(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 6/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 16/2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድነት አስፈላጊነት ከምንም በላይ በሁሉም ዘንድ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው ነው። በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም “አንድነት፣ እርቅ” የሚሉት ቃላት ተደጋግመው በመሰማት ላይ ናቸው። የቀጣዩ ፓትርያርኩ ጉዳይ ከእርቅ እና ከአንድነት በኋላ እንጂ በችኮላ አሁን መሆን እንደሌለበት አጽንዖት እየተሰጠው ባለው በአሁኑ ወቅት የየራሳቸውን ወገን “ፓትርያርክ” አድርገው ለማስሾም ፍላጎት አላቸው የተለያዩ አካላት፣ ቡድኖች፣ ግለሰቦች እና ስብስቦች በይፋ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከመንግሥት እንጀምር።
አቡነ ጎርጎርዮስ |
መንግሥት
መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን አስመልክቶ ያለውን የቆየ እና መሠረት የያዘ አቋም በተመለከተ ከዚህ ቀድሞ ሰፊ ሐተታ ማቅረባችን ይታወሳል። ያላነበበ ካለ ከዚህ (LINK) ያገኘዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመንግሥትን አቋም አስመልክቶ ወይም በመንግሥት ስም ስለ ዕርቀ ሰላሙ ሂደትና በቀጣዩ ፓትርያርክ መመረጥ ዙሪያ የሚሰማው መረጃ የተቀላቀለ ነው። (የሚባለውን በርግጥ የሚያደርገው ከሆነ ከሕገ መንግሥቱ ጋራ የሚጋጭ ነው፡፡) የአራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፍላጎት “በራሱ መንገድ አረጋግጧል” የተባለው መንግሥት÷ ቅዱስነታቸው ወደ አገር ቤት ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት በአዎንታዊነት ተቀብሎ ሲያበቃ የቅዱስነታቸው ፍላጎት ምንም ይኹን በአባትነታቸው በመንበሩ ተቀምጠው ማየት እንደማይሻና ዕርቀ ሰላሙ ይህን ሳይጨምር ሊፈጸም እንደሚችል አቋም ይዟል መባሉ ግን አሳሳቢ ኾኗል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ቀጣዩን ወይም ስድስተኛውን የፓትርያርክ ምርጫ እንድታከናወን፣ እንድታከናወን ብቻ ሳይሆን በዚሁ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅት ቀን ቆርጣ በፍጥነት እንድታከናወን እንደሚሻ ነው የሚነገረው፡፡
1. ምርጫ አንድ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
ከዚህም አልፎ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለአንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደ እንደራሴያቸውም እንደተተኪያቸውም አስተዋውቀዋቸው ነበር የተባሉትንየምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ስድስተኛው ፓትርያርክ ይኾኑ ዘንድ ወስኖ መግፋት መጀመሩ ነው የተሰማው፡፡ እንደ ምንጮች ማብራሪያ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ወደ ፕትርክናው መንበር መገፋታቸው÷ “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አቋም እና አሠራር (እነርሱ ራእይ ይሉታል) ያስቀጥላሉ፤ ለመንግሥት ለመታዘዝና ፍላጎቱን ለማስፈጸም ይመቻሉ” በሚል ሐሳብ ነው ተብሏል፡፡
2. ምርጫ ሁለት - ብፁዕ አቡነ ማቲያስ
የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልተሳካ ሁለተኛ አማራጭ ኾነው የተዘጋጁት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ለበርካታ ዓመታት በውጭ የነበራቸው ቆይታ፣ ከቤተ ክህነቱ ችግር ጋራ ብዙ ንኪኪና ትውውቅ የሌላቸው መኾኑና ከመንግሥት ጋራ አብሮ በመሥራት ረገድ አላቸው የሚባለው አቋም በጉዳዩ እጃቸውን ካስገቡት የመንግሥት ሓላፊዎች እና እነርሱን እየተባበሯቸው በሚገኙት የቤተ ክህነቱ ሰዎች በዕጩነት እንዲያዙ እንዳደረጋቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በአንድ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣን የሚመራ ነው በተባለው በዚህ የ“ቀራቤ-መንግሥት” ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ድጋፍ እየሰጡ ናቸው የተባሉት የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በዋናነት÷ በሦስት የአድባራት አለቆች የሚመራ አደገኛ የደላሎች ሰንሰለት በመዘርጋት ሙስናን በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አነገሱ የሚባሉትሥራ አስኪያጁ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን የሚጠቅስ ሲኾን ከእርሳቸውም ጋራ ዶ/ር ጸጋዬ በርሄ፣ መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ መጋቤ ሥርዐት ሙሉጌታ በቀለ፣ አቶ ተፈሪ የማነ፣ ዲያቆን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ዐማኑኤል የተባሉ እና ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ከነግብር አበሮቻቸው በቡድን አባልነት እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ |
ቡድን ስምንት
በሌላ መሥመር ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ቀዳሚ የፕትርክና ዕጩው በማድረግ በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) እየተገናኘ የሚመክረው ቡድን ስምንት የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አለቆችንና ጸሐፊዎችን በአባልነት የያዘ ሲኾን አንድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣንን በበላይነት መያዙ ይነገራል፡፡ ቡድኑን በቢሾፍቱ እና በአዲስ አበባም በታላላቅ ሆቴሎች እንደሚሰበስቡት የተመለከተውሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተክለ ጊዮርጊስ በእልቅና በተሾሙባቸው አድባራት ሁሉ በሙስናና ዘረፋ ቅሌቶች በካህናትና ምእመናን አቤቱታ በውርደት የመባረር ታሪክ አላቸው። ቡድኑን ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ አፍራሽ ዓላማቸው የተጋለጠው የ”ጉባኤ አርድእት” ነን ባይ ግለሰቦች፣ ከአንድም ሦስት የቤተ ክህነቱን ኪራይ ቤቶች በእርሷ እና በልጇ ስም ከመያዟ በተጨማሪ “ቀራንዮ በኢየሩሳሌም” በተሰኘውና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚካሄድበት የጉዟ ወኪሏ በኩል የምታገኘውን ጥቅም ለማስጠበቅ የምትሠራው እጅጋየሁ በየነ (ብዙዎች ኤልዛቤል በሚለው ያውቋታል)፣ ጉዳዩ ለጥቅምቱ ቅ/ሲኖዶስ በይደር የሚታይበት በጋሻው ደሳለኝና መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ በአባሪ ተባባሪነት እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡
የቀሲስ በላይ መኰንን ቡድን?
ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስሞች መጠለያ ያደረገው ሌላው ቡድን በአሁኑ ወቅት የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ዲን በኾነው ቀሲስ በላይ መኰንን ይመራል የተባለው ቡድን ነው፡፡ ቀሲስ በላይ መኰንን ለቦታው ብቁና ተገቢ (fit and proper) ሳይሆን በኮሌጁ ዲንነት እንደተቀመጠ ይነገራል። በኦህዴድ/ኢሕአዴግ አባልነቱ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተመራጭና የፓርቲ ፖሊቲከኝነት የሚጫነው ካህን ነው፡፡
አስገራሚው ጉዳይ ቡድኑ ኅቡእ እንቅስቃሴውን የጀመረው የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዜና ዕረፍት በተሰማበት ጥቂት ቀናት ውስጥ ግብአተ መሬታቸው ሳይፈጸም መኾኑ ነው፡፡ የቡድኑ ዋና ዓላማ “ኦሮሞ ጳጳስ በፓትርያርክነት ማስመረጥ” መኾኑ ተነግሯል፡፡ ለዚህም አንዳንድ የአድባራትና ገዳማት ሰበካ ጉባኤያት ክፍሎች ሓላፊዎችን፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ጥቂት የሥራ መሪዎችን፣ በጣት የሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተማሪዎችንና ጎሰኝነትን ሽፋን ባደረገ ጥቅመኝነት የናወዙ ጋዜጠኞችን በአሳታፊነት መያዙ ተጠቁሟል፤ ከአዲስ አበባ አስተዳደር እና ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተወሰኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም እንደ ማስፈራሪያ እንደሚጠቀምባቸው ይወራለታል፡፡ ወደ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጽ/ቤት ሳይቀር ስልክ እያስደወለ“ኦሮሞ ፓትርያርክ ካልተመረጠ የኦሮሞ ሕዝብ ይኹንታ የሌለበት ምርጫ ነው ብለን መግለጫ እናወጣለን” ብሎ እስከመዛት የደረሰው ይኸው ስብስብ ብፁዕ አቡነ ያሬድን አልያም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን ወደ መንበረ ፕትርክናው ለመግፋት እየሞከረ እንደኾነ ይነገርለታል፡፡
“ፕትርክና ለወሎ” የሚለው ቡድን
“የኦሮሞ ፓትርያርክ አስመርጣለኹ” ከሚለው ቡድን ጋራ በትይዩ የሚሻኮተው ሌላው ኅቡእ ቡድን ጉዳዩን በቅርበት በሚከታተሉት አካላት ዘንድ ‘w-group’ /ወሎ ግሩፕ/ ይባላል፡፡ ይኸው ቡድን “ጊዜው/ተራው የወሎ ነው፤ ፓትርያርኩም ከወሎ መኾን ይገባዋል” በሚል ይንቀሳቀሳል፡፡ እንቅስቃሴውን በዋናነት የሚያስተባብሩት የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል ናቸው፡፡ በጡመራ መድረኩ የመረጃ ምንጮች መሠረት ቡድኑ እንደምቹ ኹኔታ የወሰደው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤትና አህጉረ ስብከት ጀምሮ እስከ መምሪያ ሓላፊነት ድረስ ከፍተኛ ቦታ የያዙትንና በቁጥርም አንጻራዊ ብዛት ያላቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያና የጽ/ቤት ሓላፊዎች መኾኑ ተመልክቷል፡፡ በዋናነትየደቡብ ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስን ይህም ካልተሳካ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳን፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስን አልያም ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን ወደ መንበረ ፕትርክናው የማቅረቡን ሥራ በመግፋት ላይ መኾኑ ይነገርለታል፡፡
ሌላውስ ምን ይላል?
ጎልተው ከወጡትና በስም ከታወቁት ቡድኖች ውጭ በማኅበራት ስም የተደራጁና የየራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን በየፊናቸው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እንዳሉ የሚያስረዱት የመረጃ ምንጮቹ÷ ጥቅመኝነታቸውንና የፖሊቲካ ፍላጎታቸውን በጎሰኝነት መሳሳብ ለማስጠበቅ፣ ሲፈጽሟቸው በቆዩት ወንጀሎች ራሳቸውን ከተጠያቂነት የሚያድኑበትን ቀጣይ ኹኔታዎች ለመፍጠር የሚራወጡት ቡድኖች ይኹኑ ግለሰቦች ወደ ፕትርክናው መንበር ለመግፋት የሚያስቧቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና አጠቃላይ ሕዝቡን እንደማይወክሉ፣ ሊወክሉም እንደማይችሉ ይከራከራሉ፡፡
ሰሞኑን አገልጋዩና ምእመኑ አባ እገሌን ከአቡነ እገሌ በትውልድ ማንነታቸው ሳይለይ ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት እንዲጠብቅ፣ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ዶግማና ቀኖና መጽናትና መስፋፋት የሚቆም፣ ለመንጋው የሚራራ ቅንና ደገኛ አባት እንዲሰጥ በግልና በጋራ የያዘውን ጾምና ጸሎተ ምሕላ፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንኑ ለማስፈጸም እንዲተጋ በየአደረጃጀቱ ተፈራርሞ የሚያስገባቸው ማመልከቻዎች (ፔቲሽኖች) በአስረጅነት ይጠቅሳሉ፡፡ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት 131 ሰንበት ት/ቤቶችን በአንድነት የሚመራው ኅብረት፣ የፀረ ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት፣ ማኅበረ ቅዱሳን (ቴሌ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ጭምር) እና ሌሎችም ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያቀረቧቸው እና ለማቅረብ ያዘጋጇቸው ፔቲሽኖች ለዕርቀ ሰላም ንግግሩ፣ ለፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ዝግጅቱ፣ ለተቋማዊ ማሻሻያ ጥረቱ ስኬት ጥንቃቄ የተመላበት አካሄድ እንዲኖር የሚያሳስቡ ናቸው፡፡
ከመስከረም 16 - 24 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ከአራቱም ማእዝናት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያምለተመመው በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠር ኦርቶዶክሳዊ ምእመን የፀረ - ተሐድሶ ሰባክያን ጥምረት አባላት እና መንፈሳውያን ማኅበራት (የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ተምሮ ማስተማር፣ የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምክሐ ደናግል፣ ማኅበረ ሰላም፣ ኢያቄም ወሐና፣ ማኅበረ ጽዮን፣ ማኅበረ ሐመረ ኖኅ፣ ማኅበረ አሮን፣ ማኅበረ ፋኑኤል፣ የሰዓሊተ ምሕረት. . .ወዘተ) በየማረፊያ ድንኳናቸው፣ ምእመኑ በተጓጓዘባቸው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ውስጥ ሳይቀር የወቅቱን ኹኔታ አስመልክቶ የዘረጓቸው የትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች፣ መዝሙሩ እና ስብከቱ ሳይቀር የጎሰኞችን፣ የጥቅመኞችንና የፖሊቲከኞችን ፍላጎት በምኞትነቱ የሚያስቀር፤ ምእመኑን ከባይተዋርነት አውጥቶ በአንድ ቃልና መንፈስ ባለቤትና ንቁ ተሳታፊ እንደሚያደርገው ምንጮቹ ይመሰክራሉ፡፡ በትምህርቶቹ እና ስብከቶቹ ላይ ተመሥርቶ በተካሄዱ የሐሳብ ልውውጦችም ምእመኑ በቀጣይ በሚደረጉ ጥረቶች ከሚመለከተው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካል ብቻ የሚተላለፍለትን መልእክት እንደሚከታተልና የተጠየቀውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አቋሙን መግለጹ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት መጠበቅና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መርጦ ከሚሾመው በቀር የማንንም ጫና ላለመቀበል መወሰኑን እንደሚያሳይ ምንጮቹ በሙሉ ልብ ይናገራሉ፡፡
ይኸው የአገልጋዩና ምእመኑ አስተሳሰብና አቋም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ዘንድም የሚታይ ነው፡፡ አንድ ብፁዕ አባት እንደተናገሩት በሞተ ዕረፍት ከመለየታቸው በፊት በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ነገሮች ተፈጽመው ማየት ይፈልጋሉ፡፡ አንደኛው÷ ባለፉት ኻያ ዓመታት በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ የተፈጠረው ሥብራት እንዲጠገን ነው፤ ሁለተኛው÷ ደግሞ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱና እስከ አጥቢያ ለሚገኙት መዋቅሮቹ መንፈሳዊ፣ ብቁና ተገቢ የለውጥ መሠረት ተጥሎ ማየት ነው፡፡ በመኾኑም የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅ/ሲኖዶስ ከአኀት አብያተ ክርስቲያን ልምዶች በመማር፣ የአገራችንን ሕጎችና የቤተ ክርስቲያናችንን የግማሽ ምእት ዓመት የመንበረ ፕትርክና ተሞክሮ በመቀመር አዳብሮ አዘጋጅቶታል በተባለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ ለውይይት በሚቀርበው የቃለ ዐዋዲ ደንብ እና ቋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ መሠረት ከሚወሰነው ውጭ የማንኛውንም አካል ጫና ለመመከት፣ ለዚህም መሥዋዕት ለመኾን የተዘጋጁ ብፁዓን አባቶችን ማየት በርግጥም የሚያኮራ ነው፡፡ የውጭ ተጽዕኖ መግቢያው የብፁዓን አባቶች አንድነት መላላት ነውና በተለያዩ መደለያዎችና ማስፈራሪያዎች ሳይበገሩ ተስፋችንን ለቤተ ክርስቲያናችን ሉዓላዊ የመወሰን ሥልጣንን በሚያጎናጽፏት ሕጎች፣ አሠራሮችና ውሳኔዎች ላይ ብቻ ማድረግ በእውነትም የመሥዕትነት ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ117ኛው የኮፕቱ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ዕረፍት በኋላ ወራትን በወሰደው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሽግግር ጊዜ እያየነው እንዳለነው÷ ቤተ ክርስቲያናችንም ዐበይት የሽግግር ወቅት ሥራዎቻችን እንዴት፣ በማንና በምን ያህል ፍጥነት ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱመርሐ ድርጊት (Road Map) ቢያዘጋጅ የሥራውን ርምጃ ለመለካት ያስችለዋል፡፡ ከመርሐ ድርጊቱም ጋራ በአንድ ብፁዕ አባት የሚመራ የቃል አቀባይ ጽ/ቤት አቋቁሞ እንደ አስፈላጊነቱ ለብዙኀን መገናኛ፣ ለአገልጋዩ፣ ምእመኑና ለሚመለከታቸው ሁሉ በየጊዜው ርምጃዎቹን ቢያሳውቅ ከላይ የተገለጹትን ዐይነት የግብረ በላዎች ቡድን የሚራባበት ማኅበራዊ መሠረት እንደሚደርቅ፣ አውዳሚ ድርጊቱንና የሚነዛውን አሉባልታም ለመግታት አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ምንጮቹ ይመክራሉ፡፡
እንግዲህ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ዘላቂ ሰላም ጉዳይ በዚህ ደረጃ ይገኛል። የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት እና የመጠናከር ተስፋ በጎሰኛ፣ ጥቅመኛ እና ፖሊቲካዊ ፍላጎታቸው ለማምከን እየሠሩ የሚገኙትንና የቤተ ክርስቲያናችንን ተስፋ ለማጨለም የሚጥሩትን ወገኖች ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ከድርጊታቸው ሊያስቆሟቸው ይገባል። ለዚህም ደጀ ሰላም አቤት ትላለች፤ በአቤቱታዋም ትቀጥላለች ! ! !
ልዑል እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅልን፤ ቅን ደገኛ አባት ይስጥልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
No comments:
Post a Comment