Friday, April 6, 2012

ከክህነት ስለሚያስሽሩ ምክንያቶች አንዳንድ ነጥቦች ከፍትሐ ነገሥት


ካህናትን ከክህነታቸው ስለሚያሽሩ ምክንያቶች
አንዳንድ ነጥቦች ከፍትሐ ነገሥት
(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 27/2004 ዓ.ም፤ ኤፕሪል 5/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀ/ስብከት አዲስ ሊቀ ጳጳስ ተሹሞ ተልኳል ከተባለበት ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ በችግር ላይ ይገኛል። ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በሀ/ስብከቱ ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በቃለ ዓዋዲው መሠረት የመረጡትን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አልቀበልም ከማለት አልፈው ካህናቱን በሙሉ ማስፈራራት እና አንዳንዶቹንም “አውግዣለሁ” ማለት ጀምረዋል። ይህም መነሻ ሆኖን “ካህናትን ከክህነታቸው ስለሚያስሽሩ ምክንያቶች”፣ በደፈናው ከመሬት ተነሥተው “ክህነት ይዣለሁ” ስለሚሉ አቡነ ፋኑኤልን ስለመሳሰሉ ጳጳሳት አስቀድመው በቅዱሳን አበው የተሠራውን ሕግ በተመለከተ ፍትሐ ነገሥቱ የሚለውን ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን።


+++
ክህነ መዓረጉ ምጡቅ፣ ምሥጢሩ ረቂቅ ነው፡፡ የሰማያዊው ንጉሥ የእግዚአብሔር ወኪል ከመሆን የበለጠ ሥልጣን የለምና፤ ይህ ሥልጣን በሰማይም በምድርም የሚሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ከምድራዊው ሥልጣን የላቀ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ለመቀበል ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች እንደመኖራቸው ሥልጣኑን ያለ አግባብ ሲጠቀሙበት የተገኙ ወይም የክህነት ሥልጣን ከሚፈልገው ሕግና ሥርዓት ውጭ ሆነው የተገኙ ተሿሚዎች ክህነታቸው የሚያዝበት ወይም ከክህነት የሚሻሩበት ቀኖናም ተቀንኑዋል፡፡ ይህ ክታብ ለመጀመሪያ ዜ በ1958 ዓ.ም በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ በ1995 ዓ.ም በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተመውን ፍትሐ ነገሥት ንባብና ትርጓሜውን መሠረት ያደረገ ነው በዚህ ክታብ ላይ ለመዳሰስ የተሞከረው በፍትሕ መንፈሳዊ ካህናት ከሹመታቸው ስለሚሻሩበት ሁኔታ የተገለጸውን ለመጠቆም ነው፡፡

+++
በእንተ ጳጳሳት
ጵጵስና የክህነት የመጨረሻው ደረጃ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱ አባቶች በሁሉ ነገር የተመሠከረላቸው ነቅ የሌለባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያዛል፡፡ ዳሩ ግን አንዳንድ ጊዜ ሳይገባቸው በተለያየ ምክንያት እዚህ መዓረግ ላይ የሚደርሱ አሉ፡: የጵጵስና ማዕረግ ላይ ደርሶ ሳለ ከሕግና ከሥርዓቱ ውጭ ሆኖ የተገኘ ከክህነቱ ይሻራል፡፡ አንድ ጳጳስ ከጵጵስናው ከሚሻርባቸው ብዙ ምክንያቶች የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ተኛው ክፍል በአንጾኪያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት በአሥራ ሰባተኛው አንቀጽ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስ፣ ኢጲስ ቆጶስም ቢሆን በሥራ በመሾም በመሻር በማጥመቅ በማቁረብ በማስተማር አንድ ናቸው፡፡ ከተሾመ እኒህን መዓረጋት ከተቀበለ በኋላ ቤተ ክርስቲያን የማያገለግል ካህን አንድ ዕለት አንድ ሰዓትም ቢሆን ይሻር፡፡
ቦታውን /መንበሩን/ ትቶ ቢሔድ እሺ ብሎ ወደ ቦታ እስኪመለስ ድረስ የሀገሩ ሰዎች /በሀገረ ስብከቱ ያሉ ካህናት ምዕመናን/ ይማልዱት ለምነውት አልመለስም ቢል ከምእመናን አንድነትም ይለይ፡፡ የሀገሩ ሰዎች /የሀገረ ስብከቱ ካህናት ምእመናን/ ከለመኑት በኋላ ካልተመለሰ ይሰደድ፡፡ አንድም የሀገሩ ሰዎች ከለመኑት በኋላ ቢመለስ ከእነርሱ ዘንድ ሊያኖሩት ቢወዱ ስሙንም በጸሎት ሊያነሱ ቢወዱ ፈቃድ አላቸው፡፡ ካልወደዱ ግን ስሙንም በጸሎት አያንሱ፡፡ እሱ እንደጸለየላቸው ሊጸልዩ ይገባልና፡፡ እሱ እንዳልጸለየላቸው ሊጸልዩለት አይገባምና፡፡  (መንፈሳዊ ፍትሐ ነገሥት ገጽ 1ዐዐ)
ሐዋርያት በሦስተኛው ቀሌምንጦስ 62ኛው አንቀጽ ሁለት ጊዜ የተሾመ ይሻር እንዳልን ሳይሾም ሁለት ሚስት አግብቶ የተገኘ ተሿሚው ሿሚውም ይሻር፡፡ ሿሚው ሁለት ሚስት ማግባቱን ያላወቀ ቢሆን ተሿሚው ብቻ ይሻር፡፡
ሠለስቱ ምዕት በኒቂያ በጻፉት መጻፍ በሠለሳ አምስተኛው አንቀጽ ፈጽሞ ቂም የሚይዝ ሁል ጊዜ እስከ ማውገዝ ደርሶ ፈጥኖ የሚቆጣ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖር ይህን ቂሙን የማይተው፣ ሊያከብሩት የሚወድ ቂሙን የማይረሳ ሁል ጊዜ ፈጥኖ እንዳያወግዝ ከሹመቱ ይሻር ከማዕረጉ ይዋረድ፡፡
ሐዋርያት በሁለተኛው ምንጦስ በሃያ አራተኛው አንቀጽ ሕዝቡን የሚያስተምራቸው የሚመክራቸው በውግዘት ያይደለ ሕማማተ መስቀልን አስተምሮ አንድ የሚያደርጋቸው መምህር ይሁን አሉ፡፡ በማይገባ አይሠር፣ አያውግዝ፡፡ በማይገባ ቢያሥር ቢያወግዝ ሰዎችን ሊያሳዝናቸው በድለናል ብለው ሊገዙለት ወዶ ይህን ቢያደርግ እሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታሠራ የተወገዘ ይሁን፡፡
ካህናቱ በእውነት ነገር ይክሰሱት ሥራት ቢያጸናባቸው ሥራውን ለሊቀ ጳጳሱም ቢሆን ያስታውቁ፡፡ በእውነት ይነሱበት፡፡ ክርስቶስ በወርቅ ደሙ የተዋጃቸው ምእመናንን ይበድላቸው ዘንድ በሹመት ጸንቶ ሊኖር አይተዉት፡፡ እንዳያሳዝናቸው እግዚአብሔርን ወደ መስደብ ወንጌልን ወደመንቀፍ እንዳያደርሳቸው በሹመት ጸንቶ ይኖር ዘንድ አይተዉት፡፡ በሹመቱም አይዘዝ፡፡ ለሱ እንደሚገባው መጠን በደሉን አምኖ ቀኖናውን ተቀብሎ በበጎ ነገር ጸንቶ ይኑር፡፡ አንድም በበጎ ነገር ቀኖናውን ተቀብሎ ጨዋ ሆኖ ይኑር፡፡  /መንፈሳዊ ፍትሕ ነገሥት ገጽ 12/
የአንጾኪያ ሊቃውንት በጻፉት መጽሐፍ በአሥራ ሁለኛው አንቀጽ ተሿሚ አልፎ ሲሔድ ወደ ሌላ ሀገር ቢደርስ በዚያ ቦታ ቅስና ወይም ዲቁና ሊሾም ቢወድ የሀገሩ ጳጳስ፣ ኢጲስ ቆጶሳት ይሾም ዘንድ ሹም ብለው ካልጻፉለት በራሱ ፈቃድ ቢሾም የሾማቸው ሰዎች ይሻሩ፤ ሿሚውም ይሻር፡፡
በዕንቁራ የተሰበሰቡ ሊቃውንት በጻፉት መጽሐፍ በአሥራ ስድስተኛው አንቀጽ በሀገሩ ኤጲስ ቆጶስነት የተሾመ የሀገሩ ሰዎች ባይቀበሉት ወይም ከእነሱ ብዙዎች ባይቀበሉት በሥራው ሁሉ ጠብ ክርክር ቢሆን እሱ ከተሾመ አገር ጥለን እንሔዳለን ቢሉ /ሀገረ ስብከቱ እንለያለን/ ቢሉ በሀገሩ ቀድሞ የተመውን ቢጣሉት ይሻር፡፡
በሃያ ሦስተኛ ሐዋርያት በሦስተኛው ቀሌምንጦስ በስልሳ አራተኛው አንቀጽ ደጋግ ምእመናን ኤጲስ ቆጶሱን ቢከስሱት ኤጲስ ቆጶሳቱ ወደ ጉባኤ ሊጠሩት ይገባል፡፡ መጥቶ በደሉን ቢያምን በሠራው ሥራ ይቅጡት፡፡ ይፍረዱበት፡፡
ሐዋርያት በሁለተኛው ቀለምንጦስ፣ በሃያኛው፣ ሠለስቱ ምዕት በኒቂያ በጻፉት መጽሐፍ በሃምሳ ሦስተኛው፣ ባስልዮስ በጻፈው መጽሐፍ በአርባ አምስተኛው አንቀጽ ይችን ማዕረገ ክህነት መማለጃ ሰጥቶ የተሾማት ኤጲስ ቆጶስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን ይሻር  አሉ፡፡ መማለጃ ተቀብሎ የሾመውም ይሻር፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment