Thursday, October 11, 2012

ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩት አባላት በእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ተወያዩ




ከጥቅምት 6-11 ቀን 2005 . ጀምሮ ሠላሳ አንደኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይካሔዳል፡፡
የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋናው ስባሰባ ደግሞ ጥቅምት 12  እንደሚጀመር እየተጠበቀ ሲሆን በአሁን ሰዓት እንዱና አንገብጋቢው አጀንዳ የፓትርያርክ ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከውጪው ሲኖዶስ ጋር ያለውን እርቀ ሰላም በተመለከተ ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው ከአቡነ መልከፄዴቅ ጋር ብቻ ውይይት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን የዋናው ፓትርያርክ ምርጫ እስከ ሚከናወን ድረስ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩና ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር አብረው የሚሠሩት ሰባቱ አባላት    ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋር ወይይት ማድረጋቸው ተነግሯል ፡፡

በውይይቱም አቡነ መርቆሬዎስ ከዚህ በፊት እንደሚገመተው ሁሉ በገዳም መኖርን እንደሚመርጡና አንድ  ጊዜ የተጣሰው ስርዓት እሳቸው በህይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ እንዲመረጥ እንደማይፈቅዱና እሳችው እስኪያርፉ አሁን እንዳለው ቤተ ክርስቲያኗ በመንበረ ፓትርያርክ እየተመራች እንድትቆይ እንደሚሹ ማስታወቃቸውን ምንጮቻችን ዘግበውልናል፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤  አሜን፡፡


የፓትርያርክ ምርጫ
ቅዱስ ሲኖዶስ 1991 . ባወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ  ስለ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምዕራፍ አራት ላይ ያሉትን አንቀፆች እንመለከታለን

አንቀጽ 13
ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ በሚወስነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል::
  ለፓትርያርክነት የሚመረጡት ዕጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሦስት ያላነሡ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሔድ ይደረጋል፡፡
መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስትዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው 22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡
የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል፡፡
የተመረጠው ፓትርያርክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖናዋን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 14
የፓትርያርኩ የማዕረግ ስምና መንበር
ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይባላል፣ ስሙም በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ይጠራል፡፡
ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨ አገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው፡፡
አንቀጽ 15
የፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር
ፓትርያርኩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፡፡
 በዚህ ሕግ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡
ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 እና በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሲስማማበት ለብፁዓን ጳጳሳት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ይሰጣል፡፡
በዚህ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የተመረጡትን የሥራ ሓላፊዎች ይሾማል፤ በቀደምትነትና በታሪክ የታወቁትን የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የከፍተኛ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡለት የማዕረግ ስም እየሰጠ ይሾማል፡፡
ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመንግሥትን ፈቃድ ማግኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ በተግባር ላይ ያውላል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አያስወሰነ ይሠራል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጐች፣ የተላለፉ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ሕጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማው ያስተላልፋል፡፡
ከመንግሥታውያንም ሆነ መንግሥታውያን ካለሆኑ /ቤቶች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚቀርቡ ደብደቤዎች ወይም አቤቱታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው በሕግ መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ለጠቅላይ /ቤት ያስተላልፋል፡፡
በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለማገልገል ወይም የነፃ ትምህርት ለመማር የሚላኩ ካህናት በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 መሠረት ተመርጠው ሲቀርቡ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
ከውጭ የሚመጡትን እንግዶች በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቅራቢነት እየተቀበለ ያነጋግራል፡፡
ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጉብኝት ለማካሔድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልዕኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፡፡
አንቀጽ 16
የፓትርያርኩ ከማዕረግ መውረድ
ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተሾመ በኋላ የተቀበለውን ሓላፊነት በመዘንጋት፡-
        . የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
    . በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 172 እስከ 208 በተደነገገው መሠረት በደለኛ መሆኑ ከታመነበት፣
     . በቃሉ የማይገኝና በዚህ ሕግ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 7 ድንጋጌ መሠረት በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ያልጠበቀ በአጠቃላይ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ መሆኑ በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ ይወርዳል፤ በምትኩም ሌላ ፓትርያርክ ተመርጦ ይሾማል፡፡
     2.  ከዚህ በላይ በተደነገገው መሠረት ከሥልጣኑ የተገለለ ፓትርያርክ በቀኖና ተወስኖ በገዳም ይቀመጣል፡፡
    3. ከሥልጣን የተገለለው ፓትርያርክ በገዳም አልቀመጥም በቀኖናም አልወሰንም በማለት እምቢተኛ ከሆነ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል፡፡
      4.  ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራውን በማካሔድ ላይ እያለ እሥራትና ግዞት ቢደርስበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡
       5. ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዝዘው መሠረት ይፈጸማል፡፡
አንቀጽ 17
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
 ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ 40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
 የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡
/ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 ./
ደቂቀ ናቦቴ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment