DEC 01, 2025
| የጠለፋ ወንጀል በኢትዮጵያ ተባብሷል |
እንደሆነ በተደጋጋሚ ያወጣናቸው መረጃዎች ጠቁመዋል።
አሁን ከወደ ወልዲያ የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው በርካታ የዓብነት ተማሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ታፍሰው ተወስደዋል።
ስልካቸውን ከተቀሙ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በሚሊሻዎች የተወሰዱት የዓብነት (የቤተክርስቲያን) ተማሪዎቹ በወልዲያ ከተማ የሚገኘው የቲንፋዝ ደብረ በረከት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርሰቲያን እና የሌሎች ቤተክርስቲያኖች ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
"ቤተ ክርስቲያኒቱ ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ በደብዳቤ ብትጠይቅም እስካሁን ምላሽ አልተገኝም። አፍነው የወሰዱት የሚሊሻ አባላቱ በወሰዱት በእያንዳንዱ ተማሪ 7 ሺህ ብር እየጠየቁ ይገኛሉ" በማለት አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ እና ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን ጠቁመዋል።
ሚድያችን የደረሰው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያሳየው ታግተው የተወሰዱት ተማሪዎች ከቲንፋዝ ደብረ በረከት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ሶስት፣ ከፒያሳ መንበረ ንግስት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ደብር አምስት፣ ከተማው ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ደብር የሚማሩ አስራ አምስት ናቸው።
"በአጠቃላይ ከሃያ ሶስት በላይ ተማሪዎች ተወስደዋል። አሁን ላይ በከተማው ውስጥ በሚገኝ አንድ ቀበሌ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ከቤተክርስቲያን አካባቢ ሰምተናል" በማለት ሌላኛ የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው ሀሙስ ከተያዙት ተማሪዎች መካከል አንደኛው አርብ ለማምለጥ ሲሞክር ከሚሊሻ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ከፒያሳ ወደ ቲንፋዝ በሚወስደው መንገድ ላይ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል።
"ተማሪዎቹ ወደየት ይሂዱ? ገጠር ቤተሰብ ጋር ሲሄዱ ፋኖ ይወስዳቸዋል፣ ከተማ ሲሆኑ ሚሊሻ ይወስዳቸዋል። ፖሊሶች ሲጠየቁ እኛ የለንበትም፣ የምናውቀው ነገር የለም ይላሉ" በማለት ምንጫችን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ታፍሰው ከተወሰዱ በኋላ ነፃ ለመሆን እስከ 1 ሺህ ዶላር እየተጠየቁ መሆኑ ሚድያችን ከተያዥ ቤተሰቦች ሰምቷል።
"ከአሁን ቀደም ወጣቶቹን የደህነነት ስጋት ነው፣ አጣርተው እንለቃለን ብለው ይለቋቸው ነበር። አሁን ግን እስከ አንድ ሺሕ ዶላር እየተጠየቅን ነው። ገቢው ለማነው? ምክንያቱስ ምንድነው? ፖሊስ ጣቢያዎች በገንዘብ ሊቀጡ ይችላሉ ወይ? የሚቀጡትስ በዜግነታቸው ነው ወይ?" በማለት ጥያቄ ያቁርባሉ።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ በአዲሱ ሸገር ሲቲ ፉሪና ኬንቴሪ አካባቢ ወጣቶች እየተያዙ የቀድሞ ፍፁም በላይ ሆቴል እና ወጣቶች ማዕከል ውስጥ እየታሰሩ መሆኑም ታውቋል። ብዙዎች ከክፍለ ሀገር ስራ ፍለጋ የመጡ መሆናቸው የታወቁ ሲሆን ቤተሰብ ለማስለቅ ከ30 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር እየተጠየቁ መሆኑን ሰምተናል።
-መሠረት ሚድያ-
ምንጭ፡ ቱምቢ ሚዲያ ቴሌግራም
No comments:
Post a Comment