Sunday, December 28, 2025

የሠለስቱ ደቂቅ የነገረ መለኮት ትርጓሜ

እንኳን ለሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አድረሰን አደረሳችሁ በማለት፤ የነገረ መለኮትን ትርጓሜ በተለይ የሠለስቱ ድቂቅን ታሪክ በፍኖተ አበው የቴሌግራም ገጽ ያገኘነውን ለማጋራት ይሄንን የሚከተለውን ጽሁፍ እንድታነቡ በአክብሮት እንጋብዝዎታለን።

    በሠለስቱ ደቂቅ ምስጋና ሰይጣን የሰው ልጆችን ድል መንሳቱን የእግዚአብሔር ልጅም ወደ ሲኦል መውረዱን በኃይሉም ከችግራቸው 
ሊቀ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል
ስለማዳኑ የገለጠበት ምስጢር ነው። 

    ከአዳም ከተፈጠረ እስከ ክርስቶስ ልደት ድረስ ያለውን ከዚያም እስኪሰቀልና ወደ ሲኦል ወርዶ እስኪያድናቸው በምድር የሚኖርባቸውን ዘመናት ይነግረናል። ይኽም የዳንኤል አራተኛው ራእይ ነው። 
"የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት" ት. ዳን 1:1

    የእስራኤል ልጅች በፈርኦን በባርነት መኖራቸው የአዳም ልጆች ለሰይጣናት በባርነት ለመኖራቸው ምሳሌ እንደሆነ እግዚአብሔርን ስለመድፈራቸው ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆች እንደ ማረካቸው ከቅድስት ሀገራቸው እስከ ሀገሩ ባቢሎን እንዳፈለሳቸው እርሱም ከሠራዊቱ ከከለዳውያን አስገድዶ እንዳስገዛላቸው ነቢዩ ዳንኤል አመለከተ። 

    "ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል" ት.ዳን. 3:1-5 

    እግዚአብሔርን ስለ መደፋፈራቸው አዳምና ዘሩን ሰይጣን እንዳማረካቸው ከቅድስት ገነት አውጥቶ የጨለማ ምድር እስከ ሆነው እስከዚህ ዓለም አውርዷቸው እንደ ነበር ይኽችውም የሹመት ሀገሩ ናት። 

    ናቡከደነጾር የእስራኤልን ልጆችና ከአህዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩትን ከበሮ መለከት መሰንቆንና በገናን ጸናጽልንም በመስማት በዘፈን ላቆመው ምስል እንዲሰግዱ አደረገ። ላቆመው ምስልም እንዲሰግዱ እንደ አሳታቸው እንዲሁ ሰይጣን ለእርሱ ባርያ ሆነው ለትእዛዙ እንዲገዙ እስኪጠፉ ድረስ የአዳም ልጆችን በዚህ ኅላፊው የዓለም ፍትወት አሳታቸው። ኅላፊ ፍትወት ማለት ተድላ ዘፈን ደስታ ማለት ነው።

    ናቡከደነጾር ያልታዘዙት ላቆመው ምስልም ያልሰገዱትን ሠለስቱ ደቂቅን በእቶን እሳት ውስጥ እንደ ጣላቸው እንደዚሁ ሰይጣን ትእዛዙን ያልሰሙትን ጻድቃን ሁሉ አብርሃም ይስሐቅን ያእቆብን ከጻድቃን ከሌሎችንም ነቢያት ስለ አባታቸው አዳም ሕግ ማፍረስ ወደ ሲኦል ጣላቸው። 
"ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም፦ ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም።……..ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ" ት.ዳን. 3:16-20

    እሳቱ ግን የናቡከደነጾርን ሠራዊት እንዳቃጠላቸው ሠለስቱን ደቂቅ አላቃጠላቸውም። ለሰይጣን የታዘዙትን እንዳቃጠለቻቸው ጻድቃንን በሲኦል ውስጥ አላቃጠላቸውም። 
"መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ"  ት.ዳን.3:27

    እሳቱ ከሠለስቱ ደቂቅ እንደ ራቀ እንዳላቃጠላቸው እንደ ቀዝቃዛ ጠል ሆነላቸው። ይኽም ስለ ባለ ጻጋውና ስለ ደሃው ሲናገር አልአዛርም በአብርሃም አጠገብ እንደ ነበር ተናገረ። ሉቃ 16:19

    ቅዱሳን ጻድቃን በእረፍትና በቅዝቃቄ ሁኔታ ከሐድያን በእሳት ኩነኔ መኖራቸውን ዳንኤል በሦስቱ ወጣቶች ተናገረ። 

    አዛርያም "ለሕዝቡ ሁሉ ኃጢአት በእግዚአብሔር ታምኖ በእሳት እቶን ውስጥ በመቆም እንዲህ አለ "አቤቱ ባመጣህብን ነገር ሁሉ እንደ ጻድቅ ነህ ፍርድህም የእውነት ፍርድ ነው። እኛ ግን በደልን ሐጢአት ሠራን ዐመጽንም" 

    እንዲሁም ጻድቃን አበው በሲኦል ውስጥ ስለ ሁሉ የአዳም ዘር ኃጢአትና ሕግ ስለማፍረሳቸው የሚታመኑ ሆኑ።  
እስከ እለት ሞታቸው ድረስ አመኑት። ስለዚህም "ከዚህ እንጨት ከበላህ ሞትን ትሞታለህ" ባለው ጊዜን እግዚአብሔርን ሐሰተኛ ያደረገው የአዳም ኃጢአት ተተወች። "ይህችን በበላህ ግዜ አምላክ ትሆናለህ" ያለውን የሰይጣንን ቃል ባመነ ጊዜ አዳምና ልጆቹ ባሪያ ሆኑ። ዘር ሁሉ ወደ ሲኦል ወደቁ። 

       አብርሃም ይስሐቅ ያእቆብ በእግዚአብሔር በማመናቸው ቃል የገባላቸውን የከነዓንን ምድር አላወረሳቸውም። ከከነዓን የምትበልጠውን መንግሥተ ሰማያትን ሰይጣን ከእርሷ የወደቀባትን ከፍተኛውን  ስፍራ አወረሳቸው እንጂ። 

    በአዳም ላይ የሚገባውን ፍርድ ተሸክሞ በራሱ ይቤዥው ዘንድ ሊገድለው እስኪደፋፈር ድረስ መለኮቱን ከዲያብሎስ ይሰውር ዘንድ ከእርሱም ስለ ቤዛነቱ በፍትሕ ይወስዳቸው ዘንድ ነው። 

    ስለ አብርሃም ይስሐቅ ያእቆብ እምነት ሕግ ስለማፍረሱ የመጣበት የአዳም ኃጢአቱ ተተወ። ስለዚህ አዛርያ በእቶን እሳት ውስጥ ስለ አዳምና ዘሩ ማለደ። ስለ ወዳጁ ስለ አብርሃም ስለ ባለሟሉ ስለ ይስሐቅ ስለ ቅዱሱ ያእቆብ ብሎ ይቅር ይላቸው ዘንድ በጽድቃቸው የገባላቸውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ ለመነ። 

    እግዚአብሔር የአዛርያን ጸሎት ሰማ የእግዚአብሔር ልጅም ዝቅ ብሎ ወደ እነርሱ ወደ ሲኦል እንደ ሚወርድና እንደ ሚያድናቸው ገለጠ። ወደ እሳቱ ከነአዛርያ ጋር መልአክ እንደ ወረደ በተናገረ ጊዜ "መልአክ" ብሎ ጠራው። በኋላም የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ ገለጠው። 

    ናቡከደነርም "በእስር ውስጥ ተፈተው የሚመላለሱ አራት ሰዎችን አያለሁ አራተኛውም እንደ እግዚአብሔር ልጅ ይመስላል።" ዝቅ ብሎ ሰው እስከ ኾነ ድረስ ወደ እነርሱ ወደ ሲኦል እንደማይወርድ ገለጠ። 

    አዛርያ ጸሎቱን በጨረስ ጊዜ ከአዳም ጀምሮ እስከ መምጫው ያሉትን ዓመታት መጠን ገለጠ። የንጉሡ ሠራዊትም ነበልባሉ አርባ ዘጠኝ ክንድ ከፍ ከፍ እስኪል ድረስ እሳቱን አነደዱ። አርባ ዘጠኝ ክንድ የሚለው ሰይጣንን ሠራዊቱ አራት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመት በሲኦል እሳት ውስጥ ያቃጥሏቸው ዘንድ በዓለም ላይ እንደ ሰለጠኑ ማስረዳቱ ነው። እርባ ዘጠኝ ክንድ አንዱ ክንድ ስለ መቶ ዘመን ነው። 

    ይህም ማለት የሰይጣናት እሳት በዚያ ዘመን ልክ እንደ ሆነች ጻድቃን በሲኦል እንዳልተቃጠሉ ሠለስቱ ደቂቅን እንዳላቃጠላቸው የሰይጣናትን ሕዝብ ከሐድያን አይሁድን ታቃጥላቸው ነበር። በእሳት ውስጥ ያመሰግኑት ነበር። 
"ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ እስመ ለአለም ምሕረቱ" እግዚአብሔርን አመስግኑት ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና" እየደጋገሙ ሠላሣ ሦስት (33) ጊዜ አመስገኑት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከልደት ጊዜ እስከ ስቅለቱ ጊዜ ወደ ሲኦል እስከ መውረዱ ጊዜ ምድር ላይ የኖረበት የሠላሳ ሦስት ዓመት ምልክት ነው። 

    ስለዚህም ሠላሳ ሦስት ጊዜ ብለው ከፈጸሙ በኃላ እንዲህ አሉ። አመስግኑ ልዕልናውን ጨምሩ ከሲኦል አድኖናል ከሞት እጅም አስጥሎናልና ከሚነድ ነበልባል መካከልና ከእሳት እቶንም ታድጎናልና። አዳምንና ዘሩን ከሲኦል ያዳናቸው በሠላሳ ሦስት ዓመት እንደ ሆነ አሳየ። 

    ከስቅለቱ በኋላ ያመኑበትን እርሱን ያመሰግኑ ዘንድ አዘዛቸው ምሕረቱ እስከ ዘለዓለም እንደ ምትኖርላቸውም ተረዱ። ከሰዎች የኦሪትን ሕግ በወንጌል እንደ ለወጠ አይለውጣትም። የሚያመሰግን ሰው "እግዚአብሔርን ባርኩት" ሲል ቡሩካን መኾናቸው ተናገረ። አምልኳቸውም የተባረከች ነች። እነርሱም ቡሩካን ናቸው። ቅዱስ ሳዊሮስ ዘእስሙናይ 

ንዋይ ካሳሁን

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment