Wednesday, November 9, 2011

ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ

ከዳንኤል ክብረት እይታዎች የተወሰደ:

አውሮፓውያን እና አሜሪካውያን ከመቶ ዓመታት በፊት የሞራል እና የሥነ ምግባር ልዕልናን ከእምነት ተቋሞቻቸው ነጥቀዋል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በእምነት ተቋማቱ ውስጥ እና በእምነት መሪዎቹ ዘንድ የሚፈጸሙት ጥፋቶች፣ ኃጢአቶች እና
ወንጀሎች የእምነቱ ተከታዮች ከሚሠሯቸው ይልቅ እየባሱ መምጣታቸው ነው፡፡

ሴትዮዋ ጉድጓድ ውስጥ ትወድቅና ትጮኻለች፡፡ አንድ ሰው ይሰማትና ይመጣል፡፡ እጅሺን አምጭ ብሎ እጇን ጎትቶ ሊያወጣት ሲሞክር እጇን ይገነጥለዋል፡፡ ሴትዮዋ ጉድጓድ ከመግባቷ ይልቅ የእጇ መገንጠል ይብስባታል፡፡ እናም «አውጣኝ ብለው ገነጠለኝ» አለቺ ይባላል፡፡ አውጭው ከጉድጓዱ ባሰባት፡፡


የሃይማኖት ተቋማት እና የሃይማኖት መሪዎች የማኅበረሰቡን ሞራላዊ እና ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን የመጠበቅ፣ የማስተማር እና ለእነርሱም አርአያ ሆኖ የመገኘት ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ ነገር ግን «ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል» እንደተባለው ራሳቸው የእምነት ተቋማቱ እና መሪዎቹ የችግሩ ሰለባዎች ሆነው ለማኅበረሰቡ አርአያ መሆን ሲያቅታቸው፤ ሕዝቡ በእነርሱ ላይ ያለው አመኔታ፣ እነርሱም በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ይሸረሸራል፡፡

አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በእምነት ተቋማት እና በእምነት መሪዎች ዘንድ እጅግ አሳዛኝ ነገሮች እየተሰሙ ነው፡፡ የገንዘብ ዝርፊያ፣ የዘመድ አሠራር፣ ዘረኛነት፣ ጉቦ፣ የመብት ጥሰቶች፣ ማታለል፣ ለሥልጣን መታገል፣ በገንዘብ መንፈሳዊ ሥልጣንን እና ሹመትን መግዛት፣ ኢሞራላዊ የሆኑ ድርጊቶች የዕለት ተዕለት ወሬዎች እየሆኑ ነው፡፡

እነዚህ ነገሮች አደጋቸው ለእምነት ተቋማቱ ብቻ አይደለም ሀገራዊ ጉዳትም አላቸው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ሃይማኖተኛ ነኝ ብሎ የሚያምን ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ የእምነት ተቋማት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የማኅበረሰቡ የሥነ ምግባር እና የሞራል እሴቶች ምንጭ እና ጠባቂ፣ አስተማሪ እና አወራራሽ የእምነት ተቋማት ናቸው፡፡ የሀገሪቱን ቅርሶች አና ባህሎች የሚጠብቁ እነርሱ ናቸው፡፡ ለማኅበረሰቡ የበጎ ነገር አርአያ በመሆን የሞራል ልዕልና የሚያጎናጽፉ ናቸው፡፡

ሕዝቡ ስለ እምነት ተቋማቱ እና መሪዎቹ ክፉ ነገር እየሰማ በሄደ ቁጥር ግን እነዚህ ነገሮች ይቀራሉ፡፡ ከእምነት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆን ከአስተምህሯቸው፣ ከሞራል እና ሥነ ምግባር እሴቶቻቸውም ይሸሻል፡፡ ተቋማቱም ማኅበረሰቡን የመቅረጽ ሚናቸው ይቀንሳል፡፡

ይህ ሁኔታ የአይከን ለውጥ ያስከትላል፡፡ ለጨዋነት፣ ለትኅትና፣ ለንጽሕና፣ ለታማኝነት፣ ለድንግልና፣ ለትዕግሥት፣ ለይቅር ባይነት፣ አርአያ ያደርጋቸው የነበሩት የእምነት መሪዎቹ ከዚህ በተቃራኒ ሰ!ያገኛቸው ሌሎች አይከኖችን ያመጣል፡፡ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የእምነት አይከኖች ሲጠፉ ሚዲያ የፈጠራቸው አይከኖች ናቸው የተተኩት፡፡ አርቲስቶች፣ ዘፋኞች፣ የፊልም ተዋንያን፣ የፋሽን ሰዎች፣ ኳስ ተጫዋቾች፣ ወዘተ ቦታውን ተረክበዋል፡፡ እንግሊዛውያን ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በየመንደሩ የመንደሩ ጠባቂ ቅዱስ (patron Saint) የሚሉት ነገር ነበራቸው፡፡ ዛሬ የመንደሩ ጠባቂ ቅዱስ በመንደሩ ታዋቂ የእግር ኳስ ቡድን
ተተክቷል፡፡

የኛም ሀገር ዕጣ ፈንታ እንደዚህ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ሰዎች ወደ እምነት ተቋማት ሲሄዱ ከፍ ያሉ ሞራላዊ ነገሮችን ያስባሉ፡፡ እነርሱ በዚህ ዓለም ሊያደርጓቸው ያልቻሉትን ሊያደርጉ የቻሉ ሰዎችን ይፈልጋሉ፡፡ አርአያ ይሻሉ፡፡ የጽናት፣ የትዕግሥት፣ የብርታት፣ የአልሸነፍ ባይነት፣ ምሳሌ ይሻሉ፡፡ እነርሱ እንደ ሰብአ ሰገል ሲመጡ እንደ አጥቢያ ኮከብ መንገድ የሚመራቸው ይመኛሉ፡፡

ይህንን ነገር ከማግኘት ይልቅ እነርሱ ሊያሸንፉት በሚፈልጉት ነገር፣ እነርሱ በተጸየፉት ነገር፣ እነርሱ ሊጋደሉበት በሚሰለፉበት ነገር አርአያ ያደረጓቸው አካላት ተሸንፈው ሲያገኙ ሞራላቸው ይወድቃል፡፡ ተስፋም ይቆርጣሉ፡፡ አንዳንዶቹም እያደረጉት ያለው ነገር ትክክል ነው ብለው እንዲያስቡ ይሆናል፡፡

እኔ በእምነት ስም ስለሚፈጸሙ ጥፋቶች እና ወንጀሎች ማኅበረሰቡ መወያየት ያለበት አሁን ነው እላለሁ፡፡ አሁን ውይይቱ ከተጀመረ ተቋማቱን ከግለሰቦች፣ እምነቱንም ከእምነቱ መሪዎች ነጥሎ ለማየት ዕድል ይሰጣል፡፡ በዝምታ ከታለፈ ግን «ዕባብ ግደል ከነ በትሩ ገደል» የሚለው ማኅበረሰባችን ሰዎቹን ከነተ ቋማቸው ርግፍ አድርጎ ወደ መተው መዞሩ አይቀሬ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በተቋማቱ እና በግለሰቦቹ የሚፈጸሙትን ስሕተቶች መናገር ሃይማኖቱን እንደ መድፈር፣ ለጠላት አሳልፎ እንደ መስጠት፣ ገመና እንደ ማውጣት እየተቆጠረ በመምጣቱ አልባሌ ሰዎች እና አልባሌ አሠራሮች የእምነት ተቋማቱን ምሽግ አድርገው የፈለጉትን እንዲያደርጉ ዕድል እየሰጣቸው ይገኛል፡፡

ዘመኑ የሚዲያ በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ነው፡፡ በዓለም ጫፍ የተተነፈሰች ነገር በሰከንድ ወደ ሌላው የዓለም ጫፍ ትደርሳለች፡፡ እንደ ትናንቱ ነገሮችን ደብቆ ይዞ መኖር አይቻልም፡፡ ሰዎች ይሰሙታል፣ ያታል፣ ይወያዩበታልም፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ እና እየጠነከረ ሲመጣ የፍትሕ አካላትን በር ማንኳኳቱም የማይቀር ነገር ነው፡፡

አንድ በር ሲከፈት በመጀመርያ የሚወጣበት እንጂ በመጨረሻ የሚወጣበት አይታወቅም ይባላል፡፡ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት መድረስ ከጀመሩ ሌሎች የችግሮቹ ተጋላጮችም መንገዱን ይቀጥሉበታል፡፡ ይኼ ደግሞ የእምነት ተቋማቱን ሥነ ምገባራዊ እና ሞራላዊ ልዕልና ያሳጣል፡፡

በቅርቡ አንድ መነኩሴ በአንድ የ15 ዓመት አዳጊ ልጅ ላይ በፈጸሙት የግብረ ሰዶም ተግባር ልደታ የሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የ14 ዓመት ጽኑ እሥራት ፈርዶባቸዋል፡፡ ልጁ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም ሲመጣ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን እጅግ ከባድ ያደርገዋል፡፡

ይህንን የመሰለው ኢሞራላዊ ድርጊት ከሕዝቡ አልፎ ወደ እምነት መሪዎች ዘንድ መዛመቱ፣ የእምነቱ መሪዎችም ሥልጣናቸውን፣ አባትነታቸውን እና ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው እየፈጸሙት መሆኑ ለማኅ በረሰቡ እና ለተቋማቱ የመንቂያ ደውል ነው፡፡ «ጨው ለራስህ ብትል ጣፍጥ፣ ያበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው አውጥተው ይጥሉሃል» እንደ ተባለው የእምነት ተቋማቱ ያላቸውን ቦታ ከማጣታቸው በፊት ለዓላማቸው ሲሉ በፍጥነት ችግሮችን መፍታት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡

በጳጳሳት፣ በመነኮሳት፣ በአጥማቂዎች፣ በሰባክያን፣ በፓስተሮች፣ በዘማርያን፣ ዘንድ እየተሰሙ ያሉ የመብት ጥሰቶች፣ ጥፋቶች እና ወንጀሎች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ነገ አደባባይ ወጥተው የማኅበረሰቡን ቅስም መስበራቸው አይቀርም፡፡ የእምነት ተቋማቱም የመረጡት ዝምታ እና መሸፋፈን ነው፡፡ አንድ ቦታ የተወነጀለ እና የተቀጣ ሰው ወደ ሌላ ይዛወራል፡፡ በሌላ ቦታ ጥፋት የተገኘበት ሰው ወደ ሌላ ይሾማል፡፡ ችግሩን ከምንጩ የመፍታት ሥራ አልተጀመረም፡፡

በሌላም በኩል የእምነት ተቋማቱ በልዩ ልዩ የአገልግሎት ቦታ ያሠማሯቸውን አገልጋዮች ብዛት፣ ማንነት እና ተግባር አያውቁም፡፡ በስማቸው የሚሠራውን ነገር የሚከታተሉበት መንገድ አልዘረጉም፡፡ ማነው ባሕታዊ? ማነው መነኩሴ? ማነው ካህን? ማነው ዲያቆን? ማነው ሰባኪ? ማነው ዘማሪ? ማነው ፓስተር? ማነው አስመላኪ? ማነው መጋቢ? ማነው አጥማቂ? በግልጽ የሚያውቅ የለም፡፡ እነዚህ አካላት ለሚያደርሱትስ ጥፋት ተጠያቂው ማነው? እጅግ አጠያያቂ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ አባቶች ተሰባሰቡ ሲባል «ጸለዩ፣ ጾሙ፣ ተአምር አደረጉ፣ ሃይማኖት አሰፉ፣ ሥርዓት ዐጸኑ» የሚለውን አይደለም ሕዝቡ እየሰማ ያለው፡፡ ተደበደቡ፣ ቤታቸው ተሰበረ፣ ማስፈራሪያ ደረሳቸው፣ ሰልፍ ተደረገ፣ አልስማማ አሉ የሚለውን ነው፡፡ እገሌ የተባት አባት ይነሡልን፣ እገሌ የተባሉት አባት አይምጡብን የሚል ምእመን በዝቷል፡፡ ወደ የአጥቢያው ሲሄድም ሙዳየ ምጽዋት ተዘረፈ፣ ሕንፃው በዘመድ ተሰጠ፣ እገሌ በጉቦ ተሾመ፣ እነ እገሌ በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ መሬት ገዙ፣ ቤት ሠሩ፤ ንዋያተ ቅድሳት ጠፉ፣ ተዘረፉ የሚለውን ነው እየሰማ ያለው፡፡

አሁን አሁን በማኅበረሰባችን ዘንድ የምንሰማቸው እና የምናያቸው የሥነ ምግባር ጥፋቶች እና ኢሞራላዊ ድርጊቶች አንዱ መነሻ የሥነ ምግባር እና የሞራል አርአያ መጥፋት ሳይሆን አይቀርም፡፡ የእምነት ተቋማቱ ዋነኛ ሥራቸው ትተው ንግድ ወደ ማስፋፋት፣ ገንዘብ ወደ መሰብሰብ፣ ሥልጣን ወደ መቀራመት እና ቤት ንብረት ወደ ማፍራት ስለገቡ የሕዝቡን ሞራላዊ እና ሥነ ምገባራዊ እሴቶች የሚያስጠብቅ፣ አርአያ የሚሆን እና የሚያሰርጽ እየጠፋ ይመስለኛል፡፡

በማኅበረሰባችን ዘንድ ግብረ ሰዶማዊነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ሕፃናትን መድፈር እየተለመደ ነው፤ ፍች የሰዓታት ዜና እየሆነ ነው፣ በወጣቶች ዘንድ ድንግልናን መጠበቅ ነውር እየሆነ ነው፤ ከዳቦ ቤቶች ይልቅ ጫት ቤቶች እየበዙ ነው፤ ጉቦ ማሳፈሩ ቀርቶ እየተወደሰ ነው፤ አሲድ በሰው ላይ መድፋት፣ ዓይን ጎልጉሎ ማውጣት፣ በቢላዋ የትዳር ጓደኛን ማረድ፣ ልጅን ቆራርጦ መግደል እውነት የሃይማኖተኛ ሕዝብ ጠባያት ናቸውን?

የሀገሪቱ ሕጎችም የሃይማኖት ተቋማት እንደ ሕጋቸው ሳይሆን እንደፈለጉ እንዲሆኑ የሚያግዙ ናቸው፡፡ ገንዘባቸው ቁጥጥር አይደረግበትም፡፡ ግብር አለመክፈል እና ቁጥጥር አለማድረግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ገንዘብ በተዝረከረከበት ቦታ ሁሉ ወንጀል በልጽጎ መገኘቱ ደግሞ የማይቀር ነው፡፡ አወቃቀራቸው እና አሠራራ ቸውን ዘመናዊ እንዲያደርጉ፣ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲዘረጉ፣ አገልጋዮቻቸውን እና አባሎቻቸውን መዝግ በው እንዲያውቁ የሚያስገድዳቸው ነገር የለም፡፡

በተቋማቱ ውስጥ እና በአባሎቻቸው ወንጀሎች እንዳይሠሩ፣ ቢሠሩም እንዲጋለጡ የሚያደርጉ አሠራሮችን እንዲዘረጉ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ነክ ከሆኑ ጉዳዮች በቀር በሌሎቹ ላይ ግልጽነት እንዲኖር መደረግ አለበት፡፡ ከሲመት በኋላ ነገር እንዳይመጣ የሚሾሙ ሰዎች አስቀድሞ ለሕዝቡ እጩነታቸው የሚገለጥበትን፣ አስተያየት የሚሰበሰብበትን መንገድ መፍጠር ያሻል፡፡ ምእመናኑ የመ ብት ጥሰቶችን፣ ኢሞራላዊ ተግባራትን እና ወንጀሎችን የሚጠቁሙበት ግልጽ አሠራርም መስፈን አለበት፡፡

ያለበለዚያ ግን «በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርዒነ» እንደተባለ፣ ዛሬ በጭምጭምታ በጆሮ የምንሰማቸውን ነገሮች ነገ በአደባባይ ማየታችን የማይቀር ነው፡፡ ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅም በርጥቡ ማለት አሁን ነው፡፡
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment