Wednesday, November 9, 2011

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለተዋህዶ ቤተሰቦች በሙሉ

  ወቅታዊ ወሬ
           የእነ አቡነ ፋኑኤልና  የአባ ሰረቀ  ግብረ ሃይል በቅድስት ሀገራችን ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠንካራ አቋምና በቆራጥ ምዕመናን ትግል ክንዳቸው ለጊዜው ተመቷል። ነገር ግን  ለረጅም ጊዜ ዕቅድ በዘረጉባት  ምድረ አሜሪካ ግን የተሳካላቸው ይመስላል። በአቡነ ጳውሎስ አዝማችነት ታምነው የሚንቀሳቀሱ አቡነ ፋኑኤል፥ አባ ሰረቀ፥  ዲ/ን ኃይለ ጊዮርጊስ እና ሌሎችም ኢትዮጵያ ባይሳካላቸውም የግብር ሃገራቸው በሆነው አሜሪካ ግን እንደዛቱት ተሳክቶላቸዋል። አቡነ ፋኑኤል ቀድሞ ከቤተክርስቲያን ተገልለው በከፈቱት የግል ቤተክርስቲያናቸ  መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም አሁን ደግሞ ለአላማቸው ሥልጣንን ከአቡነ ጳውሎስ በአድልዎ ተቀብለው ተመልሰው በአሜሪካ የፈለጉትን ለማድረግ ተመደቡ።

          እኛ እዚህ በሰሜን አሜሪካ ያለን እውነተኛ የተዋህዶ ልጆች ኢትዮጵያ ካለው ምዕመን ልዩነት እንደማይኖረን ልናሳውቅ እንወዳለን።  እርሳቸው በሐዋሳ ምዕመናን ላይ ያደረሱት በደል የኛም በደል እንደሆነ እንቆጥራለን። “እኔ አሜሪካዊ ነኝ ምንም አይጎድልብኝም  ይብላኝ ለእናንተ” ብለው ከተሣለቁበት የሓዋሳ ሕዝብ ጎን የቆምን መሆናችንን እንልጻለን።
         ይህ ነገር  በሰሜን አሜሪካ እየተቀጣጠለ ያለውን የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ቢሆንም ከሩጫችን ግን ሊገታን አይችልም። ለጊዜው ካልሆነ በቀር እውነትንና  ፍቅርን የሚያሸንፍ አንዳች ሃይል የለምና። ወገኖች ሆይ  በቅዱስ መጽሃፍ እንደተገለጸው (ማቴ 24፥15) እንዲህ አይነት ነገሮች በተቀደሰ ሥፍራ መቆማቸው የማይቀር ነው ። እስከ መጨረሻው ጸንተን የድርጅት፥ የወዳጅ፥የሥልጣንና የጥቅም ወገኝተኝነት ትተን ለእውነትና ለቤተክርስቲያን ብቻ እንድንቆም ክርስትናችን ግድ ይለናል።
         ጌታ ሆይ ለመንጋው የሚራራ መልካም እረኛ በማጣት እስከመቼ ትተወናለህ? የታወከውን መንጋ ለማረጋጋት መቼ ይሆን ሙሴን የምታስነሳልን?  በስደት በመከራና በጭንቅ ዘመን ሕዝብ የሚያጽናኑ ሃይማኖት የሚያጸኑ ኢሳይያስንና ኤርምያስን መቼ ትሰጠናለህ? ለሕግና ለሥርዓት የሚቀኑትን ኤልያስና ዮሐንስ መቼ ታሳየናለህ። እኛ መንጎችህንስ በሞቀበት ከመዋል ለእውነት እንድንቆም የምታደርገን መቼ ነው? መቼ ይሆን እንደ ናቡቴና  እንደ ሠለስቱ ደቂቅ ብቻችን እንኳን ብንሆን ለእውነት የምንቆም የምታደርገን? አምላካችን ሆይ ይህ ሁሉ የሆነው ከኃጢኣታችን ብዛት የተነሣ ይሆናል? ነገር ግን የአንተ ቸርነት  ከአዳም ጀምሮ የሰው ልጅ ከሰራው ኃጢአት ይልቅ  ይበዛልና ይቅር ትለን ዘንድ እንለምንሃለን። ለዘመናት የተቆጣኸውን  ሀገርና ሕዝብ  የማትምረው እስከ መቼ ነው እያለ የሁላችን ዐይን ወደ አንተ ያንጋጥጣል።  

እግዚአብሔር ሁላችንም ይባርክ
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment