ጥቅምት 7/2005 ዓ.ም
በስመ አብ ወወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
የአባቶቻችንን ትእዛዝ
መፈጸም እና ለተጀመረው እርቀ ሰላም መሳካት የልጅነት ድርሻችንን መወጣት መንፈሳዊ ግዴታችን ነው!
በሰሜን አሜሪካ
አኅጉረ ስብከት የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ
ቤተክርስቲያናችን የሰላም እና የአንድነት መሠረት ነች። ሰላም እና አንድነት ከቤተክርስቲያን
ተለይተው የሚነገሩም ሆነ የሚሰበኩ አይደሉም። ሆኖም ቤተክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የተፈራረቁባት
ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ህልውናዋን ሲጋፉ ፣ሰላም እና አንድነቷን ሲፈታተኑ ቢኖሩም በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ደም ስለተመሰረተች እና የክርስቶስን አርአያ በተከተሉ ጽኑአን አባቶች ሰማእትነት ተጠብቃ ስለቆየች
ሳትጠፋ እኛ ዘመን ላይ ደርሳለች። ነገር ግን የዘመኑን የቤተክርስቲያን ፈተና ለየት የሚያደርገው
ፈተናው የልጆችዋ መለያየት መሆኑ ነው። ይህም ልጆችዋ በአንድ የአስተዳደር ጥላ ውስጥ ሆነን ሥርዓተ አምልኮአችንን እንዳንፈጽም
እና ለመጪው ትውልድ መተላለፍ ያለበትን ትውፊት እና የተቀናጀ የቤተክርስቲያን አስተዳደር እንዳናቆይ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።
የቤተክርስቲያን ሰላም እና አንድነት መናጋት በአንድነት የነበሩ ልጆቿ እንድንለያይ፣ አስተዳደሯ
ከመሰረቱ እንዲነቃነቅ፣ ወገንተኝነት እንዲጠነክር፣ ጠላቶቿ መግቢያ ቀዳዳ አግኝተው ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ
አድርጓል። ልዩነቱ መፍትሔ ሳያገኝ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ ከቀድሞ ይበልጥ ወደከፋ እና ለዘመናት ወደማይሻር ችግር ውስጥ የሚከተን
እንደሆነ የሚያነጋግር አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ ልዩነቱ አክተሞ
አንድነቱ ወደነበረበት ከተመለሰ ሐዋርያዊት እና ዓለም አቀፋዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን ህልውናዋ ከስጋት ውስጥ እንዲወጣ፣ ተልዕኮዋን
በሚገባ እንድትፈጽም፣ እንዲሁም ከራሷ ልጆች አልፋ ለዓለም ሁሉ የመዳን
ተስፋ እንድትሆን ያደርጋታል። ስለዚህ ቀደምት አበው በተጋድሎ ያቆዩልንን የቤተክርስቲያን አንድነት ወደነበረበት ለመመለስ ሁሉም
የቤተክርስቲያን አካል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባው አያጠያይቅም።
በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት
የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤም ለተጀመረው
እርቀ ሰላም አባላቱ የልጅነት ድርሻቸውን ለመወጣት በታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን
ለመግለጽ ይወዳል። ከነሐሴ 25_ 27 2004 ዓ.ም በአሌክሳንድርያ ቨርጅንያ በተካሄደው በ12ኛው የአንድነት ጉባኤው አጠቃላይ
መደበኛ ጉባኤ ላይም ስለ ቤተክርስቲያን አንድነት መጠበቅ እና ስለ እርቀ ሰላሙ አስፈላጊነት አባላቱ በስፋት እና በጥልቀት መረጃ
ካገኙ እና ከተወያዩ በኋላ “የአባቶቻችንን ትእዛዝ መፈጸም እና ለተጀመረው እርቀ ሰላም መሳካት የልጅነት ድርሻችንን መወጣት መንፈሳዊ
ግዴታችን ነው” የሚል የውሳኔ ሃሳብ አጽድቀዋል።በተለይም የእርቀ ሰላሙ መሳካት ከፍተኛ የአብያተ ክርስቲያናት የልዩነት መንፈስ ባለበት
በሰሜን አሜሪካ የተፈጠረውን የአባቶች እና ምእመናን መከፋፈል ትልቅ እልባት እንደሚሰጠው እና ቤተክርስቲያን በውጭው ዓለም ለምታበረክተው
አስተዋጽዖ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የአንድነት ጉባኤው አባላት ጠቁመዋል። ለዚህም አባላቱ በየአጥቢያቸው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ
እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
ከብፁአን አባቶቻችን ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን መዋቅር ያሉ የተለያዩ አካላት በተለይም የሰላም
እና አንድነት ጉባኤ ለእርቀ ሰላሙ መሳካት እያደረጉት ያለው የተቀደሰ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ እያስደሰተን የሚገኝ ሲሆን በሀገር
ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚገኙ ምእመናንም ለጉዳዩ እየሰጡት ያለው ትኩረት የሚበረታታ እና እርቁ ከግብ ይደርስ ዘንድ በጸሎት
እና የሚገባውን ኃላፊነት ሁሉ መወጣት እንደሚያስፈልግ እናምናለን።
አምላካችን እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ተወግዶ እና
የቤተክርስቲያን አንድነት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሶ በአንድነት እንድናመሰግነው ያበቃን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ
ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ
አኅጉረ ስብከት
የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች
አንድነት ጉባኤ ስራ አመራር
ሰሜን አሜሪካ
ግልባጭ:
·
ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
·
በሰሜን አሜሪካ ላሉ ሦስቱም አኅጉረ ስብከት
·
ለሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት በያሉበት ፣
·
ለእርቀ ሰላሙ የሰላም
እና አንድነት ኮሚቴ
·
ለኢትዮጵያ የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት ፣
·
በካናዳ በአፍሪካና በአውሮፓ ለሚገኙ ሰንበት
ት/ቤቶች
ሙሉ መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
wow betam betam des yelal Egzabehar betkrsetyanchenen yetbkelen sol the canada
ReplyDelete