Thursday, April 5, 2012

የዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት አብያተ ክርስቲያናት የአቡነ ፋኑኤልን ማስፈራርያ እንደማይቀበሉ አረጋገጡ

  • አቡነ ፋኑኤል የሀ/ስብከቱን ፀሐፊ ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን “ክህነቱን ይዣለኹ” ያሉበትን ደብዳቤ በተሐድሶዎች ብሎግ ላይ አወጡ፤
  •    ይህ ሥርዓት የሌለው “ሥልጣነ ክህነትን ማገድ” ሊቀ ጳጳሱን ከማስገመት ውጪ ትርጉም የለውም ተብሏል፤

 (ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 27/2004 ዓ.ም፤ ኤፕሪል 5/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የዋሺንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት አብያተ ክርስቲያናት “ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ወደ አሜሪካ ተመድበው ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አብያተ ክርስቲያናቱ ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመቀበል የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በሚያናጋ መልኩ፤ የፓትርያርኩ ስም በጸሎተ ቅዳሴ እንዳይነሳ በመገፋፋት፤ ሰዎች በፈለጉት መንገድ እንጂ በቃለ ዐዋዲ የሚመራ ቤተ ክርስቲያን እንዳይኖር፤ የካህናትን ክብር የሚያቃልል የቦርድ አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን እንዲስፋፋ ጥረት በማድረግ፤ በትልቅ ትጋት ሀገረ ስብከቱን ለዚህ እድገት ያበቁትን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ቀርበው ተመድቤ መጥቻለሁ ብለው ኃላፊነትን ከመቀበል ይቅ “የአብርሃምን ድንኳን” አፈርሳለሁ በሚል ስሜታዊ አዋጅ ተነሳስተው ሀገረ ስብከት የሚባል የለም  ብለው በአሜሪካ ድምጽ እስከመናገር” ደርሰዋል ሲሉ  በድጋሚ ወቀሱ። 

ቅዳሜ መጋቢት 22/2004 ዓ.ም፤ ማርች 31/2012 የተሰበሰቡት በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ፤ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፤ ምክትል ሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት፤ የሰንበት ት/ቤት፤ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች የተገኙበት ባወጡት የአቋም መግለጫ “አብያተ ክርስቲያናቱ  የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ይጠበቅ በማለታችን  የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ነኝ የሚል አባት ሊደሰት ሲገባው፤ ይህንን አቋም በመጥላት፤ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ለማዳከም መነሳሳት ከብፁዕ  አቡነ ፋኑኤል በተግባር እያገኘነው  ያለ ምላሽ ነው። ብፁዕ  አቡነ ፋኑኤል በተደጋጋሚ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤና አብያተ ክርስቲያናት የቀረበላቸውን “ወደ መንበርዎ ይመለሱ” የሚል ጥያቄ  አልቀበልም በማለት፤ በተቃራኒ መልኩ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ጠብቀው የሚያገለግሉ ካህናትን  በመደወልና በስሜታዊ ንግግር በመናገር የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲያከናውኑ የተሰጣቸውን ክህነት የፈለጉትን መፈጸም የሚችሉበት የግል ሥልጣን አድርገው በመውሰድ የቤተ ክርስቲያን መመሪያ ከሚፈቅደው ውጭ እውነትን ይዘው የተከራከሩ ካህናትን ሥልጣነ  ክህነት እይዛለሁ” ሚል መስመር በመጓዝ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።

በተለይም ብፁዕነታቸው “ሥልጣነ ክህነታቸውን ይዣለሁ” ያሏቸውን ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝን በተመለከተ የአብያተ ክርስቲያናቱ ተወካዮች ባሰሙት ሐሳብ በአንድ ድምጽ ከቀሲሱ አገልግሎት ጋር መሆናቸውን አበክረው የገለፁ ሲሆን ስብሰባ በተደረገ ማግስት ሊቀ ጳጳሱ በቃል ያሰሙት የነበረውን ማስፈራሪያ ወደ ጽሑፍ በመቀየር የውግዘት ደብዳቤያቸውን ሥልጣነ ክህነትን በማይቀበሉ ተሐድሶዎች ድረገጽ ላይ አውጥተዋል። ሥልጣነ ክህነቱ መሻር ከነበረበት ነገሩ መዞር የነበረበት ወደራሳቸው ወደ ሊቀ ጳጳሱ መሆኑን ያወሳው ጉባኤው “ሰዎችን ሊያሳዝናቸውና ፈርተው እንዲገዙለት ፈልጎ በማይገባ ቢያስር ቢያወግዘውም እርሱ (ጳጳሱ) ከእግዚአብሔር ዘንድ  የታሰረ ይሁን። ካህናትም በእውነት ይቋቋሙት” (ፍትሐ ነገሥት  አንቀጽ ፻፹፬  ረስጠብ ፳፬) የሚለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን የመግለጫው መሪ ቃል አድርጎ አቅርቧል።

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በተደጋጋሚ ደብዳቤዎቻቸውን የቤተ ክርስቲያንን እምነት በሚያራክሱ፣ ቅዱሳንን በሚሳደቡ፣ ገዳማት በእሳት መቃጠላቸውን በሚደግፉ፣ ሥልጣነ ክህነትን (የራሳቸውን ጵጵስና ይጨምራል) በማይቀበሉ የተሐድሶ የጡመራ መድረኮች (ብሎጎች) ላይ ማውጣታቸው ብዙዎችን እያስገረመ ነው። “የአጋጣሚ ወይስ ሆን ተብሎ? ከተሐድሶዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው ወይስ አብረዋቸው የሚሠሩ ተሐድሶዎች አሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች በመንሸራሸር ላይ ናቸው። ሊቀ ጳጳሱ ከሐዋሳ ግርግር ጀምሮ ከተሐድሶዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በሰፊው ሲወራ የቆየ ቢሆንም እርሳቸው ብቻ ሊልኳቸው በሚችሏቸው ደብዳቤዎች ጉዳይ ግን ነገሩ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ብዙዎች እየተቀበሉት መጥተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ሀ/ስብከታቸውን እና መንበረ ጵጵስናውን ሳይቀበሉ ሌላ ማረፊያ ካዘጋጁ ጀምሮ “ገለልተኞችን አቀርባለሁ” በሚል ፈሊጥ በሀ/ስብከቱ ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ካህናት ጋር ከመሥራት ይልቅ በራሳቸው መንገድ መሔድ መምረጣቸው ይታወቃል። የሚያሳዝነው ደግሞ “አቀርባቸዋለኹ” የሚሏቸው “ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት” በይፋ የእርሳቸውን ተልዕኮ ባለመቀበል ይልቁንም እንዳይመጡባቸው ማዕቀብ በመጣል ከሁለት ያጣች ጎመን እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ ሁኔታ ባለበት ወቅት አቡነ ፋኑኤል “ክህነት ይዣለሁ” ብለው የጻፉት ደብዳቤ ያላቸውን ዕውቀት መጠን ፍንትው አድርጎ ያጋለጣቸው ከመሆኑም በላይ “እዚህ ዘመን ላይ እንድረስ? ጵጵስና እንዲህ ይሁን?” የሚል ቁጭትን አጭሯል።

የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።  

ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment