።


ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በአገር ውስጥም፣ ከአገር ውጪም፣ በመላው ዓለም ያለው ኦርቶዶክሳዊ ድምጹን ማሰማት እንደሚፈልግ ይታወቃል። የአቅሙን የመፍትሔው አካል መሆን ይፈልጋል። ታዲያ ምን ይሻላል?  ከጥቃቅን የጽዋ ማኅበራት እስከ ግዙፎቹ፣ ከማኅበረ ካህናት እስከ ማኅበረ ምዕመናን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚገደን መናገር የሚገባን አሁን ነው። ስለዚህም ነው ይህንን የመወያያ ርዕስ የከፈትነው። መፍትሔ የምትሏቸውን ሐሳቦች በማቅረብ፣ በየአካባቢያችሁና በየአጥቢያችሁ በአካል በመሰባሰብና በመነጋገር ለእናት ቤተ ክርስቲያናችሁ ያላችሁ አለኝታነት እንድታሳዩ ይጠበቃል። እምነት በሥራ እንጂ በምን ይገለጻል? ለመነሻ እንዲሆን ይህንን እንጠቁም። እናንተም አክሉበት።

  • መረጃውን ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን ማድረስ፣ (በስልክ የኤስ.ኤም.ኤስ መልእክቶች፣ በፌስቡክ፣ በትዊተር)፣
  • በየአጥቢያችን ድምጻችንን ልናሰማ የምንችልበት ስብስብ መፍጠር፣
  • ዜናውን ለመገናኛ ብዙኃን ማድረስ፣
  • ብፁዓን አባቶችን በስልክም በአካልም በመቅረብ ስለ ጉዳዩ ማነጋገር፣ በውሳኔው እንደማንስማማ ማሳወቅ፣ (አስፈላጊ ነው ብለን በምናምነው ጊዜ ስልኮቻቸውን በይፋ ለማቅረብ እንገደዳለን)
  • ጉዳያችን እና ዓላማችን “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ” ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን አባት የመምረጥ ጉዳይ መሆኑን ለሚመለከታቸው አካላት አለ ፍርሃትና ያለ ሥጋት መግለጽ፣
  • ከመንግሥት አካላት የተደበቀ የመሥራት ፍላጎት እንደሌለን ከወዲሁ በተደጋጋሚ መግለጽ፣
  • በአገር ውስጥ ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ለጉዳዩ ሽፋን እንዲሰጡት ማበረታታት፣
  • የውጪ አገር ኢትዮጵያውያን ሚዲያዎችም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በሚል በዚሁ ሰበብ ኢሕአዴግን ለመተቸት ሳይሆን ጉዳዩን ለክርስቲያኑ ሕዝብ በማይጎረብጥ መልክ እንዲያቀርቡት ማገዝ፣
  • ኦርቶዶክሳውያን ጡመራ መድረኮችም ዜናዎችን በትብብርና በኅብረት ለምእመኑ ማድረስ፣ 
  • በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተከታዮች በሙሉ ድምጻችንን በአንድነት ማሰማት "አባቶቻችንም የመስማት ግዴታ እንዳለባቸው ማሳየት ይኖርብናል" 
  • ሰላም ከሌለ፣ የአባቶች ስምምነት ከሌለ የሚመረጠውንም ሆነ የሚመርጡትን አባቶች በጸበላችሁ ልንላቸው ይገባል፥
  • የሰላሙ ሂደት እስከ መጨረሻው ድረስ መኬድ ይኖርበታል፣ ምዕመናን የዚህች ቤተክርስቲያን ቅንቁዎች፣ ፈርጦች  መባላችንን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል፥
  • የእገሌ ወገሌ ሳይባል ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሰላም የሁሉም ወገን ተሳትፎ ወሳኝ ነው፥
  • የሕዝብ ሚዲያዎች ከሁሉም ወገን ሊቃውንትን፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን፣ ካህናትን፣ የማኅበራት ተወካዮችን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን በማገናኘት ፓናል ዲስከሽን ያዘጋጁ፣ የምዕመናን ተሳትፎ ይጨምር፣ 
  • ከእንግዲህ በኃላ ዝም የምንልበት የቤተክርስቲያን ጉዳይ የለም፥ "የቤተክርስቲያን ጉዳይ እኛንም ይመለከተናል"
  • በውጪው ዓለም በተለምዶ ገለልተኛ፣ ስደተኛ፣ እናት ቤተክርስቲያን በማለት የተከፋፈልን በአንድነት ድምጻችንን አብረን እናሰማ፥ ሰላም . . . ለቤተክርስቲያን፣ ሰላም . . . ለምዕመናን በማለት በጋራ እንጩኽ፥

ጨምሩበት

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን። 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment