“ስንዴውን እየሸከፈ ነው”
ጌታ ራሱን ከመሰለበት ምሳሌዎች ንጹሕ ዘር በሚዘራ ገበሬ ነው።እርሻውም ይህ ዓለም፣ ዘሩንም ወንጌል ነው።እንክርዳድም ክፉት
ዘሪውም ዲያብሎስ ነው።እንክርዳዱም የሚዘራው ሰዎቹ ሲተኙ ነው። ሰዎቹ ያላቸው ታላላቁ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። ማንቀላፋታቸው ዕረፍታቸው ሲሆን ሰዎቹ ሲተኙ እንክርዳድ መዘራቱ ታላላቆቹ ሲያርፉ በዲያብሎስና ግብር አበሮቹ አዲስ እንክርዳድ ሥርዓት ይዘራልና።አብረውም እስከ መከር ይቆያሉ።መከሩ የዚህ ዓለም ማለቅ ሆኖ አጫጆቹም መልእክት ናቸው።ያን ጊዜ ንጉሥ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚያበጥርበት የማያሳስት ሥልጣን የተባለ ነፋስ አለው።እንክርዳዱን በእሳት አቃጥሎ ስንዴውን በመንግሥተ ሰማያት ጎተራ ይሰበስባል ነበር የተማርነው።ማቴ፲፫፥፴፱-፵፪
| ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረኪዳን ግርማ |
ዘሪውም ዲያብሎስ ነው።እንክርዳዱም የሚዘራው ሰዎቹ ሲተኙ ነው። ሰዎቹ ያላቸው ታላላቁ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው። ማንቀላፋታቸው ዕረፍታቸው ሲሆን ሰዎቹ ሲተኙ እንክርዳድ መዘራቱ ታላላቆቹ ሲያርፉ በዲያብሎስና ግብር አበሮቹ አዲስ እንክርዳድ ሥርዓት ይዘራልና።አብረውም እስከ መከር ይቆያሉ።መከሩ የዚህ ዓለም ማለቅ ሆኖ አጫጆቹም መልእክት ናቸው።ያን ጊዜ ንጉሥ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚያበጥርበት የማያሳስት ሥልጣን የተባለ ነፋስ አለው።እንክርዳዱን በእሳት አቃጥሎ ስንዴውን በመንግሥተ ሰማያት ጎተራ ይሰበስባል ነበር የተማርነው።ማቴ፲፫፥፴፱-፵፪
የሥጋ ዓይን ሳይኖራቸው በነፍሳቸው የሚያዩት የኔታ መጋቤ ምሥጢር ተሾመ ደግሞ አሁንም “ስንዴውን እየሸከፈ ነው አሉ”።በ፳፲፫ ዓም መጽሐፈ መነኮሳትን ከእርሳቸው እያሄድኩ ሳለ ወንበር እንዳበቃ አንድ ትልቅ ሰው እንዳረፉ ሰማን።የኔታም ካዘኑ በኋላ “ አይ እግዚአብሔር እኮ እንክርዳዱን ለማቃጠል ስንዴውን አስቀድሞ እየሸከፈ ነው” አሉ። ምን ማለት ነው የኔታ ስላቸው፦ “ ሰዉ ከፍቷል፤አልመለስ ብሏል፤ ስለዚህ ወዳጆቹን አስቀድሞ ሸካክፎ በመከራ እሳት ሊገርፈን ይመስለኛል አሉ” ያን ጊዜም ጦርነት ውስጥ ነበርን። አሁንም እንደዚያው የመከራው እሳት እየገረፈን አለን።በጊዜው ተጨንቄ አሁንም የሚሆነውን ሁሉ እያየሁ እያሰብኳቸው ሳለ እንዳረፉ ሰማሁ።
የኔታ አሁን ደግሞ አንዱን ምርጥ ስንዴውን እርስዎን ወሰደ።እርስዎ ከሌሉ የታሪክ እንክርዳድ ሲዘራ ማን ያቀናል?በመጣን ቁጥር የማይዘጋ ቤት የማን አለ!ለትንሽ ለትልቁ የማይሰለች አንደበት ወዴት አለ? ታሞ የሚስቅልን አባት ወዴት እናገኛለን?ሰውነቱ ከአልጋ ተጣብቆ በደዌ ተይዞ የሚያስተምር ትዕግሥተኛ መምህርስ ?
የኔታ ሩቅ ሆኜ የት ጠፋህ የሚሉኝ ፣የኔታ በቀለም የወለዱኝ አባቴ፣የኔታ ጎንደር አራት ዓመት ስቀመጥ በደነዘዘኝ ቁጥር መጥቼ ልጅነቴን የማጫውትዎት ወዳጄ!.
የኔታ ስንዴዎቹን እናንተን ሲሸክፍ እኛን በእሳት እንዳያቃጥለን በጸሎትዎ ያስቡን። የመጽሐፈ መነኮሳት መምህር ነዎትና እኒያ በስስት ሲተረጉሙላቸው የነበሩ ከዋክብት እንጦንስና መቃርስን...ሲያገኟቸው እንደ ደከምን ይንገሩልን። ብየ አልቅሼ ነበር።
ዛሬ ደግሞ የክብረ ደናግል ናዳ ቅድስት ማርያም አበ ምኔት፤ የቅኔው፣ የመጻሕፍተ ብሉያትና ሐዲሳት፣የአቡሻኽር፣የፍትሐ ነገሥቱ ሊቅ የኔታ ይባቤ በላይ እንዳረፉ ከወንበር በኋላ ሰማሁ።የኔታ ይባቤ ቀርቤ ባላውቃቸውም በአንዲት እናታችን በቤተ ክርስቲያን ግን አውቃቸዋለሁ።እውነትን ትክ ብሎ የሚያይ የነፍስ ዓይን ያላቸው፣የአድር ባይነትን ካባ የናቁ፣ሳይማር መድረክ የያዘውን ፈር የሚስይዙ፣በአታቸውን አጽንተው በገዳማቸው የሚኖሩ መምህር እንደሆኑ ሰምቻለሁ።በሳይንስ ከተራቀቁ ምሁራን እስከ እስካልተማረው በጸሎታቸው የሚያስጠጉ ፣ በሊቅነታቸው ወደ ላይ የራቁ ቢሆንም ለሕዝቡ ደግሞ እንባ አባሽ ቅርብ አባት ነበሩ የኔታ።የኔታ ይባቤን የመጻሕፍትን ግብር የሚያውቁ መምህራንን በተጋድሎ ምጥ፣ በሊቅነት አብራክ እንዳስገኙ አብረውኝ በሰበኩ ልጆቻቸው አውቃቸዋለሁ።ለእኛ ቢኖሩልን እንጂ ለእርሳቸውስ ቅዱስ ጳውሎስ
“እፈቱሰ እፍልስ ወእትፈለጥ እምዓለም ከመ አሃሉ ኀበ ክርስቶስ -ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ” እንዳለ ፊልጵ ፩፥፳፫ የሚሻላቸው ወደ አገለገሉት አምላክ ሂደው ፊቱን አይተው ማረፋቸው ነው። ለእኛ ግን “ቤተሰቡ ሲተኙ ጠላት እንክርዳድ ዘራ” እንዳለ ጌታ የመጻሕፍትና የጸሎት ቤተሰቡ እናንተ ስትሔዱ እንክርዳድ እንዳይበቅልብን ለቀረባችሁት ጌታ ለመድኃኔዓለም አሳስቡልን፣ በጸሎት አይርሱን የኔታ።
ለሁለቱም መምህራን ደቀ መዛሙርት፣ካህናት፣ዲያቆናት፣ መነኮሳትና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ማርታና ማርያምን አብሮ አልቅሶ ያጽናና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የልብ ሰላም ይስጥልን።
ዓይኔም፣ልቤም፣እጄም ይህንን ጻፉ!
©️አባ ገብረኪዳን ግርማ
የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምስክር መምህር
ኅዳር ፳፪-፳፻፲፰ ዓም
No comments:
Post a Comment