Wednesday, January 11, 2012

የተዋሕዶ ቤተሰቦች ለምን?

በተደጋጋሚ ከተለያዩ የዝግጅታችን ተከታታዮች
  • የተዋሕዶ ቤተሰቦች ማናቸው?
  • የናንተ የጡመራ መድረክ ለምን አስፈለገ?
  • ለቤተክርስቲያን መቆማችሁን በምን እናውቃለን?
  • ዓላማችሁ ምንድነው? እና የመሳሰሉት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ከአንባቢያን ስለመጡ ሙሉም ባይሆን በመጠኑ የመልሳሉ ያልናቸውን ነጥቦች ከዚህ በመቀጠል አስቀምጠናቸዋል እና ጥያቄያችሁን ወይም አስተያየታችሁን በተለመደው መልኩ በኢሜል ወይም በፊስ ቡክ ልታደርሱልን ትችላላችሁ፤ የቻልነውን መልሰን ያልቻልነውን ሊቃውንቱን ጠይቀን መልሶቻችሁን ለመስጠት ከወዲሁ ተዘጋጅተናል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ከውስጥም፣ ከውጪም በሚመጡ ወራሪዎች እና ሃይማኖት እና ትውፊት ለዋጮች ስትታመስ ኖራለች፤ ምንም እንኳ ቤተክርስቲያኒቱ በጠላቶቿም ሳይቀር "ስንዱ እመቤት" እየተባለች እስከመጠራት ብትደርስም ፈተናው በየደረጃው መስራቿ ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ በቅናት ተነሳስተው ከሰቀሉበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ በዘመናችን እስከተነሱት ሃይማኖት ለዋጮች፣ ትውፊት ከላሾች ድረስ በብዙ ተፈትናለች፥ ዲያብሎስም ፆሩን መወርወሩን አያቆምም በተክርስቲያንም በክርስቶስ ደም ጸንታ ትቆማለች፡፡ ለዘመናት የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ፤ቀኖናና ትውፊት ሲያስተላልፉ የነበሩ ሁለት አይና ሊቃውንትን በአብነት ት/ቤቶች ስታፈራ ኖራለች፡፡ ከዚህም በላይ ቤተክርስቲያኒቱ ራሷን የምታስተዳድርበት የራሷ የሆነ ሥርዓት ለሺህ ዓመታት የነበራት ሲሆን ይህም አንድነቷን በመጠበቅ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ኖሯል፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያኒቱ ለሀገሪቱ ዘመናዊ አስተዳደር፤ ቋንቋ፤ ባህል፣ ስነ-ጽሁፍ፣ ስነ-ስዕል እና ስነ-ህንፃ ወዘተ ከፍተኛ የልማት አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ብዙ ፈተናዎችን ስትጋፈጥና በእግዚአብሄር እርዳታም ስትወጣ ኖራለች ከነዚህም ዋነኞቹ የዮዲት ጉዲት ጭፍጨፋ፣ የግራኝ መሃመድ ህንፃ ቤተክርስቲያንና ቅርስን የማውደም ዘመቻ እንዲሁም የነገስታት እና የመሪዎች የሀይማኖት ጥላች  አፄ ሱስዮስ በመካከለኛው ዘመን ያደረሱት በደል፣ የደርግ መንግስት የቤተክርስቲያኒቱን አንጡራ ሀብት መውረስ የመሳሰሉት በአብነት የሚጠቀሱ ፈተናዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዘመን የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች/ ፌስ ቡክ፤ ብሎግ፤ ዌብ ሳይት ወዘተ/ መስፋፋትን ተከትሎ ብዙ አካላት በኦርቶዶክሳዊነት ስም እነዚሁ ሚዲያዎችን በመጠቀም ለእነሱ በተመቸ መልኩ የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ፤ ቀኖናና ትውፊት የሚሽሩ መልዕእክቶች ሲያተላለፉ፣ እንዲሁም ምንፍቅናን ሲያስተምሩ በእጅጉ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ የተዛቡ መልእክቶች ለነዚህ ሚዲያዎች ቅርብ የሆኑትን በተለይ ከሀገር ውጭ ያሉ ምእመናን ግራ እያጋቡ እና በክርስቲያኖች መካከል ልዩ
ነቶችን እና ክፍተቶችን እየፈጠረ ይገኛል እንደእውነቱ ከሆነ የነሱ ዓላማቸው ይህ ስለሆነ በመጠኑም ቢሆን የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል የቤተክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖናና ትውፊት ጠብቀው የሚያገለግሉ የማህበራዊ ሚዲያዎችም አሉ፡፡ በመሆኑም የተዋሕዶ ልጆችን ተገቢውን ወቅታዊ መረጃ በመስጠት እና ተሰባስበን በትክክለኛ መስመር ያሉትን ትምህርቶችን ይበልጥ የምናስፋፋበት ፤በስህተት ከመሰመር... የወጣውን የምንመልስበት፤ አውቆ በጥፋት ያለን የምናጋልጥበትና ሌሎች ምእመናን እንዲጠበቁ የምናደርግበት አንድነት ያስፈልገናል፡፡

በሌላ በኩል በተለያየ ደረጃ በተለያየ ምክንያት ስምምነት ማጣት ፤ ክፍፍልና የፍቅር መቀዝቀዝ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ይስተዋላል፡፡ የተዋሕዶ ቤተሰብ ከሃይማኖት ህጸጽ በስተቀር ያሉ ልዩነቶች በመነጋገርና በመከራከር እንዲፈታ ከማድረግ በተጨማሪ ከጠብና መለያየት ይልቅ ፍቅርና አንድነት በኦርቶዶክሳውያን መሃል እንዲሰፋፋ በጽናት ይሰራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች ከበቂ በላይ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ወንድሞችና እህቶች አሉ፡፡ በመሆኑም በሌላ እምነት ላሉት ኢትዮጵያዊያን አባቶች፣ እናቶች፣ እህቶች እና ወንድሞች በሥርዓት ጥያቄ ለሚያቀርቡ በቂ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ሰዎችን ከተሳሰተ መንገድ መመለሰ የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡
በመሆኑም እርሶዎም ለዚህ አላማ መሳካት የበኩልዎን ኦርቶዶክሳዊ ግዴታዎን እንዲወጡ በትህትና እንጠይቃለን፡፡ በተለይ የቤተክርስቲያኒቱን ከጠራው ምንጭ ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ተምራችሁ በተለያየ ደረጃ የምታገለግሉ ወንድሞች ይህ አላማ ካለእናንተ ተሳትፎ ለማሳካት ስለሚከብድ በንቃት እንድትሳተፉ በእግዚአብሄር ስም እንጠይቃለን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች 
በፌስ ቡክ kurtegnalejoch@facebook.com
ማይኘት ይችላሉ ቸር ይግጠመን
የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment