Monday, April 9, 2012

ለቪኦኤ የተናገሩት የዋልድባው አባት በፖሊስ እየታደኑ ነው

·         ያሉበትን ካልጠቆማችኹ በሚል ሦስት ገዳማውያን ታስረው ተፈተዋል::
  • እስሩና ‹አደኑ› የቤተ ሚናስ መነኰሳት በተለይም ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ለሚደርስባቸው ልዩ ጫና ግልጽ አመልካች ነው ተብሏል::
  • በ1980 ዓ.ም የገዳሙን ሰሜናዊ ክፍል (በእንስያ ወንዝ) የጦር ካምፕ ለማድረግ የተቃጣው ሙከራ ኅቡኣን አበው ኵናት መወገዱ ተነግሯል::
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 29/2004 ዓ.ም፤ April 7/2012 READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የመንግሥት ባለሥልጣናት በዋልድባ አብረንታንት ገዳም ዘቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳት ላይ ከሚያደርሱባቸው ወከባና ማስፈራሪያ እንዲታቀቡ እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሦስት የገዳሙ ማኅበር አባላት በፖሊስ ታስረው መፈታታቸው ተሰማ፡፡ መነኰሳቱ ለእስር የተዳረጉት “ለቪኦኤ መግለጫ የሰጡት አባ የት እንዳሉ ተናገሩ” ከሚል የፖሊስ ጥያቄ ጋራ በተያያዘ መሆኑን ምንጮቻችን ከስፍራው ዘግበዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ መረጃ ኮማንደር በየነ በሚባል የፀለምት ወረዳ ፖሊስ መጋቢት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ከገዳሙ የተወሰዱት ሦስቱም ታሳሪዎች በገዳሙ በዲቁና የሚያገለግሉ ሲሆኑ ከሦስቱ ሁለቱ መናንያን መሆናቸው ተገልጧል፡፡

በደረሰን መረጃ መሠረት መጋቢት 23 ታስረው ከሁለት ቀናት በኋላ የተለቀቁት ገዳማውያን በስም ዝርዝራቸው ዲያቆን ገብረ ጊዮርጊስ /መናኝ/፣ ዲያቆን ገብረ ትንሣኤ /መናኝ/፣ ዲያቆን ገብረ ሥላሴ /ረድእ/ እንደሆኑ ተረድተናል፡፡ ይህም ሆኖ በማኅበረ መነኰሳቱ ተወክለው ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የዐማርኛው አገልግሎት ጋራ ስለ ወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት አሉታዊ ተጽዕኖ ቃለ ምልልስ ያደረጉት አባ (ስማቸውን ለጊዜው በይፋ መግለፁን አልፈለግንም) እስከ አሁን የት እንደሚገኙ አለመታወቁ ተመልክቷል፡፡
እኒህ አባ አሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለ ምልልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን በማኅበረ መነኰሳቱ ሙሉ ስምምነት ከፕሮጀክቱ የተነሣ ገዳማውያኑ ያደረባቸውን ሐዘንና ጭንቀት የሚገልጽና ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአድራሻ የተጻፈውን ደብዳቤ እንዲያደርሱ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት መነኰሳት አንዱ ናቸው፡፡ ፖሊስ እርሳቸውን ለመያዝ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንደ ቀጠለ እየተነገረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት መነኰሱ በገዳሙ እንደማይገኙ ተዘግቧል፡፡
ምዕራብ ትግራይ ዞን የማይ ፀብሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ በቅርቡ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሁለቱም ቤቶች ተወክለው ወደ አዲስ አበባ የተላኩት መነኰስ በብዙኀን መገናኛ ቀርበው ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑን፣ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ስጋቶች ሊነሡ እንደሚችሉና ለምን ተነሡ እንደማይባል ነገር ግን አጀንዳው “የምቀኝነትና ኾን ተብሎ ሕዝብን ለማነሣሣት” እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡ ገዳማዊው አባ በበኩላቸው ስለተላኩበት ጉዳይ ለሚዲያ መግለጫ መስጠታቸውን በተመለከተ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ለሚዲያ የተናገርኹት ሃይማኖቴ ስላስገደደኝ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ እርሳቸው ለቪኦኤ ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎና አሁን በፖሊስ ከሚደረግባቸው ክትትል ቀደም ብሎ “እውነተኛ የገዳሙ መነኵሴ አይደሉም፤ በገዳሙም አይኖሩም” በሚል ስለተነዛባቸው ስም ማጥፋትም “ያመነኰሱኝ አባት በገዳሙ ይገኛሉ፤ የኔ ቆብ ከመርካቶ የተሸመተ አይደለም፤” ብለው መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡ በዕርግና ምክንያት ከአበምኔት ሓላፊነታቸው የተገለሉት መምህር አባ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ አባትም ይህንኑ ቃላቸውን ለሬዲዮ ጣቢያው ማረጋገጣቸው ተዘግቧል፡፡
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ውዝግብ ወዲህ ክልላዊ የአስተዳደር አካላት በተለይም የቤተ ሚናስ ማኅበረ መነኰሳትን “በሽሬ፣ ወልቃይትና ፀገዴ ለተቃዋሚዎች ቀስቅሳችኋል” በሚል የሚያደርጉባቸው ተጽዕኖ የተለያዩ ሰበቦችን ሽፋን በማድረግ ከመቀጠሉም በላይ እያደር እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በሌላ በኩል ለመነኰሳቱ ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወገኖች ገዳማውያኑን በመጥቀስ እንደሚናገሩት÷ እነአባ አቤቱታቸውን ለክልልና የዞን አስተዳደር ቢሮዎች፤ ለአህጉረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በግልባጭ÷ ለፌዴራል መንግሥቱ ርእሰ መስተዳድር አቶ መለስ ዜናዊ በአድራሻ ለማድረስ አነሳስቷቸዋል ብለው ከሚያምኗቸው የማይዘነጉ አጋጣሚዎች መካከል ሁለት ታሪካዊ ክዋኔዎችን ይጠቅሳሉ፡፡
አንዱ ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግ በሚድበት በ1980 ግድም የሆነ ነው፡፡ የመረጃው ምንጮች ቁጥራቸው “ከአንድ ሺሕ አያንሱም” በሚል የሚገምቷቸው ኢሕአዴግ ታጋዮች የእንስያን ወንዝ ድልድይ ተሻግረው ወደ ገዳሙ ገብተው ሰፈሩ፤ ገዳሙ አምሳለ ጦር ሰፈር /ካምፕ/ ሆነ፡፡ በዚህም ገዳማውያኑ በእጅጉ ቢያዝኑ ከታጋዮቹ 80 ያህሉ ሞተው ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም ጥቂቶቹ ለቅዱሱ ቦታ የማይገባ ተራክቦ ሲፈጽሙ የዞረባቸው ዘንዶ ትንፋሽ ያልፈሰፈሳቸው ሲሆኑ የተቀሩትም ቦታው አይረክስም የሚሉ ኅቡኣን ኵናት የቀሠፋቸው ናቸው፡፡ መነኰሳቱ የገዳሙ ክብር የተገለጠበትን ይህን ፍትሐ እግዚአብሔር (ተግሣጽ) ለህወሓት/ኢሕአዴግ ሊቀ መንበር በማለበም፣ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ዐቃጅና ተግባሪም ፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ የፕሮጀክቱ አግባብነት እንዲፈተሽ ማሳሰብ በሚል ቀናነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ/ በአድራሻ ለመጻፍ እንደቆረጡ ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡
ለቤተ ክህነቱ አካላት በግልባጭ ብቻ ከማሳወቅ በቀር በአካል ያልሄዱበት ምክንያት ደግሞ ገዳማውያኑ ቢያንስ ከ16 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያመለክቱበት ለነበረው ችግራቸው ተቋሙ መፍትሔ ሊሰጣቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ይኸውም በሁለት ክልላዊ መስተዳድሮች የባለቤትነት ውዝግብ መካከል የቆየው የዋልድባ ገዳም “ለጸጥታ አጠባበቅ እንዲያመች” በሚል እስከ ዳልሽሓ እና ሰቋር ድረስ ያለው ወደ አማራ ክልል ከማኅደሮ ወዲያ ያለው የገዳሙ ክፍል ደግሞ ወደ ክልል ትግራይ እንዲሆን በ2000/01 ዓ.ም መወሰኑን ምንጮቻችን ያስረዳሉ፡፡
ይህም ኹኔታ በቀድሞው መንግሥታት ወቅት ልዩ ሥራ እንዳይሠራበት በዐዋጅ ተከብሮ የቆየው የገዳሙ ክልል ከብቶች እንዲሰማሩበት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዕጣን መቃሪዎች (ለቃሚዎች) እና ወርቅ ጫሪዎች (ቆፋሪዎች) በተለይ በማይ ሰሪ ወንዝ በኩል ያለከልካይ አልፈው ጎጆ ቀልሰው እንዲሰፍሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ በዚህም በበጋ ወቅት መንሥኤው በማይታወቅ ቃጠሎ በየጊዜው የሚጠፋው ደን ሳያንስ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸው ዕፀዋት ፈልሰዋል፤ የማር አዝመራ የሚቆረጥባቸው ዕፀዋት ሳይቀሩ እረኛው በልምላሜ እየቆረጣቸው በቁማቸው ደርቀው ቀርተዋል፤ የግሑሳን መሳፈርያ የነበሩ የዱር እንስሳት ተሰደዋል፤ መንፈሳዊ ተጋድሎና ቅድስና ሽተው ዓለሙን ንቀው የመጡ አባቶችም ተረብሸዋል፡፡
ማኅበረ መነኰሳቱ ይህንኑ ችግራቸውን መጋቢት 27 ቀን 1989 ዓ.ም በገዳሙ ለተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ በወቅቱ አበምኔት መምህር አባ ተጠምቀ ገብረ ኢየሱስ በኩል አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 1989 ዓ.ም ታትሞ የወጣው ልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ መጽሔት “ከአምስቱ ፓትርያሪኮች ዋልድባን ለመጎብኘት የመጀመርያው ናቸው” በተባሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት በአበምኔቱ የተሰጠውን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርቦት ነበር፡-
“. . . ወኵሉ ፍጥረት ተፈሥሓ በምጽአትከ ባለው መሠረት በቅዱስነትዎ መምጣት ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶናል፤ ደስታውም የእኛ ብቻ ሳይሆን የዓለሙ ሁሉ ደስታ ነው፡፡ በዚህ ገዳም ያለፉት ቅዱሳን አባቶቻችን በመንፈስ እየተደሰቱ ነው፡፡ አባትዎ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ‹መጥቼ አየዋለኹ› በማለት ተስፋ ሰጥተውን ነበር፤ ነገር ግን እንዘ ወልድየ አንተ ኮንከኒ አበ እንደተባለው እርሳቸው በመንፈስ እርስዎ በአካል በመምጣትዎ ተድስተናል፡፡ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፡- ከዚህ ቅዱስ ስፍራ ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መጥተው ከስውራኖች[ኅቡአን] ጋራ የተነጋገሩት ከዚህ ገዳም ነው፤ ቀጥሎም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ 70 ዓመት ተቀምጠው ዐርፈውበታል፤ እንዲሁም በእርሳቸው እግር የተተኩ ብዙ ቅዱሳን ፈልሰውበታል፡፡
ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ካሉት ገዳማት ቀዳሚነት ያለውና ተወዳዳሪ የሌለው ገዳም ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ቦታም ብዙ የበርሓ አራዊት ይገኙበታል፡፡ እንደ ድሮው አንበሳ እንኳ ባይገኝ እንደ ነብር፣ አጋዘን፣ ወደንቢ፣ ድኵላ. . .በብዛት ይገኙበታል፡፡ አሁን ግን ችግሩ ይህ የቅዱሳኖች ዋሻና የአራዊት ደን ቦታችን የከብቶች ማሰማሪያ በመኾኑ ቅዱሳኖች በመረበሽ አራዊቱም በመሰደድ ላይ መኾናቸው እንዲታወቅልን እንወዳለን፡፡. . .ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፡- . . . በየቦታው ርዳታ ማድረግና የልማት ዘርፎችን መዘርጋት ልማዱ የኾነው ቅዱስነትዎ ረድኤትና ጸሎት በማንኛውም ወቅት ከገዳማችን እንዳይለይብን እንጸልያለን በማለት አሳስበዋል፡፡”
እንደ መጽሔቱ ዘገባ ፓትርያሪኩ በወቅቱ ለገዳሙ መናንያንና አገልጋዮች መነኰሳት የኀምሳ ሺሕ ብር የገንዘብ ርዳታ፣ መስቀሎችን፣ ጃንጥላዎችን፣ መጎናጸፊያዎችንና ምንጣፎችን የመሳሰሉ የንዋየ ቅድሳት ስጦታ፤ በራሳቸው የሚገለገሉባቸውን የራስ አክሊል፣ የደረት አይከን፣ የእጅ አርዌ ብርትና ሙሉ አልባሳት ለገዳሙ መገልገያ ይኾን ዘንድ ጨምረው አበርክተዋል፡፡
ይኹንና ፓትርያሪኩ በቤተ ክርስቲያን ስም እንደሰጡት የተገለጸው የብር ርዳታ ይቅርብን ወይስ እንቀበል በሚል አነጋግሮ እንደነበረው ሁሉ በቃለ ቡራኬያቸውም ወቅት፡- “ገዳሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከመናንያኑ የቋርፍ ምግብ በስተቀር እህል ውኃ ስለማይቀመስበትና ሴቶች እስከተወሰነ ቦታ ድረስ ስለማይገቡበት መንፈሳዊውን አገልግሎት በአንድነት ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ የቆየ በመሆኑ ወደፊት ለሁሉም በሚያመች አማካይ ስፍራ ሁሉም በአንድነት አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ” ሲሉ በትግርኛም በአማርኛም የሰጡት መምሪያ በማኅበረ መነኰሳቱ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬና ቍጣ ቀስቅሶባቸው እንደነበርም የመረጃው ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡
አሁን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት በፕሮጀክቱ ላይ የሚቀርቡትን የመነኰሳቱን ስጋት አለመልካቸው መልክ መስጠታቸው “ሁሉም አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተ ክርስቲያን ይሠራ” በሚል ሽፋን የገዳሙን ሥርዐት ለመከለስ የሚሹትን የአቡነ ጳውሎስን መመሪያ በስኳር ፋብሪካ ግንባታና በሸንኮራ ልማት አጋጣሚ ለማሳካት የሚደረግ መፍጨርጨር ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በገዳማውያኑ ጸሎትና ሕዝቡ በጻፈላቸው ግልጽ ደብዳቤ ተፈጻሚ ሳይሆን መቅረቱ በሚነገርለት በዚሁ የአቡነ ጳውሎስ መመሪያ አዝነውና አልቅሰው በወቅቱ ፓትርያሪኩን ፊት ለፊት የተቃወሙና ያስጠነቀቁት (ከቤተ ጣዕማም ከቤተ ሚናስም) እንደ አባ ተስፋ ሚካኤል፣ አባ ቃለ ጽድቅ እና አባ ገብረ ሥላሴ የተባሉ አበው መነኰሳት በፓትርያሪኩ ባለሟሎች ‹እብዶች› በሚል ተዘልፈው እንደነበርም ምንጮቹ አይዘነጉም፡፡
ጥቡዐኑ መነኰሳት የተቆጡት “ሰምተነው አናውቅም” ባሉት በዚሁ የፓትርያሪኩ ንግግር ብቻም አልነበረም፤ በጉብኝቱ ወቅት “ገዳሙን የጦር አውድማ አስመስሎት ነበር” በሚል የተነቀፈው ለአቡነ ጳውሎስ የተደረገ ወታደራዊ እጀባ እና ውጠራም ጭምር እንጂ፡፡ ይኸው በ1989 ዓ.ም ለሃይማኖት አባት ሊደረግ ከሚያስፈልገው በተጋነነ መልኩ ታይቶ የነበረው የኀይል ስምሪትና ውጠራ ፓትርያሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ገዳሙ በመጡበት 2002 ዓ.ም ከበፊቱ በተጠናከረ አኳኋን መደገሙ በተአምኖ እግዚአብሔር ብቻ ላይ ጸንተው የኖሩትንና የሚኖሩትን አበው ልብ በእጅጉ ያሻከረ እንደሆነ ነው ምንጮቹ ለማብራራት የሚሞክሩት፡፡
እናሳ? በአጠቃላይ በዘላቂ ሥነ ልማት አስተምህሮ አግባብ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ተጽዕኖው በሚዛን ታይቶ ቢታቀድ፣ መንግሥት እንደሚለው የአገር ውስጥ ስኳር ፍጆታን ከማሟላት አልፎ በዓለም አቀፍ ገበያ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘት፣ የኢንዱስትሪ ልማቱን በማስፋፋት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥና የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ የሚጠቅመው የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ÷ የገዳሙን ህልውናና ክብር የሚፈታተን፣ ከዚህም አልፎ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች ጋራ እየተሸመነ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መለዮ የኾኑ ገዳማትን የማጥፋት ተልእኮ ተደርጎ ባልተወሰደ ነበር !!
ቸር ወሬ ያሰማን
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment