Tuesday, January 3, 2012

ሰበር ዜና - ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ


  • READ THIS ARTICLE IN PDF.
  • በየአህጉረ ስብከቱ ለሚፈጠሩት ችግሮች የአቡነ ጳውሎስ ግፊት እንዳለበት ቅዱስ ሲኖዶስ ገለጸ
  • አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ፓትርያርኩ ያቀረቧቸው አጀንዳዎች “ለአስቸኳይ ስብሰባ የማይበቁ ናቸው” በሚል አጣጥሏቸዋል::
  • በፓትርያርኩ እልከኝነትና ተንኮል ላይ ያመረሩት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት “የቤቱ ችግር ተጣርቶ መወገዝ ያለበት ይወገዝ፤ ስለ ወንጌል አገልግሎት፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰላም እና ልማት መነጋገር ሲገባን ቤተ ክርስቲያን በእርስዎ የተነሣ ስትበጠበጥ እና ስትናጥ መኖር የለባትም” በሚል አቡነ ጳውሎስን ሲገጹ እና ሲያስጠነቅቁ አርፍደዋል::
  • ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከሲዳማና ጌዲኦ ዞኖች አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት እንዲነሡ ‹በ15,000 ምእመናን ፊርማ› ቀርቧል የተባለው ‹አቤቱታ› ስድነት የተሞላበትና በአቡነ ጳውሎስ ግፊት የቀረበ የተሐድሶ መናፍቃን ሤራ መሆኑን ሲኖዶሱ ገልጧል፡፡ በሕገ ወጥ አድመኞች የቀረበውን ይህንኑ ስድ አቤቱታ በመቃወም 20,000 የሐዋሳ እና ዲላ ምእመና ያሰባሰቡት የተቃውሞ ፊርማ አቤቱታ ለሲኖዶሱ ጽ/ቤት ደርሷል::
  • አቡነ ጳውሎስ “ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም” የሚለውን ስመ ማዕርጋቸውን በመጠቀም በአኵስም ሀገረ ስብከት ላይ ሥልጣናቸውን የሚያጠናክር አጀንዳ አቅርበዋል፡፡ አጀንዳው አቡነ ጳውሎስ አስገነባዋለሁ ከሚሉት ሙዚዬም አገልግሎት ጋራ በተያያዘ አጠያያቂ ገጽታዎች እንዳሉበት ተነግሯል::

(ደጀ ሰላም፣ ታኅሣሥ 24/2004 ዓ.ም፤ January 3/2012)፦ አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ታኅሣሥ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች እንዳስታወቁት አስቸኳዩን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የጠሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ እና ድንገተኛ ስብሰባ ለመጥራት መንሥኤ የሆኑት አጀንዳዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው “አቡነ ገብርኤል ከሲዳማና ጌዲኦ ዞኖች አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት እንዲነሡ 15,000 ያህል ምእመናን የተቃውሞ ፊርማ አቅርበዋል” መባሉ ነው፡፡
ሁለተኛው አጀንዳ ደግሞ በረጅሙ ስመ ማዕርጋቸው ውስጥ “ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም” የሚለውን ሥልጣናቸውን የሚያጠናክር እንደሆነ የተነገረለት ነው፡፡ ይኸውም በአሁኑ ወቅት የትግራይ ማእከላዊ ዞን አኵስም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ሰላማን ከሀገረ ስብከቱ በማንሣት አልያም በገጠር ደረጃ በመወሰን እርሳቸው በሀገረ ስብከቱ ቀጥተኛ ቁጥጥር እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነው፡፡ በጸሎታቸውና ፍጹም መንፈሳዊነታቸው የሚታወቁት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ “እኔ ቆሞስ ልሆን ነው ወይስ ወዴት ልሄድ ነው?” በማለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አጀንዳ ማዘናቸው ተገልጧል፤ አዘውትረው በሚለዩበት “ይግባኝ ለታቦተ ጽዮን” በተሰኘው የተግሣጽ እና የአረኅርኆ ቃላቸው ጉዳዩን አብልጠው ‹እንደሚያመለክቱበትም› ተገምቷል፡፡
በሌላ በኩል አጀንዳው አቡነ ጳውሎስ አስገነባዋለሁ ከሚሉት ሙዚዬም ጋራ በተያያዘ ከአንድ የውጭ ኤጀንሲና ከሕገ ቤተ ክርስቲያን በተፃራሪ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና በአሜሪካ ካቋቋሙት የውጭ ግንኙነት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተጠሪ ጋራ በወል ለማሰባሰብ ላቀዱት የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ‹ሁኔታዎችን ለማስመቸት› እንደ ሆነ ተጠርጥሯል (ለዚህ ጥርጣሬ መነሻ የሆነውን መረጃ ዝርዝር እንደ ደረሰን እናቀርባለን)፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 14 ንኡስ አንቀጽ 1 እንደተመለከተው ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚጠራበት የማዕርግ ስምና መንበር “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት” የሚል ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ያለ ኤጲስ ቆጶስ (ሊቀ ጳጳስ) የሚመራ ሀገረ ስብከት እንደማይኖር በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የተመለከተ ሲሆን ኤጲስ ቆጶስ (ሊቀ ጳጳስ) አንዴ ከተሾመበት ሀገረ ስብከት ሊዛወር እንደማይችል፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዕድገት ወይም በሌላ ሥራ ምክንያት እንዲዛወር አስፈላጊ ከሆነ ወይም በተመደበበት ቦታ ለመቆየት አስቸጋሪ ሆኖ ከተገኘ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጠንቶ በውሳኔ ሊዛወር እንደሚችል በአንቀጽ 22 ከንኡስ አንቀጽ 1 - 3 ላይ ተደንግጓል፡፡
ሁለቱም አጀንዳዎች ሲኖዶሱን ለድንገተኛ የስብሰባ ጥሪ የማያደርሱ መሆናቸውን የተቹት የአስቸኳዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተሳታፊዎች÷ “በአስቸኳይ መነጋገር ካለብን መነጋገር ያለብን እርስዎን በተመለከተ ነው፤ ያቀረቡት አጀንዳ ሆነ ተብሎ ግጭት ለመፍጠር የታሰበበት ነው፤ ይህንንም የሚያደርጉት እርስዎ ነዎት፤ ከጀርባውም የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አለበት፤ ቤቱም ድጋፍ እየሰጠበት ነው፤ ስለ ወንጌል አገልግሎት፣ ገዳማት ልማት፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደር መነጋገር ሲገባን ሁልጊዜ በዚህ መቸገር አለብን? ጥለን ወደ ገዳም እንሂድ እንዴ? ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ መበጥበጥ ሁልጊዜ መናጥ አይገባትም፤ ነገሩ የሃይማኖትም ጉዳይ ስላለበት ከቤቱ ጀምሮ ተጣርቶ፣ ተለይቶ መወገዝ ያለበት ይወገዝ!!” በማለት በፓትርያርኩ የማያባራ እልክ እና ተንኮል መማረራቸውን በመግለጽ ቁርጥ ማሳሰቢያቸውን አስታውቀዋቸዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ ሁለቱንም አጀንዳዎች አጣርቶ እና አጥንቶ ለግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚያቀርብ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የሚመራ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሕግ ባለሞያዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም በማዘዝ ለግማሽ ቀን ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ አጠናቆ ተነሥቷል፡፡ በተለይም የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እንዲነሡ ቀርቧል የተባለው የ15,000 ሕዝብ የፊርማ አቤቱታ ከጀርባው የተሐድሶ መናፍቃኑ ቅስቀሳና ሤራ እንዳለበት አስረግጦ የተናገረው ቅዱስ ሲኖዶስ÷ የሚቋቋመው ኮሚቴ ፈርመዋል የተባሉ ግለሰቦችን ሃይማኖታዊ ማንነት ጭምር በሚገባ እንዲያጣራ ነው ያዘዘው፡፡ በስብሰባው ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በበኩላቸው እርሳቸውም የሕገ ወጥ አድመኞቹን ሤራ የሚቃወም የ20,000 ምእመናን ፊርማ መያዛቸውን በማስታወቅ እንደተባለው ችግሩ ያለው በቤቱ [በዚያው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፓትርያርኩ ዘንድ] በመሆኑ ጉዳዩ በሚገባ ተጣርቶ ችግሩ በቁርጥ እንዲለይለት በአጽንዖት ጠይቀዋል፡፡ ይኸው የ20,000 ምእመናን የተቃውሞ ፊርማ ከሐዋሳ እና ዲላ ከተሞች ምእመናን የተሰበሰበ ሲሆን ከአስቸኳዩ ስብሰባ ቀደም ብሎ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደርሶ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተከታታይ ዘገባዎቻችን እንዳስታወቅነው “አስቸኳይ እና ድንገተኛ ነው” የተባለው ይኸው አጀንዳ በርግጥም በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወቅት ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተደጋጋሚ አቅርበውት በምልአተ ጉባኤው አባላት ውድቅ የተደረገባቸው ነው፡፡ አጀንዳው የተገፋበት መነሻ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ዋዜማ በመናፍቁ አሰግድ ሣህሉና ሌሎች የሕገ ወጥ ቡድኑ አባላት አስተባባሪነት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተጠርቶ በነበረው የተቃውሞ ትዕይንት “ከሀገረ ስብከቱ የተለያዩ ከተሞች የመጡ ናቸው” በተባሉ ግለሰቦች እንደቀረበ የተነገረ ጥያቄ ነበር፡፡
ራሳቸው አቡነ ጳውሎስ እንዳነሣሡትና ድጋፍም እንደሰጡበት የተነገረውን ይህንኑ የሕገ ወጦች ጥያቄ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የታሰሩ አድመኞችን ጉዳይ ለመከታተልና ወደመጡበት ለመመለስ ፓትርያርኩ በልዩ ትእዛዝ ተቀብለው መስተንግዶ ባደረጉላቸው ወይዛዝርት በኩል ዐሥር ሺሕ ብር መስጠታቸው ተዘግቦ ነበር፡፡ በአንጻሩ በወቅቱ የጥቂት ሕገ ወጦችን የተቃውሞ ትዕይንት በፀረ ተቃውሞ ትዕይንት በመመከት 131 የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ምልአተ ጉባኤው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ላይ ርምጃ እንዲወስድ ላቀረቡት ባለአምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ድጋፍ ለመስጠት በመገኘታቸው “ሁከት በማነሣሣት” በሚል ለእስር ለተዳረጉ ስምንት ወጣቶች አንዳችም ሐዘኔታ አላሳዩም፡፡
ይሁንና የዘንድሮው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም በፕሮቴስንታንት ድርጅቶች እየተደገፉ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በመቀሰጥ እና ምእመኑን በመከፋፈል የጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩ ስምንት ማኅበራትና የሕገ ወጥ ቡድኑ አባላት የሆኑ ግለሰቦችም ኑፋቄ ተመርምሮ እንዲቀርብለት፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሓላፊ የነበሩት አባ ሰረቀም ከሓላፊነታቸው ተነሥተው እምነታቸው እንዲመረር ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ቀደም ሲል አቡነ ጳውሎስ ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ወጥ ሰባክያን ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም የተጉትን የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዓለም እሸትን ያለ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ስምምነት ከቦታቸው ለማስነሣት ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋራ በመመካከር ወደ አዲስ አበባ ለመጣው የጆቢራ ቡድን ብር 5000 ሰጥተው መሸኘታቸው ይታወሳል፡፡
በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላይ “የማይበርድ ቂም” እንዳላቸው በእነ ያሬድ አደመ የተነገረላቸው አቡነ ጳውሎስ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብፁዕነታቸውን ከሀገረ ስብከቱ ለማስነሣት በተደጋጋሚ አቅርበውት ውድቅ የተደረገባቸው አጀንዳ አሁንም መሣሪያ ያደረገው በእነ ያሬድ አደመ የተጭበረበረ ቅስቀሳ ተሰብስቧል የተባለውን የ ‹15,000 ምእመናን› የተቃውሞ አቤቱታ ፊርማ ነው፤ የተጭበረበው ፊርማው የተሰበሰበበት ርእሰ ጉዳይም ፈርመዋል የተባሉት ግለሰቦች ማንነትም ነው፡፡
የዜና ምንጮች ከሐዋሳ እንደ ተናገሩት፡- ሕገ ወጦቹ እነ ያሬድ አደመ የአቤቱታ ፊርማው ያሰባሰቡበት የሽፋን ርእሰ ጉዳይ “በሐዋሳ መስቀል አደባባይ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ፈቃድ ለመጠየቅ” በሚል የተቀሰቀሰበት ነው፡፡ ቆይቶ ይኸው የአቤቱታ ፊርማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “በሀገረ ስብከታቸው የሉም፤ ከሀገረ ስብከቱ ይነሡልን” የሚል ሆኖ ቀርቧል፡፡ በግለሰብ ቅጽር ውስጥ በተከራዩት አዳራሽ ስብከት እንደሚያካሄዱ የተነገረላቸው ሕገ ወጦቹ እንደ ሰበብ የተጠቀሙበት ብፁዕነታቸው ጥቅምት 20 ቀን 2004 ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ከሀገረ ስብከታቸው ውጭ ለአንድ ወር ያህል መቆየታቸውን ነው ተብሏል፡፡
በእምነት መካከል ያለው የአስተምህሮ ድንበር የማይገዳቸው እነ ያሬድ አደመ ዘረኝነትን በመጠቀም ወንጌልን መነገጃ በማድረግ እና በሌሎች መንገዶች እንዳሰባሰቡት በተነገረው በዚህ የተቃውሞ አቤቱታ ላይ ስማቸው እና ፊርማቸው የተመለከቱት ግለሰቦች በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ እና ሰንበት ት/ቤት ማጣራት ቢደረግ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ለመሆናቸው አጠራጣሪ እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገረ ስብከቱ የሠርክ ዐውደ ምሕረት ጉባኤያት በምድብ እና ተጋባዥ መምህራን በተጠናከረበት፣ ሰንበት ት/ቤቶች የአገልግሎት መርሐ ግብሮቻቸውን ባጎለበቱበት ሁኔታ ይህ በአድማ የተሰበሰበው የሕገ ወጡ ቡድን ጥያቄ በርግጥም የቤተ ክርስቲያናችንን ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የማይሹ የተሐድሶ መናፍቃኑ ሤራ እንዳለበት ግልጽ ያደርገዋል፡፡
መ/ር አእመረ አሸብር
ሰሞኑን በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሃይማኖታቸው ርቱዕነት ላይ ጥያቄ ያነሣባቸው የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ መ/ር አእመረ አሸብር (ፎቶውን ይመልከቱ) ወደ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊነት መዛወራቸው፣ በሐረር እና ድሬዳዋ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆችና አቀንቃኞች በአካባቢው የሰነበቱትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን እንደ ልብ ለማግኘት የቻሉበትን ባለሟልነት፣ በአንጻሩ በሁለቱም አህጉረ ስብከት ሙስናንና ኑፋቄን የሚዋጉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዐይናችሁ ለአፈር የተባሉበትን መገፋት ስንመለከት አቡነ ጳውሎስን አዘውትረን ከምንገልጽበት የቅንነት ማነስ፣ እልከኛነትና ተንኮል በላይ ጉዳዩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፋፍሎ የማዳከም ልዩ ተልእኮ እንደ ሆነ በውስጣችን የምናጉላላውን ስጋት በግልጽ እንድንናገረው ያደርገናል፡፡
ከታኅሣሥ 20 - 22 ቀን 2004 ዓ.ም በአሰበ ተፈሪ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት የተቆጣጠሩት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዞ የተለየው የ‹ሃይማኖተ አበው› ርዝራዦች የሆኑ ማኅበራት ከፓትርያርኩ ባገኙት ቀጥተኛ ፈቃድ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ ፈቃድ ውጭ የሰበካ ጉባኤያቱን ልዕልና እየተጋፉ በሊቃውንት ጉባኤ ሃይማኖታቸው እየተመረመረ ያሉ ሕገ ወጥ ሰባክያን መድረክ እንዲያገኙና እንዲፋንኑ ማድረጋቸው፤ በሐረር የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች ቀድሞ ይነሡልን ያሏቸውን ብፁዕ አቡነ ያሬድን በማመስገን እንዲቆዩላቸው ለመጠየቅ፣ በጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተመደቡትን ብፁዕ አቡነ አብርሃምን በመቃወም እንዳይመጡ ለመከላከል በቅርቡ ለማካሄድ ባቀዱት ጉባኤ ላይ ፓትርያርኩ እንዲገኙላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ አቡነ ጳውሎስን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ  ተሐድሶ ተጋድሎ ዋነኛ ዒላማ አድርገን በይፋ እንድንታገላቸው ለማድረግ ከበቂ በላይ የሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ለዚህም ባለፈው ሳምንት እሑድ በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት መካነ ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ አቡነ ያሬድን ለመሸኘት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ለመቀበል በተከናወነው ደማቅ መርሐ ግብር ላይ ከሁለቱም ብፁዓን አባቶች የተላለፉት መልእክቶች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፤ ምእመኑ በሽኝት-አቀባበሉ መርሐ ግብር ላይ የነበረው ስሜትና ተሳትፎም የሚያበረታታ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ያሬድ “እኔ ብሄድም ሌላ አባት ቢመጣም ሕግ አይለዋወጥም፤ አባቶቻችን እንዳደረጉት ነው የምናደርገው” በማለት ሐረር የተሐድሶ መናፍቃን የሚደራጁበት መደብር/ቅልዝ መሬት እንዳይሆን የወሰዱት አቋም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው፣ “እኔ ውሸት አልፈልግም፤ መርሔ አሳምነኝ ወይ ላሳምነህ የሚል ነው፡፡ መጪው ጊዜ ስለ ሃይማኖታችን አብረን የምንሠራበት፣ የምንነጋገርበት፣ የምንጠብቅበት፣ የምናስጠብቅበት ይሆናል” በማለት የተሐድሶ መናፍቃንንና በአስተዳደራዊ መዋቅሩ የተሰገሰጉ አቀንቃኞቻቸውን ግንባር ለግንባር ለመፋለም መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡
በአንጻሩ በምዕራብ ሐረርጌ/አሰበ ተፈሪ የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ከኢትዮጵያ ውጭ በመሆናቸውና እስከ አሁን በሀገረ ስብከቱ ባለመገኘታቸው፣ የቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ወደተዛወሩበት ወላይታ ሶዶ በመሄዳቸው ሀገረ ስብከቱን በማተራመስ ረጅም ታሪክ ያላቸው የቀድሞዎቹ መናፍቃን ክትያዎች የሆኑ የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኝ ማኅበራት ከጥቂት ግለሰቦች ጋራ በመተባበር ለሕገ ወጥ ሰባክያን መድረክ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩ ከሕገ ወጦቹ ጋራ የዓላማ እና ጥቅም ተጋሪ የሆኑ የአቡነ ጳውሎስ ባለሟሎችና የራሳቸው የፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ እንዳለበት ምንጮች ያረጋገጡ ቢሆንም ሀገረ ስብከቱ ያለተከላካይ አባት መቆየቱ አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳደረገም የሚካድ አይደለም፡፡ (የዚህን ዜና ዝርዝር በቆይታ እንመለስበታለን)
 
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

1 comment:

  1. huli mechekachek kirsthos yestemaren fikir new
    lemin anwadedim egizeabeher telo mefite yamtalin

    ReplyDelete