Tuesday, January 3, 2012

አክራሪ ሙስሊሞች የወራቤ ደብረ ኃይል ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያንን ሊያቃጥሉ ሲሉ ተያዙ


‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጸልዩ››

(አንድ አድርገን ታህሳስ 17 2004 ዓ.ም) ፡-የቤተክርስትያናችን ፈተና መልኩን እየቀየረ መጥቷል ፤ ፈተናችንም ከብዷል ፤ የዛሬ አንድ ወር ገደማ አክራሪ ሙስሊሞች የቅድስት አርሴማን ቤተክርስትያን ሲያቃጥሉብን ፤ ሀዘናችን ከልባችን ሳይወጣ ፤ መንግስትም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ሄዶ ፍትህ ሳናገኝ ፤ ሌላ ትንኮሳ ተካሂዶብናል ፤ ፤ የሙስሊም ማህበረሰቦች ያሉበት አንዳንድ ቦታ ላይ ቤተክርስትያን መስራትም ሆነ በተሰሩት ላይ አምልኮተ እግዚአብሔር መፈፀም እየከበደ ነው፡፡

በስልጢ  ዞን  የምትገኘውን  አርሴማ  ቤተ ክርስቲያን  ያቃጠሉ  ሙስሊሞች  ዛሬ ሌሊት 16/04/2004  በስልጢ  ዞን  በዋና  ከተማ  ወራቤ  የሚገኘውን  የወራቤ  ደብረ  ኃይል ቅዱስ  ሩፋኤል ቤተክርስቲያን  ሊያቃጥሉ ሲሉ በቤተክርስቲያኑ  ጥበቃ  በተከፈተ  ተኩስ ለጊዜው ሊያመልጡ ችለዋል፡፡  በጊዜውም በበረንዳው  ላይ እሳት  ሲለኩስ  የነበረ  አንድ  ሰው  በጥበቃ ፤ በካህናቱና በአስተዳዳሪው የተያዘ  ሲሆን ፤ጥያቄ ሲጠየቅ ‹‹ ሁለት ሰዎች ወደ መስጊድ ስሄድ ክብሪትና  ማቃጣጠያ  ሰጡኝ ›› ብሏል፡፡ ተኩሱን  ሰምተው  የመጡ  የፖሊስ  አባላት   ይዘውት ወደ ጣቢያ ሄደዋል፡፡  ይህ ሰው ከዚህ በፊት  በከተማው  እራሱን እንደ እብድ አድርጎ የሚኖር እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡ 

አዎን የባለፈውን የቤተክርስትያን ቃጠሎ ቪዲዮ ፤ ኦዲዮ ፤  የሰው ፤ የፎቶ ማስረጃ ፤ ከፌደራል ጉዳዮች መንግስት መድቧቸው ለመጡ ሰዎች ተሰጥቷል ፤ ጉዳዩን ግን ፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔ ሊያስወስኑልን ፤ ፍትህን ሊሰጡን አልቻሉም ፤ መንግስት ፍትህ አለመሰጠቱ  ሰዎቹን የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደርጋል ፤  ላደረሱት አደጋ ተመጣጣኝ የሆነ ፍትህ ቢሰጣቸው ኖሮ ዛሬ ደግመው ይህን ባላሰቡት ነበር ፤ አስበውም ባልተገበሩት ነበር ፤ እነርሱ ምን ያድርጉ ? እንደ ፓርላማ አባል ያለመከሰስ መብትን ከመንግስት አግኝተዋል መሰል ፤ በህግ ፊት ሁሉም እኩል ከሆነ አሁን ፍትህ ለማሰጠት ጊዜው የረፈደ አይመስለንም፡፡ ያለበለዚያ የት ሄደን አቤት እንበል ? አንድ የማይገባኝ ነገር የቤተክህነቱ ዝምታ ነው ፤ መንግስት ዝም ቢል እንዴት ቤተክህነቱ ጉዳዩን ዝም ይላል ፤ ባለቤት የሌለው ቤት አስመሰሉት እኮ ፤ ይሄኔ ሹም ሽር ቢሆን ኖሮ እስከ ደም ጠብታ ድረስ ሲሟገቱ ይውሉ ነበር፡፡ ምእመኑም እየተደረገ ያለውን ነገር ማወቅ አለበት የሚል እምነት አለን ፤ ለምን ቢባል ነገ የሚመጣውን በማሰብ ራሱንና ቤተክርስትያንን የመጠበቅ ሀላፊነት ስላለበት ጭምር ነው፡፡

እኛም ይህን አይነት በቤተክርስትያናችን ላይ የሚደረግ እኩይ ምግባርን በጊዜው ህዝብ ዘንድ በማድረስ ፤ ምዕመኑ ቤተክርስትያንን እንዲጠብቅ የተሻለ መነቃቃት እንፈጥራለን ፤ በተጨማሪ መንግስትም ጉዳዩን ከቁብ በመቁጠር ሌሎች ይህ አይነት አደጋ ይከሰታል ብሎ የሚሰጋበት አብያተክርስትያናት ላይ ጥበቃውን ያጠናክራል ብለን እናስባለን፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ሁላችን ስለ ቤተክርስትያናችን አጥብቀን ብንፀልይ ፤ እግዚአብሔር እንዲጠብቃት ብናሳስብ የተሻለ ነው ብለን እናምናለን፡፡
 
ተጨማሪ መረጃ ለማግኝት ያደረግነው ጥረት ሊሳካ አልቻለም ፤ ፖሊስ ይችንም መረጃ ለማንም እንዳይተላለፍ ጥብቅ ማጠንቀቂያ መስጠቱን ለማወቅ  ችለናል ፤ ፖሊስ እንዲህ ቢልም መረጃው ከእኛ ሊያመልጥ አልቻለም ፤ ከቀናት በኋላ  አጣርተን የምንመለስበት ጉዳይ ይሆናል፡፡


ከእኛ የሚያመልጥ እርሶ ጋር የማይደርስ የቤተክርስትያናችን ጉዳይ አይኖርም፡፡ 

‹‹እግዚአብሔር ቤተክርስትያንን ይጠብቅልን››
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment