Saturday, November 12, 2011

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከፍተኛ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል


ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል


ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከፍተኛ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል፣ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜን አሜሪካን የቤተ ክርስቲያን ችግር ንክኪ የሌለባቸው አባቶች እንዲመድብ ፊርማ እየተሰባሰበ ነው

 READ IN PDF
የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 02/2004 ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገቡነት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚጠብቃቸ እየተነገረ ነው:: ብፁዕነታቸው ከዚህ በፊት የሰሩዋቸው ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባራት በዚህ አካባቢ በሰፊው የሚታወቅ ስለሆነ ተቃውሞው የከፋ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል:: በሰሜን አሜሪካ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ማኅበር፣ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት፣ በገለልተኛ አስተዳደር ስር የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና በሰሜን አሜሪካ የማኅበረ በዓለ ወልድ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል ተብሎዋል:: “የግል ቤተ ክርስቲያን ያለው አባት እንዴት ቤተ ክርስቲያን አንድ ሊያደርግ ይችላል”? የሚል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑም እየተነገረ ነው::


የተሐድሶ መናፍቃን ልሳን የሆነው “አባ ሰላማ” ብሎግ ለብፁዕነታቸው አቀባበል እንደሚደረግ ዘግቧል:: ይህ የመናፍቃኑ ብሎግ የተዋሕዶ አንደበት እንዳልሆነ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እስከነ ማስረጃ አቅርበን ነበረ:: “አባ ሰላማ ብሎግ” እመቤታችን  ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ጻድቃንን፣ ቅዱሳን መላእክትን ይሳደባል:: እንዲሁም ደግሞ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ይተቻል:: ለምሳሌ ይህንን በማጫን አንብበው ይታዘቡት:: አባ ሰላማ ብሎግ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ዘግቦዋል:: ይህ የተሐድሶ መናፍቃን ብሎግ “ለምን ይሆን እነ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እና አባ ሰረቀ ብርሃንን የሚደግፈው”?? ከአባ ሰረቀ ጋር እንኳ  የዓላማ አንድነት አላቸው:: ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤልስ? መልሱን ግዜ ይፈታዋል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ እጅግ ባጣም ውስብስብ ችግር ውስጥ እንደሆነች ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል:: ለዚሁ ውስብስብ ችግር ውስጥ መግባት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል አንዱ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ናቸው:: በሰሜን አሜሪካን በአስተዳደር ወደ ሰባት አይነት የሚደርሱ አጥቢያ አቤያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ:: ለምሳሌ ያህል:-
1. ራሱ ስደተኛ ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራው ቡድን ውስጥ የሚተዳደሩ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት፣
2. ራሳቸው “ገለልተኛ” ነን በማለት የሚጠሩ በገለልተኝነት የሚተዳደሩ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት፣
3. በግለሰብ ስም የአባ ኤገሌ ወይም የአቶ ኤገሌ ተብለው የሚጠሩና በግለሰቦቹ የሚተዳደሩ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት፣
4. ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንቀበላለን ነገር ግን ሀገረ ስብከት አንቀበልም የሚሉ አጥቢያ  አብያተክርስቲያናት፣
5. የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንቀበላለን ነገር ግን ፓትሪያርክ አባ ጳውሎስን አንቀበልም የሚሉ አብያተክርስቲያናት፣
6. ከአሜሪካ ውጪ በሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ወይም ቆሞሳት በበላይ ጠባቂነት ወይም በባለቤትነት የሚመሩና  የሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናት፣
7. የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር በመጠበቅ በሀገረ ስብከት የሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናት ናቸው::

ሥለዚህ ቤተ ክርስቲያን በዲያስጶራ እንደዚህ ውስብስ ውስጥ እንድትገባ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የራሳቸው ሚና ተጫውተዋል:: ብፁዕነታቸው ለክፍፍሉም የአንበሳ ድርሻ እንደሚወስዱ ብዙዎች ይናገራሉ:: የብፁዕነታቸው አጥቢያ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የጵጵስና መዓረግ ከመቀበላቸው በፊት በገለልተኛው አስተዳደር ውስጥ ነበረ:: አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ገለልተኛ አድርገውት የነበረው “አባ መላኩ” የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ናቸው:: አሁን ግን በተራ ቁጥር 5 የተገለጸው ማለትም  “የኢትዮጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንቀበላለን ነገር ግን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አንቀበልም የሚሉ አብያተክርስቲያናት” ውስጥ የሚመደብ ነው:: አጥቢያው ሀገረ ስብከትም አይቀበልም:: ቅዱስ ሲኖዶስ የመደባቸው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አይቀበልም እንዲሁም በሥርዓተ ቅዳሴው ስማቸው አይጠራም:: የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ስም ግን ይጠራል፤ ምክንያቱም ንብረታቸው ሥለሆነ::

ይህ ሁሉ ቅድመ ታሪካቸው የሚያውቀው የአሜሪካን ምእመናን እና አገልጋዮች ካህናት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የቤተ ክርስቲያን አንድነትን በፍፁም ሊያመጡ አይችሉም የሚል አቋም ይዘዋል::

በአህጉረ ስብከቱ የሚገኙ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት በሙሉ አንድነት ሊያመጣ የሚችል አባት ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲልክላቸው ፊርማ እያሰባሰቡ መሆናቸም ተሰምቶዋል:: የቤተ ክርሲቲያናችን አንድነት እንዲመጣ ከተፈለገ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሜን አሜሪካን የሚመድባቸው አባቶች ከዚህ በፊት የችግሩ ተዋናኝ፤ የክፍፍሉም ፈጣሪ የሆኑትን እንዳይላኩ መደረግ እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው:: ሥለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንን ችግር ተገንዝቦ በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች ጠይቀዋል::

ቀሲስ ታደሰ ሲሣይ
“ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አቀባበል ይደረግላቸዋል” በማለት የመናፍቃኑ “አባ ሰላማ” ብሎግ የዘገበው ከእውነት የራቀ ነው:: በእርግጥ የቀድሞ ጓደኞቻቸው እነ ቀሲስ ታደሰ ሲሣይ እና የግል ንብረታቸው የሆነው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ካህናት እየተዘጋጁ መሆኑን ማወቅ ችለናል:: ቀሲስ ታደሰ ሲሣይ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ ከላይ በተራ ቁጥር 3 ማለትም “በግለሰብ ስም የአባ ኤገሌ ወይም የአቶ ኤገሌ ተብለው የሚጠሩና በግለሰቦቹ የሚተዳደሩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት” ውስጥ የሚመደብ የራሱ ቤተ ክርስቲያን አለው:: የአጥቢያው ምእመናን ብሶት ይህን በመጫን ያንብቡ:: ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ ያለ ሀገር ስብከታቸው በነሐሴ ወር ላይ እዚሁ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ክህነት ሰጥተውበታል::


እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ይጠብቅልን!!!

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment