Thursday, January 5, 2012

ቤተ ክርስቲያናችን በሀገረ አሜሪካን በይበልጥ ውስብስብ የሆነ ችግር ውስጥ እየገባች ነው

ይህ ጽሁፍ አሐቲ ተዋሕዶ ከሚባል ፌስ ቡክ የተገኘ ነው፤ ይጠቅማል ብለን ስላሰብን እንደሚከተለው አቅርበነዋል መልካም ንባብ ይሁንልዎ።

ባለን መረጃ በሰሜን አሜሪካ በ26 ግዛቶች(እስቴቶች) ውስጥ 106 አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ:: በሁሉም  እስቴቶች ቢቆጠር የአጥቢያዎቹ ብዛት ከ106 በላይ ይሆናል ማለት ነው:: እነዚህ አጥቢያዎች ሁሉ በውጫዊ እና  በውስጣዊ ተጽኖዎች ምክንያት በፖለቲካ፣ በዘር እና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የተከፋፈሉ ናቸው:: በአስተዳደር መዋቅር  ደግሞ ስደተኛ ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ፣ በግለሶዎች፣ እና በኢትዮጵያ ሲኖዶስ በማለት የተለያዩ ናቸው:: በአስተዳደር  ብቻ ሳይሆን በሃይማኖታዊ ሥርዓት ጭምር የተላያየ አቋም ያላቸው አጥቢያዎች አሉ:: ለምሳሌ እመቤታችን ቅድስት  ድንግል ማርያም የአዳም ኀጢአት ወርሳለች በማለት በግል የመሠረቱት አጥቢያቸው ውስጥ የሚያስተምሩ እነ አባ መዓዛ  በየነ እና ቀሲስ አስተራየ ጽጌ የሚጠቀሱ ናቸው:: እንዲሁም ደግሞ አንዳንድ አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት በይፋ  በኦርጋን መዘመር ተፈቅዶዋል በማለት ወደ መቅደሱ ኦርጋን አስገብተው የሚዘምሩ አሉ::

ይህ በአስተዳደር፣ በፖለቲካ፣ በዘር፣ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅም እና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩት አጥቢያዎች  እንዴት አንድነት ማምጣት ይቻላል? የተወጋገዙት የጳጳሳት መታረቅስ ይህንን ችግር ይፈታው ይሆን? ጊዜ ይፍታው  ተብሎስ የሚተው ጉዳይ ነውን? አሐቲ ተዋሕዶ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር ከተጠበቀ ለዚህም መዋቅር  መጠበቅ በጋራ ከሰራን አንድነት ይመጣል ብላ ታምናለች:: የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅሯ ከግንዱ ተለይቶ  እዚህ ሀገረ ቅርጫፎች ብቻቸውን ከተስፋፉ ወደፊት ከፕሮስቴንታንቶቹ የሚለየን ነገር አይኖርም የሚል ስጋት አለን::  የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር መጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው ብለንም እናምናለን::


በሰሜን አሜሪካን ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማት ፈተና ከጅምሩ ብናየው የአመሠራረት ችግር አልነበረባትም::  የመጀመርያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኒዎርክ ቅድስ ሥላሴ መሆኑን መዛግብት ያስረዳሉ:: ይቺ አጥቢያ ቤተ  ክርስቲያን በንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታነት እና  ንብረትነት ተገዝቶ ነበረ:: በወቅቱ ንጉሰ ነገሥቱ እና አገልጋዮቹ ካህናት ቤተ ክርስቲያኒቷ ሲገዙ በግል ስማቸው  አላስመዘገቡትም ነበረ:: የዚህ ሀገር ሕግ እና ሥርዓት በሚያዘው መሰረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን ባለቤትነት ስም ገዝተው አስቀመጡልን:: ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ ብቸኛው በቤተ ክርስቲያናችን  ይዞታነት እና ንብረትነት ቆይቶልናል:: ይህም  ከትውልድ ወደ ትውል ሲተላለፍ ይኖራል ማለት ነው::

ባለፉት  ዘመናት ቤተ ክርስቲያናችን ሰሜን አሜሪካን እና የካረቢያን ደሴቶች እንደ አንደ ሀገረ ስብከት አዋቅራ በአንድ ሊቀ  ጳጳስ ስታስተዳድር ለ፳ /ሃያ ዓመታት ያህል ቆይታለች:: በዚህ ቆይታ ግዜ ነው ነገሮቹ እየተበላሹ የመጡት::  አስተዳደራዊ መዋቅሩ እየላላ መሄድ ጀመረ:: በደርግ ዘመነ መንግስት ወደ ሰሜን አሜሪካን በስደት የሚፈልሱ  ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መጥቶ እንደነበረ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ይመሰክራሉ:: በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያውያኑ  በብዛት በሰፈሩበት ግዛቶች በዋሽንግተን ዲሲ እና በሎሳንጀለስ ከተሞች ላይ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሰረቱ::  የአጥቢያዎቹ አመሠራረት ላይ ችግሮች መታየት ጀመረ:: እነዚህ አጥቢያዎች ሲመሰረቱ እንደመጀመርያው እንደ ኒዮርክ  ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ሌላ መንገድ ተከትለው ነበር:: የተመሰረቱት አጥያዎች በመሰረቱዋቸው ግለስዎች  ስም እና ይዞታነት አስመዘገቧቸው:: ከዛ ግዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሚመሰረቱት አጥቢያዎች በአጠቃላይ ማለት  ይቻላል የሚመዘገቡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ ይዞታነት እና ንብረትነት ሳይሆን  አጥቢያዎቹን በሚመሰርቱ  ግለብዎች ስም ነው:: እናም አሁን እስካለንበት ግዜ ድረስ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን  የአመሠራረት ችግር አለ:: መሥራቾቹ ምእመናን እነሱ በሚፈልጉት መልክ ሁለት ዓይነት መተዳደርያ ደንቦች አዘጋጅተው  አጥቢያዎች ይመሰርታሉ:: የሚፈልጉት አስተዳዳሪ ለመሰረቱት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይሾማሉ ወይም ያሾማሉ::

የደርግ  መንግስት ከወደቀ በኋላ ሰሜን አሜሪካን ከካረቢያን ደሴቶች ተለይታ ለብቻው እንደ አንድ አንድ ሀገረ ስብከት  ተዋቅራ ለ14 ዓመታት ያህል ቆይታለች:: በዚህ ግዜ ችግሮች በይበልጥ እየተወሳሰቡ መጡ:: ለችግሩ መወሳሰብ  ምክንያት በኢህአዴግ መንግሥት ተገፋን መንበራችን ተቀማን የሚሉት ጳጵሳት ወደ እዚህ ሀገር መጥተው የራሳችን ሲኖዶስ  መሰረትን አሉ:: ሌላ ሶስተኛ ወገን ደግሞ “ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ አንቀበልም እዚህ ሀገር በስደት ተመስርቶዋል  የተባለው ሲኖዶስ አንቀበልም” በማለት ራሳቸውን “ገለልተኛ” ብለው ተመሰረቱ:: ከፖለቲካው በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን  በዘር ተከፍላ “ሰደተኛ ሲኖዶስ” ነን የሚሉት ጎንደሬዎች፣ “ገለልተኛ” ነን የሚሉት ሸዋዎች እና በኢትዮጵያ  ሲኖዶስ ነን የሚሉት ደግሞ ትግሬዎች በመባል መቧደን ጀመሩ:: ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ መሀል ሰፋሪ ተባሉ::

የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ የሰሜን አሜሪካን ግዛቶችን ለሦስት ተከፍለው ቤተ ክርስቲያናችን ሦስት ሀገረ ስብከቶችን  አቋቁማ ሦስት ጳጳሳት ወደ እዚህ ሀገር ተመድበው መጡ:: ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለካሊፎርንያ እና ምዕራብ እስቴቶ  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ አብረሃም ለኒዮርክ እና ለሰሜን ምስራቅ እስቴቶች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  እና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ለዋሽንግተን ዲስ እና ለደቡብ ምስራቅ እስቴቶች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመደቡ::  ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል እና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ቀድሞ አሜሪካ ሀገር ነዋሪ ስለነበሩ እና የየራሳቸው አጥቢያ ቤተ  ክርስቲያን በስማቸው ስለነበራቸው ምእመናን አንቀበል፤ ”እናተ ማን ናችሁ? ከእኛ አትለዩም ትናንት እንደ እኛው  ገለልተኞች ነበራችሁ አሁን ምን አግኝታችሁ ነው የተመለሳችሁ” ስላላቸው ሁለቱትንም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ:: በእነሱ  ምትክ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ብፁዕ አቡነ ዮስጣጥዮስ ተመደቡ:: ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ለስድስ ወራት ብቻ  ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ:: በቦታቸውም የኒዮርክ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ ብፁዕ አቡነ አብረሃም ለዋሽንግተን ዲሲ  እና ደቡብ ምስራቅ እስቴቶች ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመደቡ:: ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ ደግሞ ለኒዮርክ እና ለሰሜን ምስራቅ  እስቴቶች እስቴቶች ሊቀ ቀጳጳስ ሆነው ተመደቡ::

እንግዲህ ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ግዜ ከዛ በፊት ለብዙ ዘመናት ያህል ያልነበሩ በዓይን የሚታዩ በእጅ የሚዳሰሱ  ለውጦች መታየት ጀመሩ:: ለምሳሌ የሀገረ ስብከቶቹ ጽፈት ቤት መቋቋም እና በቤተ ክርስቲያናችን ቃለ ዓዋዲ መሰረት  ለሀገረ ስብከቶቹ የሰበካ ጉባኤ  የሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ መዋቀር ተጀመረ:: ባለፉት ዘመናት እንደ ኀጢአት ይቆጠር  የነበረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር መጠበቅ በይፋ ትምህርት መሰጠት ተጀመረ:: ምእመናኑ በተለይም  ወጣቶች ስለ ሀገረ ስብከት እና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅር በቂ ግንዛቤ መጨበጥ ጀምረው ነበረ::

ይህ በእንዲህ እያለ በዘንድሮው የጥቅምት ወር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዛሬ ስድስት ዓመት ከተዋቀሩት ሦስት  ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ሁለቱን ሀገረ ስብከቶች በማጠፍ አንድ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ብቻ መደበ:: እነዚህ  ሁለቱ ሀገረ ስብከቶች ማለትም የዋሽንግተን ዲሲ እና የደቡብ ምስራቅ እስቲቶች፣ ካሊፎርኒያ እና የምዕራብ እስቴቶች  በተፈጥሮአዊ አቀማመጣቸው በጣም የተራራቁ በመሆናቸው በአንድ ሊቀ ጳጳስ ብቻ ለመተዳደር በጣም አስቸጋሪ ነው::  በሀገራችን የአክሱም ሀገረ ስብከት ከደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ጋረ መቀላቀል እንደማለት ነው:: ይባስ ብለው ለሀገረ  ስብከቱ የተመደቡት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ቀድሞ የነበረውን የሀገረ ስብከቶቹን ጅምር ሥራ አልቀበልም  በማለት የራሳቸው መንገድ መጓዝ ጀመሩ:: መጀመረያ የነበረውን የሀገረ ስብከት ጅምር ሥራዎች ላይ ችግር ካለባቸው  እንዲስተካከሉ ማድረግ ትተው የነበረውን በማፍረስ ሥራ ጀመሩ:: ይህ የማፍረስ ተግባር ግን በሕገ ሰብ እና በሕገ  እግዚአብሔር የሚያስጠይቅ ነው:: የነበረውን ጅምር ሥራ አፍርሰው የራሳቸ ሌላ ሀገረ ስብከት አቋቋሙ::

በዚህም ምክንያት መጀመርያ የነበረው የዋሽንግተን ዲሲ እና የደቡብ ምስራቅ እስቴቶች ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ  የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሥራ በመቃወም የአቋም መግለጫ አወጣ:: በሀገረ ስብከቱ ውስጥ  የሚገኙት አጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት በሥርዓተ ቅዳሴ የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ስም እንዳይጠራ እና ከብፁዕነታቸው ጋር  አብሮ ለመስራት እንማይቻል የሀገረ ስብከቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ አስተላለፈ:: ከፊሎቹ አጥቢያዎች ይህንን  ውሳኔ ሲቀበሉ ከፊሎች ግን በሥርዓተ ቅዳሴ ስማቸውን እንጠራለን ነገረ ግን ቀድሞ የነበረውን ሀገረ ስብከት  ብፁዕነታቸው እስካልተቀብሉት ድረስ አብረናቸው አንሰራም አሉ:: ስም መጥራት አብሮ ግን አለመስራት የሚል አቋም  የያዙ አሉ፤ ሌሎች ደግሞ የሀገረ ስብከቱ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ውሳኔ ተቀብለው የቀጠሉ አሉ:: በዚህም ምክንያት  በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የነበሩት አጥቢያዎች መካከል ልዩነት መፈጠሩን እየተሰማ ነው::

ቀድሞ የነበረው የካሊፎርኒያ እና የምዕራብ እስቴቶች ሀገረ ስብከት የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ግን እስከ አሁን ድረስ ያለው አቋም ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም::
ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ስታዋቅር ዘመኑ በሚፈቅደው ሁኔታ በጥናት የተመረኮዘ መሆን ያለበት ይመስለናል:: ጥናቱም የሚከተሉትን ነጥቦች ቢያካትት መልካም ነው:-
  • የአካባቢው ሁኔታ፣
  • ያሉት የአጥቢያዎች ብዛት እና አጥቢያዎቹ ያሉበት ሁኔታ፣
  • በአንድ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚጠቃለሉ እስቴቶች ብዛት፣
  • በዚህ ሀገር የሚገኙት ሌሎች አሐት አቢያተ ክርስቲያናት የሀገረ ስብከት አወቃቀር ተሞክሮ ማየት፣
  • ወደ እዚህ ሀገር የሚመደቡት ሊቃነ ጳጳሳት ቀደምት ለዚህ ችግር ተሳትፎ የሌለባቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ፣
  • የሚመደቡ ሊቃነ ጳጳሳት የዚህ ሀገር ሁኔታ በደንብ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያናችን በሰሜን አሜሪካ በአስተዳደር እና እንዲሁም በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጭምር ከግዜ ወደ ግዜ እየተወሳሰበች ትገኛለች::


የመላው ዓለም የተዋሕዶ ቤተሰብ

No comments:

Post a Comment