Thursday, January 19, 2012

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም በጤና አደረሳችህ አደረሰን

"በፍሰሐ ወበሰላም ወረደ ወልድ ውስተ ምጥማቃት"

እንኳን ለጌታችን ለመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን አሜን
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሰዎት
የዛሬ ፲፻፱፸፬ ዓ.ም. ዓመት አካባቢ የእግዚአብሔር አብ የባሕሪይ ልጅ የሆነው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ወልደ እግዚአብሔር) በእደ ምጥምቁ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ ምስጢር በዮርዳኖስ ወንዝ  ተፈፀመ። ጥንት ነቢያት በትንቢት የተናገሩለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት እነኛ ደገግ ነብያት ሊያዩት ቢወዱም ነገር ግን እድሜ እረፍታቸው ገድቧቸው ሊያዩት አልታደሉም፥ ጥንት ነቢያት የተነበዩለት ጊዜው ደረሰና በይሁዳ፣ በራማ፣ አካባቢ ድምጽ ተሰማ ይህ ድምጽ  በገሊላ አውራጃና አካባቢው ኮረብታማ ሥፍራ ተራርቀው በሚኖሩ ከተሞች ሁሉ ደረሰ።
ይህን ድምጽ ሰምተው ምላሽ ለመስጠት ከቤታቸው የወጡ በግብርና የሚኖሩ፣ በባሕር የነበሩ አሳ አጥማጆች እንዲሁም በገዥው መደብ ስር በተለያየ ማዕረግ እና ስም የሚጠሩና የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ ነበሩ፤ በጥሪው ምክንያት ሁሉም በአንድ ሥፍራ ተሰብስበዋል ጥሪውም እንዲህ የሚል ነበር "የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ። " ሉቃስ ፫ ፥ ፫ - ፮ ለዚህ ድምጽ ምንነትና ማንነት ለማየት እና ለመስማት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የወረደው ሕዝብ ስፍር ቁጥር አልነበረውም፥ ተናጋሪው ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ነገር ግን በበረሃ ሲኖር ከኅብረተሰቡ ተለየቶ የበረሃ ማር እና አንበጣ እየበላ በጸጋ ያደገው የካህኑ ዘካሪያስ ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ ነበር።

ይህ የበረሃ ሰው በብሥራት የተወለደ ምስክርነትም ከጌታው አፍ የተነገረለት ነቢይ ነበር፥ " እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤" ማቴዎስ ፲፩ ፥ ፲፩ የተባለለት ወዴት እና እንዴት እንዳደገ ሳይታውቅ በአንድ ወቅት ማለትም የተነገረው ትንቢት ሲደርስ ብቅ ብሎ ሕዝቡን ሁሉ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር። እንዲህም ይላቸው ነበር "እኔ በውኃ አጠምቃችኃለው ከእኔ ይልቅ የሚበረታ እርሱ ሲመጣ በእሳት እና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኃል" እያለ የአዳኙን መምጣት ያበስር ነበር። ይህም ብቻ አልነበረም መጥምቁ ዮሐንስ ይል የበረው " ልባችሁን አቅኑ እርሱንም ለመቀበል ተዘጋጁ እያለ ስለ ጌታ ንጽህና ይሰብክ ነበር፤ ዮሐንስ ይህን ሲል ሁሉም ሃጢያቱን እየተናዘዘ ይጠመቅ ነበር፣ የሰው ዘርን በሥጋ እና በደም የተዋሐደው ጌታችን እና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮሐንስ መጣ፥ ለ፴ ዘመናት እናቱን ሲያገለግል በማኅበረሰቡ መካከል በጸጋና በሞገስ አድጎ ዛሬ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ጥሪውን ሰምቶ ከመጣው ሕዝብ መካከል ብቅ አለ፥ ትንቢት የተነገረለት፣ ሱባኤ የተቆጠረለት ደግሞም የብዙዎች ናፍቆት ለፍጡራን በተዘጋጀው ሥርዓትና ትህትናን ሊያሳይ ወደ ፍጡሩ ዘንድ ሊጠመቅ ሄደ።  ከሃጢያት በስተቀር ፈጽሞ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተዋሕዶ ምስጢር ሰው የሆነው ጌታ ወደ ዮሐንስ እራሱን ዝቅ አድርጎ ሊጠመቅ በመጣ ጊዜ ዮርዳኖስም ወደኃላው ሲመለስ፣ ኮረብቶችንም ልቅ እንደ እምቦሳ ጥጃ ሲዘሉ መጥምቁ ይህን አስተዋለ።
"ሰላም ለማይ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ዘአተቦ መንፈስ ቅሱስ ከመ አጥበቦ ሶበ መፅዓ ቃል እምሰማይ ለተናብቦ ነደ ለማየ ባሕር ከበቦ ማየ አመ የሐውር ፀበቦ" ወደ ዮሐንስ ዘንድ ሃጢያታቸውን ተናዘው ሊጠመቁ የሚመጡት በሙሉ በሃጢያት፣ በበደል ጎብጠው ከሃጢያታቸው ብዛት ጉስቁልና የሚታይባቸው ነበሩ፥ አሁን ግን ወደ ዮርዳኖስ ባሕር የገባው ከበፊተኞቹ የተለየ ነበር መጥምቁ ዮሐንስም የጌታውን መልክ ልክ ሲያየው ንጹህ እና ቅዱስ መሆኑን ፍጹም አምላክነቱን ሲረዳ እንዲህ ብሎ ለሕዝቡ ተናገረ ". . .በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢያት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። . . ." ዮሐንስ ፩ ፥ ፳፱  ጌታም በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ በመጣ ጊዜ፣ ዮሐንስ እንዲህ አለ ". . .
ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር።. . ." ማቴዎስ ፫ ፥ ፲፬ ታላቅነቱንም ለሕዝብ ሁሉ እንዲህ እያለ ያውጅ ነበር " የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኳን የማይባኝ ከእኔ በኃላ ይመጣል" ብሎ ነበርና ታዲይ ጌታም እንዲህ አለው " እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ እንፈጽም ዘንድ ይገባል. . ."  ዮሐንስም በዚያው ቃል ጌታውን አጠመቀ። በጥምቀቱም ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስም በርግም አምሳል ወረደ፣ እግዚአብሔር አብም በደመና ሆኖ እንዲህ አለ ". . .
ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።. . ." ማርቆስ ፱ ፥ ፯፣ ማቴዎስ ፫ ፥ ፲፯፣ ፪ኛ ጴጥሮስ ፩ ፥ ፲፯ "መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል ዝንቱ ውዕቱ ወልደየ ዘአፈቅር ውሎቱ ስምዕዎ" ብሎ ለሕዝቡ ሁሉ አስታወቀ። እንዴት ይደንቃል እንዴትስ ይገርማል እንዴትስ ያለ ታላቅ ነገር ነው፣ ፈጣሪ በፍጡር እጅ ተጠመቀ ይህንንም ታላቅ የሆነ ትህትና ለእኛ ዛሬ ገለጠልን። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቁ ጠላት ዲያብሎስ በእኛ ላይ የጻፈውን የእዳ ደብዳቤ በማየ ዮርዳኖስ አቅልጦ እንደ ሸክላም ሰባብሮ አጠፋልን የድኅነታችንም መጀመሪያ ሆነ፥ ባሕረ ዮርዳኖስ ለዘመናት ጠላት ዲያብሎስ የፃፈብንን የእዳ ደብዳቤ ደብቃ የኖረች ቦታ ነበረች፣ ነገር ግን በጌታችን ጥምቀት ተቀደሰች የሰው ልጅንም አርነት አወጀች። ዲያብሎስ የእዳውን ደብዳቤ አንዱን በዮርዳኖስ፣ ሌላውን በሲኦል ቀብሮት ነበር፣ በጌታችን ጥምቀት በዮርዳኖስ የተቀበረውን በጥምቀቱ ሲያጠፋልን፣ በሲኦል የተቀበረውን ደግሞ በሞቱ አጥፍቶልናል እና ክብር ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን አሜን።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም በጤና አደረሳችህ አደረሰን አሜን።


የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment