Monday, October 15, 2012

ዐቃቤ መንበሩ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ የስልክ ውይይት አደረጉ



(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 5/2005 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 15/2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከአራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋራ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተሰማ፡፡ የውይይት መሥመሩን ያመቻቸው በውግዘት በተለያዩት አባቶች መካከል ዕርቀ ሰላም ወርዶ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት ይጠበቅ ዘንድ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው “የሰላምና አንድነት ጉባኤ” ነው፡፡ በሁለቱ አባቶች የስልክ ውይይት÷ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጋራ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፤ ከአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋራ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አብረው መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡


የውይይቱ ምንጮች ለደጀ ሰላም እንደገለጹት÷ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መከበር ላይ ትኩረት በመስጠት ተናግረዋል፡፡ ቅዱስነታቸው ወደ መንበራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ቢኾኑም በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ተቀምጠው ቅዱስ ሲኖዶሱን በርእሰ መንበርነት እየሰበሰቡ አመራር የመስጠት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የፕትርክናው መንበር በእንደራሴነት በሚመረጥ ብፁዕ አባት ተጠብቆ ቢቆይ ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መከበር እና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት መመለስ አስፈላጊ በመኾኑ በዚሁ መንገድ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት መልካም ፍጻሜ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ፣ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩም የበኩላቸውን ሓላፊነት እንዲወጡ ማሳሰባቸው ተዘግቧል፡፡

ሓላፊነታቸው መንበሩን መጠበቅ መኾኑን፣ ለዕርቀ ሰላሙ ንግግር ሥምረትም የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት እንደሚወጡ የተናገሩት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የቅዱስነታቸውን ሐሳብ ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቅርበው እንደሚነጋገሩበት ገልጸውላቸዋል፤ በውይይቱም ቅዱስነታቸው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ላቀረቡላቸው ጥያቄም ቅዱስነታቸው ቀሪ ዘመናቸውን በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስኖ መቆየትን እንደሚመርጡ መመለሳቸውን በመግለጽ ምንጮቹ አክለው አስረድተዋል፡፡ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ከአቡነ መርቆሬዎስ ጋራ የተካሄደውን የስልክ ውይይት ዐሥራ አምስት አባላት ላሉት ቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ሪፖርት ማድረጋቸውን ደጀ ሰላም ያረጋገጠ ሲኾን በመጪው ጥቅምት 12 ቀን ጀምሮ በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአጀንዳነት ቀርቦ ዐቢይ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስበት ተስፋ ተደርጓል፡፡

የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀዳሚ የውይይት አጀንዳዎች እንደሚኾኑ ከሚጠበቁት መካከል፡- በየዘመኑ ለተሾሙት አምስት ፓትርያርኮች አመራረጥ ይዘጋጅ ከነበረው ተለዋዋጭየፓትርያርክ ምርጫ ደንብ ይልቅ ቋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ረቂቅ፤ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቃለ ዐዋዲው ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፤ በማሻሻያዎቹ የሚመጣውን ተቋማዊ ለውጥ የሚሸከምና የሚያስፈጽም የተጠናከረ የቅዱስ ሲኖዶስና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መዋቅርየሚሉት ወሳኝ ጉዳዮች የሚኖሩ ሲኾን ከዚህም ጋራ አሁን በመልካም ሂደት ላይ የሚገኘውን የዕርቀ ሰላም ንግግር በአጭር ጊዜ ወደ ፍጻሜ የሚያደርሱ የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡካን ከብቁ እና ተገቢ የሰው ኀይል ጋራ የሚሠየሙበት እንደሚኾን ተጠቁሟል፡፡

ነገር ግን÷ እኒህ በየጊዜው እየተሞከሩ በየምክንያቱ ሲደናቀፉ የቆዩና ባለንበት መድረክ ወሳኝ የሰላምና አንድነት፣ የተቋማዊ መሻሻልና መጠናከር አጀንዳዎች የኾኑት የቤተ ክርስቲያናችን ነባር ችግሮች አሁን በሰላምና አንድነት ጉባኤው፣ በቀድሞው ፓትርያርክ፣ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ እና በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ በሚታየው ተስፋ ሰጪ አያያዝ ከመሠረታቸው እንዳይፈቱ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አሉባልታዎች እና ድርጊቶች በቸልታ ሊታዩ አይገባም እንላለን፡፡

የሰላም እና አንድነት ጉባኤው እንደ አካል ይኹን አባላቱም እንደ ግል ለሁለቱ ተወያይ አባቶች በማእከላዊነት ማገልገላቸው መልካም ኾኖ በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚሰጠው በሚጠበቀው መግለጫም በወዲያኛውም በወዲያኛውም የተፈጸሙና ቅር ከማሰኘት አልፎ አደናቃፊና ጣልቃ ገብ ተግባራትን የሚገሥጽ፣ ጠቅላላ ሂደቱም በተፋጠነ አኳኋን ወደፊት ተራምዶ በአጭር ጊዜ ወደ ፍጻሜ የሚደርስበትን መንገድ የሚጠቁም እንዲኾን ያስፈልጋል፡፡ ከኻያ ዓመት በኋላ ለሰላም፣ ዕርቅና ፍቅር ከመሥራት አልፈው ጥብቅና መቆም የሚገባቸው ብፁዓን አባቶች አንድነት እንዲፈጥሩ ለማግባባት ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ይኖርብናል?!

በተያያዘ ዜና ይህንኑ አባቶችን እርቅ እና አንድነት በተመለከተ ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው የሁለተኛ ሳምንት የስልክ ውይይት ትናንት እሑድ ተደርጓል። አበው ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን እና የተለያዩ ምሁራን አስተያየታቸውን በሰጡበት በዚህ ዝግጅት ላይ በወቅቱ ለተነሡ የተለያዩ ጥያቄዎች ከማኅበሩ እና በአስረጂነት ከቀረቡት ከ“የሰላምና አንድነት ጉባኤ” አባላት ምላሽ ተሰጥቷል። ተሰብሳቢዎቹ በሰሜን አሜሪካ ያለው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ክፍፍል ማብቃት እንዳለበት በጥልቅ መንፈሳዊ ስሜት ሲገልጹ ከመሰማታቸውም በላይ በቀጣይነት ሁሉንም የሚያሳትፍ እና እንቅስቃሴ የጀመረውን ““የሰላምና አንድነት ጉባኤ” ሊረዳ የሚችል ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment