Thursday, December 4, 2025

"ዓራት ዓይናው ታላቁ አባት መላከ ገነት አምደብርሃን የኔታ ይባቤ በላይ ትላንት ምሽት ለዛሬ ሌሊት አጥቢያ አርፈዋል " - ቤተክርስቲያኗ

➡️ " የስኳር ህመም በፊትም አለባቸው፤ ግን አሞኝም ብለው ከጉባዔ አልወረዱም፤ ከተኙ በኋላ ነው ገደማያውያኑ 'ምን ነው'? 
መልአከ ገነት አምደብርሃን የኔታ ይባቤ በላይ

ሲሏቸው ማውራት አልቻሉም' ነው ያሉን" - የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት

በሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት፣ "ክብረ ደናግል ናዳ ቅድስት ማርያም ገዳም" አበምኔት፣ የአራቱ ጉባዔያት መምህር መላከ ገነት አምደብርሃን የኔታ ይባቤ በላይ ማረፋቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ዛሬ ረፋድ ገልጻለች።

የቤተክርስቲያኗ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ መላከሰላም ሰለሞን ቶልቻ በሰጡን ቃል፣ " ዓራት ዓይናው ታላቁ አባት መላከ ገነት አምደብርሃን የኔታ ይባቤ በላይ ትላንት ምሽት ለዛሬ ሌሊት አጥቢያ አርፈዋል " ብለዋል።

ቀብራቸው ብፁዓን አባቶች፣ ታላላቅ መምህራንና የየኔታ ተማሪዎች በተገኙበት ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ሲያገለግሉበት በነበረው ገዳም እንደሚፈጸም የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ለቤተ ክርስቲያኗ ማሳወቁን ነግረውናል።

"የኔታ በርካታ ሥራዎች አሏቸው። ታዋቂ የዓራቱ ጉባዔያት መምህር ናቸው። በተለይም በመንፈሳዊ አባትነታቸው በርካታ ደቀመዛሙርት እና ተማሪዎችን ያፈሩ ታላቅ አባት ናቸው" ያሉት ኃላፊው፣ ዝርዝር ሥራቸውን ሀገረ ስብከቱ በቀጣይ እንደሚያሳውቅ አስረድተዋል።

" እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብዙ ሊቃውንት፣ ብዙ ጳጳሳት፣ በርካታ አባቶችን ያፈሩ አባት ናቸው። በርካታ በጎ ትሩፋቶቻቸውን መረጃዎችን አስደግፈን በቀጣይ ይተነተናል " ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የኔታ የሞቱት በህመም ምክንያት ነው ወይስ የተለዬ ምክንያት አለ ? ስንል የጠየቅናቸው ኃላፊው፣ " የኔታ እድሜያቸው ብዙ የገፋ አይደለም። ግን ፈጣሪ ነው የወሰዳቸው፤ የጠነከረ በሽታም አልነበራቸውም " ሲሉ መልሰዋል።

" ተማሪዎቻቸውም፣ ቤተሰቦቻቸውም እንደነገሩን አልታመሙም፣ ከዚህ በፊትም 'ጉባዔውን ሰው ተኩ፣ እኔ አልቆይም የሚል ሀሳብ ያቀርቡ ነበር' ህመም የለባቸውም ተናግረው ነው ያረፉት፤ 'ትናንትም ይባርኩ ነበር ጉባዔ ላይ' ፤ እንደ ጉንፋን ድካም ካልሆነ በስተቀር የጠና ህመም የላቸውም " ሲሉም ነግረውናል።

" የኔታ ወላዲ አዕላፍ ናቸው፤ ሥራዎቻቸው የሚቀጥሉ ናቸው። ሰው ሞተ የሚባለው ስሙ በሥራው ሊነሳ የማይችል ሲሆን ነው፣ የኔታ በርካታ ደቀመዛሙርት እና ሊቃውንትን ያፈሩ አባት ስለሆኑና በቤተክርስቲያኗ ለዘመናት ስለሚጠሩ አልሞቱም፣ ህያው ናቸው ስማቸው ከመቃብር በላይ ህያው ነው " ብለዋል።

" እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ አባት ነው ያጣነው። ከትምህርታቸው፣ ከእውቀታቸው፣ ከአገልግሎታቸውም ባሻገር በመንፈሳዊ ህይወታቸው የተለዩ አባት ነበሩ። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሀዘን ነው የገጠመን፤ ግን እግዚአብሔር አላማ አለው። ከዚህ ዓለም ድካም ነው ያረፉት " ነው ያሉት።

የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አለ ?

የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጂ መላከገነት አምደሃይማኖት ፈጠነ፣ " የኔታ ይዛቤ የተለየ ህመም አላመማቸውም፤ ስኳር በሽታ ነበረባቸው። ትናንት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲባርኩ፣ ልጆቻቸውን ሲመክሩ ቆይተዋል። ማታ ተኙ በዚያው አረፉ ፤ ሰው ክፉ ነገር አድርሶባቸው አይደለም፤ ሚዲያዎች በወቅታዊ ጉዳይ ነው ? ብለው ይጠይቁኛል፤ ነገር ግን በመንግስትም ሆነ በጫካ ባሉ ታጣቂዎች የደረሰባቸው ነገር የለም " ሲሉ ለቲክቫህ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ታስረው እንደነበር ያስታወሱት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ " ታሰሩ መንግስት ጋር ተነጋገርን ከእስር ተለቀቁ፤ ከዚያ ውጭ መንግስትም ሌላውም ያደረሰባቸው ተፅዕኖ የለም። ጉባዔያቸውን እያስተማሩ ነው የነበረው። እስከ ትናንትናዋ እለት ድረስ ደህና ነበሩ " ነው ያሉት።

ምናልባት ከስኳር በሽታው ጋር በተገናኘ የጠና ህመም ኖሮባቸው አመመኝ ብለው ነበር ? የሚለውን የቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ፣ "የስኳር ህመም በፊትም አለባቸው፤ ነገር ግን አሞኝም ብለው ከጉባዔ አልወረዱም፤ ከተኙ በኋላ ነው ገደማያውያኑ 'ምን ነው? ' ሲሏቸው ማውራት አልቻሉም' ነው ያሉን " ሲሉ መልሰዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ 
አዲስ አበባ 



የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment