Friday, October 31, 2025

በአርሲ የእልቂት ድግሱ እንደቀጠለ ነው፤ ለማን አቤት ይባል???

አርሲ በኦርቶክስት ደም ታጥባለች ፤ 

በምሥራቅ  አርሲ  ሽርካ  ወረዳ ሄላ  ዘባባ ቀበሌ  ከሚኖሩ ኦርቶዶክሳዊያን ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ መታገታቸው ተሰማ፡፡

በወረዳው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ115 በላይ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውና ከ16 በላይ ዐብያተ ክርስቲያናት መዘጋታቸው ታውቋል።

ጥቅምት ፲፱/፳፻፲፰ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ 

ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን በደረሰው መረጃ ጥቅምት  17 ቀን 2018  ዓ.ም ከለሊቱ 4:00 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ ሄላ ዘባባ ቀበሌ አርሴማ አጥቢያ የሚኖሩ ምእመናን በታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ ደግሞ መታገታቸው ተገልጿል።

ከተገደሉት ምእመናን ውስጥ የአንዱ ሟች አባትና ወንድም መታገታቸው በመረጃው የተገለጸ ሲሆን ታፍነው የተወሰዱት ምእመናን ስለሚገኙበት  ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል፡፡

በመረጃው እንደተነገረው የሞቱት ሦስቱ ኦርቶዶክሳውያን በትላንትናው ዕለት ጥቅምት 18  ቀን  2018  ዓ.ም  ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2016 ዓ.ም መስከረም 02 ጀምሮ  እስከ  2017 ዓ.ም  ድረስ ያለማቋረጥ በወረዳው ከ115 በላይ ምእመናን የተገደሉ  ሲሆን  27  ኦርቶዶክሳዉያን  ደግሞ አሁንም  ድረስ  ታግተው  ያሉበት  እንደማይታወቅ  ነዋሪዎቹ  ለጣቢያችን  ገልጸዋል።

በግድያ  ያላበቃው  መከራና  ስቃይ  በሽርካ  ወረዳ  ብቻ  በዘጠኝ  ቀበሌዎች  በሺዎች የሚቆጠሩ  ኦርቶዶክሳዉያን  መፈናቀላቸውንም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

ይህ  በእንዲህ  እንዳለ በወረዳው  ካሉ 37 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ16 በላይ የሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውንና  ከእነዚህም  መካከል 3ቱ  መሉ በሙሉ መዘረፋቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

የኦርቶዶክሳዉያን  መገደል  እንዲቆም  ለሀገረ ስብከቱና  ለመንግሥት  አካላት  በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢደረግም  ምላሽ  እያገኙ  አለመሆናቸውን  ያነሱት  ነዋሪዎቹ  በዚህም አካባቢው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል  ሲሉ  ተናግርዋል፡፡

በተለይም በሀገረ ስብከት ደረጃ ለተፈናቀሉት ወገኖች ድጋፍም  ሆነ  ማጽናኛ  ለማደረግ ጥረት ባለመደረጉ  ማዘናቸውን የአካባቢው  ምእመናን  ገልጸዋል፡፡

እየደረሰ ያለው  የሰው ሕይወት እልፈት ፣ መታገትና የንብረት ውድመት ችግር እልባት አንዲያገኝ  የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት ባለድርሻ አካላት  አሁንም ትኩረት ሰጥተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 
ዘገባው የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ነው።

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment