Wednesday, November 9, 2011

ጠ/ቤተ ክህነቱ በሹመትና በሽረት እየታመሰ ነው፤ አባ ሰረቀ ም/ሥራ አስኪያጅነቱን አጥተዋል

by Deje Selam on Wednesday, November 9, 2011 at 4:36pm
  • የጠ/ቤ/ክህነቱ የሹመትና ዝውውር ውዝግብ በሽምግልና ተይዞ ቀጥሏል 
  • ንቡረ ድ ኤልያስ ኣብርሃ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነትን ቀድሞ ከነበሩበት የጠ/ቤ/ክህነቱ የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ጋራ ደርበው እንዲይዙ፤
  • ንቡረ ድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴየገዳማት መምሪያ ዋና ሓላፊ እንዲሆኑ፤
  • አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊእንዲሆኑ ሐሳብ ቀርቧል 
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ የሆኑትን ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን ከትንት በስቲያ አባ ሰረቀን በሕገ ወጥ መንገድ ለሾሙበትየመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ም/ዋ/ሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን መርጠዋቸው የነበረ ቢሆንም የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን ስምምነት አላገኙም 
  • ቤተ ክህነቱ ሙስና የሚያፍርበት ሳይሆን የሚያሾምበት ይነተኛ ተቋም ሆኗል


(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 29/2004 ዓ.ም፤ ኖቬምበር 9/2001)፦ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ጽ/ቤት፣ የጽ/ቤቱን ከሁለት ያላነሱ መምሪያዎች እና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ማዕከል በማድረግ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን የተፈጠረውና  በትናንትናው ዕለት በሃይማኖት ሕጸጽ የሚጠረጠሩትን አባ ሰረቀን የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ም/ዋ/ሥራ አስኪያጅ በማድረግ በፓትርያርኩ በተፈጸመው ሕገ ወጥ ሹመት ከፍተኛ ጡዘት ላይ የደረሰው ውዝግብ ትናንት ሙሉ ቀን በሽምግልና ተይዞ ሲያነጋግር እንደ ዋለ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ገለጹ፡፡

ከትናንት በስቲያ ከቀትር በኋላ አባ ሰረቀ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ተደርገው በፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕገ ወጥ መንገድ መሾማቸውን በመቃወም በዚያኑ ዕለት ማምሻውን ነበር ብፁዕ ዋ/ሥ/አስኪያጅ አቡነ ፊልጶስ ከሓላፊነታቸው እንደሚለቁ ያሳወቁት፡፡ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ትናንት ማምሻውን ለፓትርያርኩ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቡት የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አባ ሰረቀ ለተጠቀሰው ሹመት መታሰባቸውን ከፓትርያርኩ አንደበት በሰሙበት በሳምንቱ መጨረሻ ተጽፎ ሳይሰጥ የተቀመጠው እንደነበር ተመልክቷል፡፡

ደብዳቤው በይዘቱ፣ቅዱስ ሲኖዶስ አባ ሰረቀ በተጠረጠሩበት የሃይማኖት ሕጸጽ ሳቢያ ከሓላፊነታቸው ወርደው ጉዳያቸውን የሚከታተል አካል እንዲቋቋም መወሰኑን እንጂ ከመምሪያ ወደ መምሪያ እንዲዘዋወሩ አለመወሰኑን፤ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የመሾም ሥልጣን በቋሚ ሲኖዶስ በኩል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መሆኑን እንዲሁም የተፈጸመውን ስሕተት ባሉበት ቦታ ሆነው በመቃወም “ፓትርያርኩን ማስቀየም” እንደማይፈልጉ በመግለጽ የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ሳይጠናቀቅ ከጠ/ቤ/ክ/ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ተነሥተው ወደ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት በተዛወሩት ንቡረ ዕድ ኤልያስ ኣብርሃ ምትክ ተገቢው ሰው እንዲመረጥ የሚያሳስብ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዐርብ ማምሻውንና በበነጋው ቅዳሜ ጠዋት ከፓትርያርኩ ጋራ የጀመሩት ጭቅጭቅ ያልተቋጨላቸው ብፁዕነታቸው በመጨረሻ አባ ሰረቀ የሚሾሙ ከሆነ ጉዳዩን ለምልአተ ጉባኤው አስረድተው ከሥልጣናቸው እንደሚለቁ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቃል በማሳወቃቸው ፓትርያርኩ “መሾም እችላለሁ፤ የማዝዘው ባለሥልጣኑ እኔ ነኝ” የሚሉትን ሥልጣናቸውን ለማሳየት በግትርነት የያዙትን አቋም ያለዘቡ መስለው ለመታየት ተገደዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደማዘናጊያ ቢጠቀሙበትም ለጊዜው የተደረሰበት ስምምነት ግን “ቀደም ሲል ለም/ዋ/ሥራ አስኪያጅነት ታስበው የነበሩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ አባ ገ/ማርያምም ሆኑ የአባ ሰረቀ ሹመት በቋሚ ሲኖዶስ ተነጋግረንበት እስክንወስን ድረስ ነገሩ በይደር እንዲቆይ” የሚል ነበር፡፡

ከቅዳሜው ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላ ምልአተ ጉባኤው ሲነሣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የቋሚ ሲኖዶስ ሰብሳቢ ቢሆኑም ጉዳዩን ለቋሚ ሲኖዶሱ በወጉ አቅርበው ለማስወሰን የሰነበተ እልካቸው አላደረሳቸውም፡፡ በምትኩ ያደረጉት ነገር ወደ መዝገብ ቤት እየደወሉ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ፣ የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ልዑል ሰገድ እና የቀድሞው የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የሹመት ደብዳቤዎች በማን ፊርማ እንደወጡ ማረጋገጥ ነበር፡፡

የእልክ መንገዳቸውን በመቀጠልም ቀደም ሲል አባ ሰረቀን ለመሾም ያደረጉትን ሙከራ የተቃወሙትን ብፁዕ ዋና አስኪያጁንና የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁን በየተራ በመጥራት የእነርሱ የሹመት ደብዳቤ የወጣው በእርሳቸው ፊርማ እንደነበር በማስታወስ እርሳቸው መሾም እንደሚችሉ ያሳውቋቸዋል፡፡ እነርሱም በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ዋና ሥራ አስኪያጅን እየመረጠ የመሾም ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ መሆኑን፣ ምክትል ሥራ አስኪያጁም በዋና ሥራ አስኪያጁ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ በእጩነት ቀርቦ ከተመረጠ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ ሲስማማበት በፓትርያርኩ እንደሚሾም በማስረገጥ፣ የእነርሱም ሹመት ይኸው ሥርዓት ሳይከናወን ተፈጽሞ ከነበረ ስሕተት መሆኑን፣ አንድ ጊዜ የተሠራ ስሕተትም ለሌላ የስሕተት ተግባር አጽድቆት እንደማይሆን መልሰውላቸዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ ንግግር በኋላ ነበር በጀመሩት የእልክ ቁልቁለት የቀጠሉት ፓትርያርኩ አባ ሰረቀን የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገው መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በግል ቲተራቸው ያወጡት፡፡ ሕገ ወጡ ደብዳቤ ለአቡነ ፊልጶስ በግልባጭ ቢደርሳቸውም የሲኖዶሱ ጽ/ቤት ግን ወሬውን ከመስማት በቀር የሚያውቀው ጉዳይ አልነበረም፡፡ በተቃውሟቸው የቀጠሉት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስም ባለፈው ሳምንት ዐርብ ለቅዳሜ አዘጋጅተውት የነበረውን የመልቀቂያ ደብዳቤ ለፓትርያርኩ ለመስጠት መዋል ማደር አላስፈለጋቸውም ነበር፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንደሚናገሩት የብፁዕነታቸው መልቀቂያ ሰኞ ማታ የደረሳቸው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የእንደራሴያቸው ያህል የሚቆጥሯቸው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በነገሩ ሽምግልና ገብተው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ መልቀቂያቸውን እንዲያነሡ እንዲያግባቡላቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ እንደ ትእዛዛቸው ቃልም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ትናንት ማለዳ ከሀ/ስብከታቸው ገሥግሠው በመድረስ ሌሎች ሁለት ሊቃነ ጳጳሳትን በመያዝ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን ማግባባት ይጀምራሉ፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን ቀደም ሲል በአሜሪካ የተነሣባቸውን ተቃውሞ በማርገብ ሹመታቸውን ለማደላደል በሚማስኑት አቡነ ፋኑኤል በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት የማኅበረ ቅዱሳንን የአመራር አባላት ከአቡነ ፋኑኤል ጋራ ለመሸምገል ጥረት የሚያደርጉት አቡነ ጎርጎርዮስ ይህ የአጣብቂኝ ጊዜ አካሄዳቸው ጥቂት በማይባሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ አልተወደደላቸውም፤ ነገር እንደማበላሸትም ተቆጥሮባቸዋል - የአለመግባባቱ መሠረት የሕገ ቤተ ክርስቲያን እና የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን መከበር ወይም አለመከበር እንጂ የሁለት አባቶች ጠብ አይደለምና፡፡

የሆነው ሆኖ በትናንት ዕለት በአቡነ ጎርጎርዮስ እና ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት ሲሸመገል የቆየው ውዝግብ እስከ ማምሻው ድረስ በደረሰበት ሁኔታ፣ ፓትርያርኩ አሁን የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ የሆኑትን ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬን የመንፈሳዊ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገው ያቀረቡበት ነበር፡፡ ይህ ሥልጣን በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 31 ንኡስ አንቀጽ 2 መሠረት፡- በስም ተለይቶ ያልተመለከተ፣ በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ የተሰጠው የሥራ ዝርዝር ምን እንደሆነ በውል ያልታወቀ፣ እስከ አሁን እንደታብነውና አንዳንዶችም እንደሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁን በቅርበት ለመቆጣጠር እንደ ንቡረ ዕድ ኤልያስ ያሉ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀራቢ እና ታማኝ የሆኑ ሰዎች የሚሾሙበት እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ በዚህም የተነሣ ይመስላል በሽምግልናው ሂደት ላይ ንቡረ ዕድ ኤልያስ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነትን  እንደያዙ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ በሽምግልናው ላይ ሐሳብ መቅረቡ የተገለጸው፡፡

ያም ሆነ ይህ ፓትርያርኩ “የመጨረሻ ሐሳቤ ነው” በሚል ባቀረቧቸው ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ላይ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ስምምነታቸውን እንዳልሰጡ ነው ሽምግልናውን የሚከታተሉ ምንጮች የሚናገሩት - መሠረቱ የሕገ ቤተ ክርስቲያን መጣስ ነውና፡፡ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ በ29ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ እንደተመለከተው ከከፋ የሙስና ተግባር እና በኦዲት ከተረጋገጠው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ጉድለት ጋራ በተያያዘ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ከተነሡ በኋላ በመጀመሪያ የዕቅድ እና ልማት መምሪያ፣ በመቀጠል የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ አሁን ደግሞ የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ
ቀደም ሲል የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ እንዲሆኑ ደብዳቤ ደርሷቸዋል የተባሉት ንቡረ ዕድ አባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ በትናንቱ ሽምግልና የገዳማት መምሪያ ሓላፊ እንዲሆኑና በሃይማኖት ሕጸጽ የተጠረጠሩትና ከፍተኛ የማስፈጸም ችግር ያለባቸው አባ ሰረቀ ደግሞ የትምህርት እና ሥልጠና መምሪያ ሓላፊ እንዲሆኑ ሐሳብ መቅረቡ ተገልጧል፡፡

ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት ከአውሮፓው የኢኮኖሚ /የአገሮች ዕዳ/ ቀውስ ጋራ በተያያዘ የሥራ አፈጻጸማቸው ደካማ የሆኑና በተለያዩ ቅሌቶች የተጠረጠሩ መሪዎች በሕዝባቸው ቁጣ ከሥልጣን እንደሚነሡ እየተሰማ ነው፡፡ በእኛው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግን በግል ማኅደራቸው አንድም በጎ ስኬት ያልተመዘገበላቸው ሙሰኛ እና ደካማ የሥራ አፈጻጸም ያላቸው ግለሰቦችን በቁልፍ ቦታዎች በማስቀመጥ፣ በመሾም እና በመሸለም ቤተ ክህነቱ ሙስና የማሳያፍርበት ሆኗል፤ ባናቱም የተቋሙን ቁልፍ መዋቅሮች የማድቀቅ የእብሪት ተግባር ቀጥሏል -  አንድ አባ ሰረቀን በመሾም የሥልጣን ልዕልናቸውን ምናልባትም የዓላማ አንድነታቸውን ለማሳየት እየጣሩ በሚገኙት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ምክንያት ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በየሰዓቱ የሚወጡት መረጃዎችም እያደናገሩም እያሸበሩም ቀጥለዋል፤ የዛሬውስ ቀን ምን ያሰማን ይሆን? ቆይተን እናየዋለን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

1 comment:

  1. what is wrong with this person, what is his plan really? am sure he is trying to distruct the whole church. People we have to do something before it's too late. This man plus this followers are doing so bad latly and we must do something now than later.
    God bless you all

    ReplyDelete