Wednesday, April 4, 2012

አምስተኛው የቤተክርስቲያን የስደት ዘመን!

በኤርሚያስ ኅሩይ
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለማችን ቀደምት ከሚባሉ ጥንታውያት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷና በግምባርቀደምነት ተጠቃሽ መሆኗ ተደጋግሞ የተወሳና ከማንም ያልተሠወረ ሐቅ ነው። ይህች ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ ተልእኮዋ በተጓዳኝ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያንንም ኢትዮጵያውያን ያሰኙ እጅግ ብርቅና ድንቅ የሆኑ እንደ ፀሐይ መመላለስ ያለመቋረጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ ሀገርና ትውልድ የሚያኮሩ መንፈሳውያትና ቁሳውያት ዕሤቶችን ፈጥራ ያስረከበች ጠብቃም ያኖረች ውለታዋ እጅግ የበዛ ቤተክርስቲያን ናት። ኢትዮጵያዊ ፊደል፣ቁጥር፣የቀን መቁጠሪያ፣ስነ  ጽሑፍ፣ግጥም፣ቅኔ፣ዜማ፣ሰንደቅ፣ባህል፣ታሪክ፣ሐውልት፣ደን፣ ወዘተ ዛሬ ኢትዮጵያውያን “የእኛ” “የራሳችን” ብለን የምንመካባቸው ብዙዎች የሌላቸው ሀብታችን ከመመካትም አልፎ ተርፎ ቀላል የማይባል የቱሪዝም ገቢ የሚዛቅባቸው ዕሤቶች ከሌላ ከማንም ሳይሆን ከዚህችው እናት ቤተክርስቲያን ያለ ዋጋ የተገኙ ገጸበረከቶች ናቸው። ይህን ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ አባል ቢሆንም ባይሆንም የሀገሪቱን ታሪክ ያጠና ወይም ምድሪቱን የጐበኘ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሊመሰክረው የሚችለው አሌ የማይባል እውነታ ነው።             
        
          በሁለት ሺህ ዓመታት ታሪካዊ ጉዞዋ ውስጥ ቤተክርስቲያኒቱ ለሕዝብና ለሀገር ያበረከትችውንና አሁንም በማበርከት ላይ ያለችውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንድ ሁለት ብሎ  ለመቁጠር መሞከር ዐባይን በጭልፋ ቀድቼ እጨርሰዋለሁ እንደማለት ነው፤እንደው  በጥቅሉ “የዕውቀት ምንጭ፣ የጥበባት ማዕድ፣ የታሪክ ድርሳን፣ የቅርስ ግምጃ ቤት አስተማሪ መካሪ አስታራቂ አጽናኝ አስታማሚ ቤተክርስቲያን የሀገርና የሕዝብ ባለውለታ!” ብል በቂ ነው ባይባልም ታላቁን አስተዋጾዋን በጥቂቱ ይገልጥዋል ብዬ አስባለሁ። ይህ የማይገባው ካለ ፊደሉን ቁጥሩን የማን ነህ? ብሎ ይጠይቅ፤ የላሊበላን ወቅር አብያተ ክርስቲያናት የማን ናችሁ? ማን አበጃችሁ? ይበላቸው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስገኘችን ቤተክርስቲያን አኖረችን ይሉታል። ለምስክርነት ችሎታዬ ያንስብኛል እንጂ እኔንም ቢጠይቁኝ ያልተበረዘ  ያልተቀየጠ ኢትዮጵያዊነት እኔነቴን ያገኘሁት ከቤተክርስቲያን ነው፤ ይህች ጨዋነትን ፣መተዛዘንን፣ ለሥራ መትጋትን፣ታማኝነትን፣መከባበርን፣ አንድነትን የምታስተምር፣ ለሀገር ሉዐላዊነትና ለሕዝብ ነፃነት ዘብ የምትቆም፣ ታሪክና ቅርስ ጠብቃ የምታኖር ቤተክርስቲያን ባትኖር ኖሮ በማንነት ፍለጋ እባክን ነበር እንጂ በዓለም መድረክ በኩራት የምመሰክረው ኢትዮጵያዊነት እንዴት ሊኖረኝ ይችል ነበር? ብዬ ጥያቄውን በጥያቄ እመልሳለሁ።
         
           እውነቴን እኮ ነው! ከማንም በላይ በታሪክም በእውነታም እናት ሆና በቅርቤ ያገኘዃት ቤተክርስቲያንን ነው፤ ጥንታዊውን ሥልጣኔ ልተርክ ብል ቤተክርስቲያን ከብዙ ድንቅ ሀገርኛ የስነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ግኝቶቿ ጋር አብራ ትወሳለች፤ የጦርነቱንም ገድል ልዘርዝር ብል በአደዋ ከታቦቷና ከካህናቷ ጋር ዘምታ የድል መዝሙር ስትዘምር ትሰማለች፥ በአዲስ አበባና በጎሬም ሰውም ምድሪቱም ለፋሺስት እንዳይገዛ አውግዛ ሐዋርያቶቿን ለመሥዋዕትነት ስትሰጥ ተገኝታለች፤ ዛሬም በክኒን ፈውስ ያላገኙ ሚልዮኖችን በጠበሏ ስትፈውስ፣ የሙት ልጆች ስታሳድግ፣ ሽማግሌ ስትጦር ፣የታሠረ ስታስፈታ፣ነዳያንን ስትረዳና ስታስረዳ በከተማም በገጠርም ያገኘዃት የማገኛት ቤተክርስቲያንን ነው። ያደረገችውን ከሞላ ጐደል እንዲህ መግለጽ ይቻል ይሆናል ያደረገችውን ከተደረገላት የዋለችውን ከተዋለላት ጋር ማወዳደር ግን አዳጋች የሚሆን ይመስለኛል። ይህን ማለቴ መቼም ምንም አልተደረገላትም ለማት ፈልጌ ወይም  የደጋጎቹን የቀደሙ ነገሥታትና ያለፉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ መልካም ሥራ ዘንግቼ አይደለም፤ የተደረገላት ሁሉ ተደምሮ ካደረገችው ጋር ቢመዛዘን የታሪክ ምንጭ ከሆኑ የብራና መጻሕፍቶቿ የአንዱ ዋጋ እንኳ የሚመጥን አልመስልህ ስለሚለኝ በዚያውም ላይ የተቀበለችውና አሁንም ዕረፍት ያልሰጣት መከራና ስደት ያሳጣትና እያሳጣት ያለው መንፈሳዊ፣ ሰብአዊና ቁሳዊ ሀብት ስንኳ ለመዘርዘር ለማስላትም አስቸጋሪ ስለሚሆንብኝ ነው።                                
      
           በታሪክ በምናውቃቸው የስደት ዘመናት በዮዲት ጉዲት እና በግራኝ መሐመድ አይሁዳዊና እስላማዊ ጂሀድ፣ በሱስንዮስ ዘመንም በሮምካቶሊካዊት ቤ/ክ ሚስዮኖች የተፈጸመውን የ8 ዓመታት ጭፍጨፋ እና በዕድሜያችን ባየነው የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለም አራማጅ በነበረው በደርግ ዘመን የተጋተችውን መራራ ጽዋ ሁሌም ስለምናስታውሰው ለጊዜው ትተን አሁን ዲሞክራሲ አለ ተብሎ በሚለፈፍበት የኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለመቀበል የተገደደችውን መከራ መቁጠር አንችልም እንጂ መቁጠር ብንችል ከላይ የገለጥሁትን አሳብ ፍንትው አድርጎ ያሳየን ነበር። እስኪ ጥቂቱን ለማስታወስ እንሞክር፦   እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከ90% በላይ ጥንታውያት አብያተ ክርስቲያናት፣ቅዱሳት ሥዕላት፣መስቀሎች፣ የብራና መጻሕፍት፣ በቤ/ክ አካባቢ ያሉ ሐውልቶች፣ የነገሥታት አልባሳትና ዘውዶች፣ታሪካዊ ሰነዶች ወዘተ ናቸው፤ ባለፉት 15 ዓመታት በባህልና በቅርሳ ቅርስ ጥበቃ ጉዳይ በሚኒስቴርነት፣በሚኒስቴር ዲኤታነትና በኮምሽነርነት የተሾሙት በሙሉ ሙስሊሞች ናቸው፥ የዚህ ተግባር ዓላማ ቅርሶች እንዲጠበቁ ወይስ እንዲወድሙ? በግልጽ ባያወድሟቸው እንኳ በቂ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ባለመደረጉ የተዘረፉት ተዘርፈዋል የቀሩትም አርጅተውና በልዘው በራሳቸው ጊዜ ለመጥፋት እየተጣደፉ ነው ምክንያቱም ተሿሚዎቹ ይህ ደንታ አይሰጣቸውም።                        
            በአሊ አብዶ የከንቲባነት ዘመን የተቀበለችውን ሌላውን መከራ እናስታውስ፤ በመጀመሪያ ደረጃ 88% የከተማው ነዋሪ የኦርቶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ነው በሚላባት አዲስ አበባ አብላጫውን ሕዝብ የማይወክል ሰው በከንቲባነት መሾም ምንም ማለት ይሆን? ሃይማኖት ሌላ መንግሥት ሌላ ሊባል ይችል ይሆናል እውነት ሊሆን ግን አይችልም ምክንያቱም ሙስሊም ነዋሪዎች በሚበዙባቸው የአፋርና የሱማሌ ክልሎች ክርስቲያን ከንቲባ ተሹሞ  አያውቅም ፤አቶ አሊም ቢሆን በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ ከ130 በላይ መስኪዶች አሠርቶ ከመውጣቱ በቀር ይህን አደረገ የሚባልለት ምንም ፖለቲካዊ ወይም አስተዳደራዊ የሥራ ውጤት እንዳልነበረው ከሥልጣን የተባረረበት የግምገማ ውጤት ምስክር ነው። እርሱ ይህን ያህል መስኪድ ባሠራባቸው በእነዚህ ዓመታት ከተማ ውስጥ በመሠራት ላይ የነበሩ አብያተክርስቲያናት ፈርሰዋል ነባሮቹም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የላችሁም በሚል ግንባታና ጥገና እንዳያደርጉ ተከልክለዋል፤ የጥምቀት በዓል ማከባሪያ ቦታዎቻቸውንም ተነጥቀዋል፤ መስኪድ እንዳይሠራ ተቃውማችኋል ተብለው ከቅዳሴ ታፈሰው ተወስደው የተደበደቡ ካህናትና ምእመናንም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ሥራው እንግዲህ ይህ ነበር፤ ታዲያ ይህ ነው የመንግሥት ሥራ? ወይስ የመንግሥት ተልእኮ ቤተክርስቲያንን ዘግቶ መስኪድ ማስፋፋት ነው? ነው ከተባለ ሰውየው ተልእኮውን በብቃት ተወጥቷል ማለት ነዋ? ታዲያ ለምን በግምገማ ወረደ ተባለ? ነገሩ ማደናገሪያ እንደነበር ግልጽ የሆነው ወህኒ ይወርዳል ተብሎ ሲጠበቅ ወደናዝሬት ሲዘዋወር ቀጥሎም በአምባሳደርነት ሲሾም ነው።
         
           ሌላው የመከራ ጽዋ በተደጋጋሚ በሐረር፣ በአርሲ፣ በጅማ በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ካህናትና ምእመናን ላይ በአክራሪ ሙስሊሞች የተፈጸመው ኢሰብአዊ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ነው፤ ከሀገር አልፎ የአፍሪካን ቀንድ ሰላም አስከብራለሁ እያለ በጐረቤት ሀገሮች ሠራዊት የሚያሰማራ መንግሥት በሀገር ውስጥ ይህን የመሰለ ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ሲፈጸም ዜጐችን መታደግ ወንጀል እንዳይሠራ መከላከል እንዴት አቃተው? ግዴለሽነት ወይስ ግብረ በላነት? ሳያጠፉ ለተቀጡት፤ ለጸሎት በቆሙበት እንደ ጐመን በሰይፍ ለተቀረጣጠፉት ወገኖቻችን ማንም አልደረሰላቸውም እንደውም በከተማ በገጠር ያለው ሕዝበ ክርስቲያን እንዳያዝን እንዳያለቅስላቸው መንግሥት አየን ሰማን ያሉትን ሁሉ እያደነ ያሥር ነበር፤ የተገደልን እኛ እንደጥፋተኛም የታሠርን እኛ፣ በግፍ የፈሰሰውን የንጹሀን ደም አሞራ የበላውን የምእመናን ሥጋ ስናስታውስ ልባችን ደም ያነባል የቤ/ክ አምላክ መፋረዱ ግን አይቀርም!
       
         ለፖለቲካ ማትረፊያ “የነፍጠኛ ሃይማኖት”፣ “የኦርቶዶክስ ጥምቀት በውኃ መንቦጫረቅ”፣ “ጳጳሳቶቿ አይረቡም” እያሉ ቤ/ክኒቱን በፖለቲካ መድረኮቻቸው ላይ ያንቋሽሹ የነበሩ የዚህ መንግሥት ሹመኞችንም ከነክፋታቸው መቼም ቢሆን አንረሳቸውም ፍርድ በእነርሱ ላይ እስኪሆን ድረስ በኀዘንና በጸሎት እንፋረዳቸዋለን ከእኛም በላይ የቤ/ክ አምላክ ለቅጣት ቀን ይጠብቃቸዋል! እየሆነ ያለውንም እናስተውል በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ በጎንደር የመጻሕፍት ትርጓሜ  ት/ቤት፣ በደብረ አሰቦትና በዝቋላ ገዳማት የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰ ብዙ ጉዳትም አደረሰ፤ አሁን ደግሞ ከ700 ዓመታት በላይ ተከብሮ የኖረውን ታላቁን የዋልድባ ገዳም ይዞታ ቆራርሶ ስኳር ማምረቻ ለማድረግ የሚደረገውን ሩጫ የተቃወሙ በገዳሙ የሚኖሩ መናንንያን ሰሚ አጥተው በተቃራኒው በአታቸው በወታደር እየተበረበረ በእንግልት ይገኛሉ። በርግጥ ለስኳር ማምረቻነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቦታ ዋልድባ ብቻ ነውን? ሌላው መሬት ለምቷል ያልለማ  ምንም መሬት የለም? ይህ ለማንም ኢትዮጵያዊ አሻሚ አይመስለኝም፤ ኢትዮጵያ ገና ብዙ ያልለማ  ድንግል መሬት ያላት ሀገር ናት ይህ አሁን በዋልድባ ገዳም ላይ የታለመው ቤተክርስቲያኒቱን ገዝግዞ ለማዳከምና ብሎም ለመጣል የሚደረግ ኢቤተክርስቲያናዊ ዓላማ ያዘለ እኩይ ተንኮል እንጂ ትክክለኛ የልማት አሳብ አይደለም። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባት የገዳማት መቃጠልና መፈራረስ የአብነት ት/ቤቶች መውደም ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው።

       ሌላው አስገራሚ ነገር መንግሥት የሕዝብን አቤቱታ ለመስማት እንኳ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው! ይህንኑ አስመልክቶ ሰሞኑን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ድምፃቸውን ለማስማት በክርስቲያናዊ ስነ ምግባር መዝሙር እየዘመሩ ወደኢትዮጵያ ኤምባሲ ቢሄዱም ቀደም ብሎ የሙስሊም ሰልፈኞችን ወጥቶ ያናገው አምባሳደሩ እኒህን የቤ/ክኒቱ አባላት ወጥቶ ለማናገር ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ ነው። እንዴ ሰዎቹ ምን እያሉ ነው? ቤተክርስቲያኒቱና ተከታዮቿ ሁሉ ወንጀለኞች ናቸው እያሉን ነው ወይስ ኢትዮጵያዊነታችንን ክደውታል? በቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመው ይህ በታሪክ ተደርጎ የማያውቅ ድፍረትና ንቀት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ምእመናን ችላ  የማይባል በደል ነው። ያምናሉ ቤ/ክናችንን ያከብሩልናል ብለን አንጠብቅም ግን እንዴት አቤቱታችንን ለማሰማት በር ይዘጋብናል? የግብረ ሰዶማውያንን መብት አከብራለሁ የሚል መንግሥት እንዴት የሰላማውያን ክርስቲያኖችን ሰብአዊና  ሕገመንግሥታዊ መብት ይቀረጥፋል? ኧረ ወገን ነገሩ ወዴት እያመራ ነው? አክሱም ላይ መስኪድ ካልተሠራ ብለው ሕዝብ ሲያደባድቡ፣ ቤ/ክ ሰብረው ገብተው ቤ/ክ ታስጥለናለች ብለው የተጠለሉ ተማሪዎችን ሲደበድብ፣ ሁከተኞች ናቸው ብለው ቤተመቅደስ ድረስ በጫማ ገብተው ምእመናን ሲቀጠቅጡ፣ የቤ/ክ ይዞታዎችን እየነጠቁ ለባለሀብቶች ሲሸጡና ይህን የመሰለውን ብዙ ጥፋት ሲያደርሱ ዝም ስላለን ትዕግሥታችን ከልክ ስላለፈ አይመስላችሁም እዚህ የተደረሰው? ሰዎቻችንን ኦነግ፣ ነፍጠኛ፣ ከዳተኞች፣ ቦዘኔዎች ወዘተ እያለ ከጨረሳቸው ገዳማትና አድባራቱንም በልማት ስም እየቆራረሰ ከወሰደ ለእሳት ቃጠሎና ለአክራሪ ሙስሊሞች ሰይፍ ከሰጠ እንግዲህ ምን ዓይነት ቤ/ክ ናት ልትኖረን  የምትችለው? የወታደር ማሠልጠኛ ካምፖችን ገንዘብ እያሳዩ ፍላጎታቸውን ሊያስፈጽሙ ደፋ ቀና ለሚሉ የእስልምና አስፋፊ ዐረቦች ለሥልጠና የሚያከራይ መንግሥት ለብዙ መቶ ዓመታት የኖሩ ገዳማትን ሊነጥቀን ከተነሣ ይህ በርግጥ መንግሥት ነው ወይስ ፀረ ቤ/ክ ጂሀዲስት? እኔ በበኩሌ የኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለቤ/ክ ህልውናዋን አደጋ ላይ የጣለ ክብሯን ዝቅ ያደረገ 5ኛው የስደት ዘመን ሆኖ ነው ያገኘሁት! 
    
           ጎበዝ ይህ ችላ የሚባል ጉዳይ አይመስለኝም የመጀመሪያዎቹ የኢህአዴግ ተዋጊዎችም ቢሆኑ የተዋጉት ቤ/ክንን ለማውደም በተቃራኒው ለአክራሪ እስልምና መስፋፋትና ቤ/ክንንና ምእመናን እንዲያርዱና እንዲያቃጥሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንዳልሆነ መገመት አያዳግትም። አሁን ሁኔታው ተለውጦ አመራር ላይ ያሉ የገንዘብ አምሮት ያሰከራቸው ግለሰቦች ቤ/ክንን እንደ ግራኝ በይፋ ሳይሆን እንደ ሰደድ እሳት ቀስ ብሎ በሚዛመት ውጊያ ሊበትኗት ቆርጠው ከተነሡ ከእንግዲህ በዘርና በፖለቲካ እየተሳበበ መጥፋቱ ቢበቃና ማንንም የማትነካ ቤ/ክናችንን አትንኩብን አትድፈሩብን ለማለት ጊዜው አሁን ይመስለኛል። ወታደርወገኖቻችንስ ቢሆኑ የራሳቸው የሆነ ሚዛናዊ አመለካከት እንዳይኖራቸው ተከልክለዋል እንዴ? ታዝዘን ነው ምን እናድርግ እያሉ እስከመቼ ድረስ ነው ቤ/ክንን ሊጠብቋት ሲገባ ባነገቡት ጠመንጃ ሲኮረኩሟት የሚኖሩት? እግዚአብሔር የለም የተባለበት የኮሚኒስቶቹ ጊዜ እንዳለፈ ሁሉ ይህም ጊዜ እኮ ያልፋል ነገ ሌላ  ቀን ይመጣል ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ይከፈታል ታዲያ ያኔ አያስተዛዝብም?፤ ማንም የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ ጠባያችን በሃይማኖት ፣በእናትና በሀገር ቀልድ የለም ማለታችን ነበር እኮ የሀገሩን መሬት ለዐረብና ለፓኪስታን ነጋዴዎች የሚቸረችር ነጋዴ መንግሥት ለሕዝብ አሳቢ መስሎ  ለልማት ነው እያለ  ቤ/ክንን ሲያጠፋ  ለዚህ ፀረቤ/ክ ተልእኮው ተባባሪ መሆን በታሪክም በእግዚአብሔርም ተጠያቂ ማድረጉን ሊዘነጉት አይገባም። ዝቋላ ደብረ አሰቦት በእሳት ከተሞከሩ ዋልድባ በስኳር ስም ከታረሰ ነገ ደብረሊባኖስ ላሊበላ ሐይቅ ጣና ለመስኖ  ወይም ለፓርክነት ተፈልጓል ብሎ ማፈናቀሉን መቀጠሉ አይቀሬ ነው ይህ ደግሞ የማንን ፍላጎት ለማርካት እንደሆነ ግልጽ ነው።  ወገን ከሃይማኖት የበለጠ ዘመድ ከቤ/ክ የቀረበ ቤተሰብ ያለን አይመስለኝም ዝምታውን ትተን ውጊያውን ልንዋጋው ያስፈልጋል በዕብሪት የተወጠረ በፍቅረንዋይ የሰከረ የመሪዎቻችንንም ልብ እንዲያስተነፍስልን አባቶች ቢያውጁልንም ባያውጁልንም በያለንበት ምሕላ ልናደርስ ይገባል ብዬ አምናለሁ ምን ይመስላችኋል?። ስደት ለአሳዳጆች ውርደት ለአዋራጆች!
                                           
                                                         ቸር ወሬ ያሰማን
                           
                                                         ኤርምያስ ህሩይ              
                                           

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

1 comment:

  1. ስደት ለአሳዳጆች ውርደት ለአዋራጆች!

    ReplyDelete