Saturday, December 22, 2012

“ከፓትርያርክ ምርጫ - ዕርቅና አንድነት ይቅደም” ስንል ምን ማለታችን ነው?



(ደጀ ሰላም ታኅሣሥ 12/2005 ዓ.ም፤ ዲሴምበር 21/2012/PDF)፦ እንደሚታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን በመስቀልያ መንገድ ላይ እንደምትገኝ ተደጋግሞ የተገለጸ ነው ዋነኛዎቹ ርዕሰ ጉዳዮች ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው ለ20 ዓመታት በውግዘት የተለያዩ አባቶች አንድ እንዲሆኑ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን፣ አንድ አስተዳደር፣ አንድ ቅ/ሲኖዶስ እንዲኖረን ማድረግ ነው። ለዚህም “ተስፋ ሰጪ” ሁኔታ ላይ ተደርሷል። ይህ ዳር እንዲደርስ እናድርግ። ሁለተኛው ደግሞ 20 ዓመት ለቆየው መለያየት ዓምድና ምልክት የነበረው የፕትርክናው ሥልጣን አንዱ የመወያያ አጀንዳ ስለሆነ ከዕርቁ በፊት ሌላ እርምጃ አይደረግበት የሚለው ነው። ይህንን በሚጋፋ መልኩ በጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ግፊትና በመንግሥት ተጽዕኖ 6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም “አስመራጭ ኮሚቴ” ተቋቁሟል። ሁለቱ አጀንዳዎች የሚገናኙት እዚህ ላይ ነው።

1.      ዕርቀ ሰላሙ ይፈጸም ማለት 4ኛው ፓትርያርክ የግድ ሥልጣኑን ይያዙ ማለት አይደለም። ሐሳቡ ውጪ በሚገኙት አባቶች በኩል የቀረበ መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል። ለውይይት የቀረበ እንጂ ውሳኔ አይደለም። ውይይት የሚደረገው “ሰጥቶ በመቀበል ሕግ” አባቶች እንዲስማሙባቸው ሁሉንም አጀንዳዎች ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጡ ማለት ነው።

2.     ምንም ቢሆን ከመለያየት አንድነት ይሻላል። ስለዚህ ዕርቁን ማስቀደሙ ተገቢ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን በመልዕክቱ አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት የሚያመጣ ዕርቀ ሰላም መፈጸም ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ከማሰብ አንጻር፣ መንጋውን ከማነጽና ሐዋርያዊ አገልግሎትን ከማቅናት አንጻር ለአባቶቻችን ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚፈለገው ዕርቀ ሰላም እውን እንዲሆንም ለእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ለእውነት፣ ለኅሊና ምስክርነት መገዛት አግባብ ይሆናል”ሲል በትክክል ያስቀመጠውን ሐሳብ እዚህ ላይ ብንጠቅስ ተገቢ ይሆናል።

3.     አንዳንድ ሰዎች ስለ 4ኛው ፓትርያርክ ሲነሣባቸው የሚደነግጡበት ዐቢይ ምክንያት “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ታሪክ ይደመሰሳል” ብለው በመስጋት ነው። እንደሚታወቀው ይህ ዕርቀ ሰላም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ የተጀመረ እንደመሆኑ ዕርቁ መሳካቱ ማንንም “የርሳቸው የቅርብ ሰው ነኝ” ባይ ሊያስደነግጠው አይገባም።

4.     ደጀ ሰላም ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን  በሚያደርጉት ተግባር ለረዥም ጊዜ ስትቃወማቸው እንደቆየች የአደባባይ ምሥጢር ነው። ስንቃወማቸው የነበረው ግን “በትክክል አልተሾሙም፣ ቀኖና የጣሱ ናቸው” ብለን አልነበረም። አይደለምም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከመንበራቸው ከተነሱ በኋላ “ባዶ መንበር አግኝተውና ተመርጠው” መሾማቸውን እናውቃለን። በወቅቱ ለተፈጸመው ጥፋት አቡነ ጳውሎስን ተጠያቂ ማድረግ ትክክል አይሆንም። በታሪክም በእግዚአብሔርም ፊት ሐሰተኛ ያስብላል። በመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት፣ በቤተ ክህነቱ ሰዎች ተባባሪነት 4ኛው ፓትርያርክ ሥልጣናቸውን ተቀምተዋል። አቡነ ጳውሎስ 5ኛ ፓትርያርክ በመሆናቸው አጠፉ ማለት ትክክል አይሆንም። ነገር ግን ቦታውን ከያዙ በኋላ በፈጸሙት ተግባር ግን (መሬት ይቅለላቸውና) ስንኮንናቸው ቆይተናል። አሁንም “እርሳቸውን እወዳለኹ” የሚል ቢኖር (በቤተ መንግሥቱ እንደሚባለው የርሳቸውን ራዕይ ለማስቀጠል) በእርሳቸው ዘመን የተጀመረውን ዕርቅ ማሳካት እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም።

5.     የዘመነ አቡነ ጳውሎስ ግርግር ሳያንስ አሁን ደግሞ ሌላ የከፋ ልዩነትና ብጥብጥ እንዲፈጠር እየተደረገ ያለው ሩጫ በእጅጉ የሚኮነን ነው። ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ እንዳሉት “በፍፁም ተቀባይነት የለውም”። ብፁዓን አባቶች ከዚህ ታሪካዊ ስህተት ራሳቸውን ነጻ ማድረግ አለባቸው። እውነቱን ተናግረው መከራውን መቀበል ካልፈቀዱ ራሳቸውን ከዚህ ውሳኔ በማውጣት ከጥፋቱ ራሳቸውን ማዳን ይኖርባቸዋል። በዘመነ ደርግ ታላቁን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ለመከራ አሳልፎ ለመስጠት በተደረገው ስብሰባና ፊርማ ላይ የነበሩ አባቶች በሙሉ ዛሬ ስማቸውና ፊርማቸው ከነታሪካቸው ይፋ እንደሆነው ሁሉ አሁንም ቀን ሲያልፍ፣ ጊዜ ሲለወጥ በዚህ ድርጊት ውስጥ ያሉት አባቶች እያንዳንዳቸው አንገታቸውን የሚደፉበት ታሪክ እንዳይቆያቸው ቢያስቡበት መልካም ነው።

6.     ፓትርያርክ መሾሙ ያደርሳችኋል። መጀመሪያ አንድ ሁኑ።

ቸር ወሬ ያሰማን፣ አሜን።
“እኔም የቤተ ክርስቲያኔ ጉዳይ ያገባኛል”
  
6ኛ ፓትርያርክ ለመሾም የሚደረገውን ጊዜውን ያልጠበቀ ሩጫ አልደግፍም

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment