ደብር ወገዳም
መልካም ቃላት የሚበዙት ክፉት ሲበዛ ነው። ሰው መልካም ሥራ ሲርቀው ክፋቱን ሊደብቅ ሲል መልካም ስም ማዕረግ ይደረድራል። መልካም ቃላት ጋጋታ ይጠቀማል። የዘንድሮን የመንፈስ እርቃንነት መቋቋም ያልቻለ ስው ግማሹ በስም ግማሹ ባሸበረቀ ካባና ቀሚስ እንደ ሞዴል በሚቀያየር አልባሳት ያጌጣል።
ቀደም ባለው ጊዜ የቆየው ባሕል ሊቃውንት ብቻ የሚጠሩበት ሥም አለ። እንደየ ትምህርታቸው እንደ ደብሩ ትልቅነት የአለቃ ስም ይሰጣል። ዛሬ ግን ስም ያልወሰደ የለም። የማይንቆለጳጰስ የለም።
| ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕርዳር እና የምዕራብ ጎጃም ሃገረ ስበከት ሊቀ ጳጳስ |
ሰላም በሌለበት ደብር የመልአከ ሰላም አበዛዙ፣ የተማረው የተመገበው ሳይኖር የመጋቤ ሐዶስና ብሉይ አበዛዙ ግርም ይላል።
መልአከ ከዋክብት፣ መልአከ ጨረቃ፣ መምህረ መምህራን፣ ርዕሰ ርዑሳን፣ ርዕሰ ባሕታውያን፣ ቆሞስ ሞቆሳት …..ሊቀ ሐዋርያት፣ መጋቤ ሰማእታት… ምኑ ቅጡ። አምፓል ለቀጠለ ኹሉ መልአከ ብርሃን።
አቡነ አብርሃም ደግሞ ሰሞኑን አንዲት ስም አስተዋውቀዋል። ደብር ወገዳም የምትል። የዶላር ስም ናት መሰለኝ። መቼስ ለብር ቤተ ክርስቲያን እንዲኽ ያለ ስም አይወጣም።
ደብር ሌላ ገዳም ሌላ። ደብር ወገዳም ማኪያቶ ናት። ደብር ከተባለ ምእመናንም አሉ ለማለት ገዳም ከተባለ ደግሞ መነኮሳት ብቻ የሚቀድሱበት ለማለት ካህናትን የመግፋት የተሸረበች የቆብ ስር ክፉ ስልት ናት። አቡነ ኢብራሂምን መች አጥቼ።
እንደ ጀግና እየጮኹ ነው ቤተክርስቲያንን አፈር ላይ ጥለዋት የሄዱት። አሜሪካም ተሻግረው ደብር ወገዳም የሚል ስም አውጥተዋል።
ይኽንን ያክል በዘረኝነት በበድንተኝነት ካህናትን ምእመናን ማናከስ መለያየት ምን የሚሉት አጋንንት ነው። ዘመዶቻቸውን ሰብስበው ጵጵስና ለማሾም ነበር ከአሜሪካም የጠሯቸው፣ እነ አቡነ ሳዊሮስን አዘዘባቸው በመተባበር ቤተክርስቲያን ገደል ከተቷት። እሱ አልሳካ ሲል ወደ አሜሪካ የጠብ ጸጋቸውን ላኩ።
የድርብ ታቦት ባሕል ሲገርመኝ እንደ ዘመኑ ልጅ ስም “ያልተለመደ ወጣ ያለ” በማለት ይመስላል “ደብር ወገዳም” በማለት መሰየም ይዘዋል። ለማንኛውም ደብር ወገዳም የጨዋ ስያሜ ነው። ካቴድራል የሚል የካቶሊክ ስም መሸከማችን ሳያንስ ደግሞ ደብር ወገዳም። አባ መምሬ ማለት ነው።
አሜሪካ ቨርጁንያ ያለች ቤተክርስቲያን የአቡነ አብርሃም የግል ካምፓኒ አይደለችም። የአባት ርስት አይደለም። አንድ ሊቀ ጳጳስ ድሮ የመሰረተው ሀገረ ስብከት ሲቀየር የእርሱ አይደለም። ድሮ መሠረትኩ ብሎ ዛሬ አያዝም። ሲቀየር ተቀየረ ነው አያዝም አይናዝዝም።
ዲሲ ላይ የቤተክርስቲያን ስያሜ የሚሰጡት አቡነ ፋኑኤል ናቸው እንጂ ማንም አይደለም። ደብሩም ስያሜ ከፈለገ የሚጠይቀው ሃገረ ስብከቱን ነው እንጂ በሪሞት የሚያዘውን ጳጳስ አይደለም። መጀመሪያ መስመሩን ማረም ያስፈልጋል።
ንዋይ ካሳሁን
No comments:
Post a Comment